ያለ ግብ ከተጠናቀቀው የ9ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ የሀዲያ እና ሀዋሳ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።
አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
በጨዋታው ስለነበረው አካላዊ ጉሽሚያ
ጨዋታው አካላዊ ጉሽሚያዎች የበዙበት ስለነበረ ሁለታችንም በምንፈልገው መንገድ አልተጫወትንም። ከነበረው የተሻለ የኳስ ፍሰት ይኖራል የሚል ግምት ነበረን። ነገርግን ያሰብነውን ነገር ለመፈፀም አልቻልንም። በአጠቃላይ በጨዋታው ሁለታችንም ቡድኖች ያሰብነውን ተግብረን ተጫውተናል ብሎ መናገራቸውን ያስቸግራል።
ተስፋዬ አለባቸውን ተክቶ ስለገባው ብሩክ ቃልቦሬ
ብሩክ ከአንድ ዓመት በላይ ነው ከሜዳ የራቀው። እሱን ቀይረህ ከሜዳ ብታሶጣ የሚፈጥረው የአምሮ ተፅዕኖ አለ። ከጨዋታ የራቀ ከመሆኑ አንፃር መፍረድ ከባድ ነው። ቢሆንም ግን የምፈልገውን ነገር ከብሩክ አላገኘሁም። ነገርግን ወደፊት ተሻሽሎ ይጠቅመናል የሚል ዕምነት አለኝ።
ፎፋና እና ዳዋ ስለነበራቸው ጥምረት
የምፈልገውን ታክቲካል ዲስፕሊን ከእነርሱ አግኝተናል። ግን እኛ ኳስ ስናገኝ አስበን የነበረው ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ልከን በ4 ተጫዋች ለማጥቃት ነበር። ነገርግን ሜዳ ላይ እንደታየው መስመሩን በደንን አላጠቃንበትም። ይሄ ክፍተታችን ነበር። ይህ ለሚቀጥለው ጥሩ የቤት ስራ ይሆነናል።
ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
በጨዋታው ስለተመዘገቡት 43 ጥፋቶች
በጨዋታው እንደዚህ እንደሚሆን እርግጥ ነው፣ የታወቀ ነው። የፈለከውን ነገር ለማድረግ ትንሽ ከበድ ይላል። ዞሮ ዞሮ ግን መልካም ነው።
የቡድኑ አጥቂዎች አጥተውት ስለነበረው የመጫወቻ ክፍተት እና ቡድኑ
በእንደዚህ አይነት ጨዋታዎች ላይ የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ትንሽ ከበድ ይላል። ጥንቃቄን ከመፈለግ ሳይሆን የጨዋታ እንቅስቃሴው ጎል አካባቢ ብዙም ባለመቆየቱ ነው። ኳሶች ቶሎ ቶሎ በረዥሙ ይመቱ ነበር። ከዚህ መነሻነት ክፍተቶችን ለመፍጠር እና ተደራጅተን ለመሄድ ትንሽ ጭንቅንቅ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሰው በሰው አያያዝ ነበር። ይህ የምንፈልገውን ነገረኝ እንዳናደርግ አድርጎናል። እንደሚታወቀው ደግሞ አጥቂዎቻችን ትንሽ ትኩረት ተደርጎባቸዋል። በጨዋታውም እንደፈለጉ ሊንቀሳቀሱ አልቻሉም። በአጠቃላጥ ሀዲያዎች አግሬሲፍ ሆነው ነው ሲጫወቱ የነበረው። እርግጥ እነሱ ይዘውት የመጡት ነገር ነው። እኛ ግን ይዘነው የመጣነውን ነገር አልተገበርንም። በተለይ የመስመር ላይ አጨዋወታችንን ለማቆም ሞክረውብናል። ኳስን ለማደራጀትም ትንሽ ተቸግረናል። የሆነው ሆኖ ጨዋታው ትንሽ ከበድ የሚል ነበር። አቻ መጠናቀቁም ለሁለታችንም ቡድኖች ፍትሀዊ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ