ሪፖርት | ከፍተኛ አካላዊ ፍትጊያን ያስተናገደው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

ሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው ጨዋታ በርካታ ጥፋቶች ተመዝግበውበት 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ ሲዳማን በረታበት የመጀመሪያ አሰላለፉ ዛሬም ወደ ሜዳ ሲገባ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከቅጣት የተመለሰላቸውን ግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪን በደረጄ ዓለሙ መድሀኔ ብርሀኔን በአዲስ ህንፃ ምትክ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

እጅግ በርካታ የሜዳ ላይ ግጭቶችን ያስተናገደው የቡድኖቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ሙከራዎች ሳይታዩበት ነበር የተጠናቀቀው። እንደወትሮው በመስመሮች በኩል አድልተው በቅብብሎች እና በተሻጋሪ ካሶች አደጋ ለመፍጠር የሚሞክሩት ሀዋሳዎች ወደ ሀዲያ የግብ ክልል ለመድረስ ከብዷቸው ታይተዋል። ሆሳዕናዎችም ቢሆኑ ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸውን ረዘም ባሉ ኳሶች ለማግኘት ቢሞክሩም ተጋጣሚያቸውን ማስጨነቅ አልቻሉም። ከ ሃያ በላይ ጥፋቶች ባስተናገደው አጋማሽ በጡንቻ መሸማቀቅ ተቀይሮ ከወጣው ተስፋዬ አለባቸው ሌላ የከፋ ጉዳት አለመድረሱ በራሱ የሚገርም ነበር። በአጋማሹ ተቀይሮ የገባው ብሩክ ቃልቦሬ ከረጅም ጊዜያት በኋላ ወደ ጨዋታ ተመልሶም ታይቷል።

የመሀል ዳኛው ዮናስ ማርቆስን ትዕግስት መፈታተኑን የቀጠለው ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው የጥፋት ቁጥሩን በእጥፍ አሳድጓል። በእርግጥ ቡድኖቹ ከዕረፍት ሲመለሱ ዕድል መፍጠሩ የተሻላ ነበሩ። ሀዲያ ሆሳዕናዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ መትቶ የወጣበትን ሙከራ ሲያደርጉ 59ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አይዛክ ኢሲንዴ ከግብ አፋፍ ላይ ወደ ላይ በላከው ኳስ ለግብ ቀርበው ነበር። በሀዋሳ በኩል የተደረገው እና የጨዋታው ብቸኛ ኢላማውን የጠበቀ የቅጣት ምት ሙከራ በመሀመድ ሙንታሪ ድኗል። ቀስ በቀስ የሙከራዎች ቁጥር እየቀነሱ የሄዱበት ጨዋታ ወደ ኃይል የቀላቀለ እንቅስቃሴ ቀጥሎ ያለግብ ተጠናቋል።



© ሶከር ኢትዮጵያ