የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛው ዙር ምርጦች

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ከታኅሣሥ 10 እስከ ጥር 21 ድረስ በሀዋሳ ከተማ ተደርጎ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የታዩ ምርጥ ግብ ጠባቂ ፣ ምርጥ ተጫዋች ፣ ተስፈኛ ተጫዋች እንዲሁም የውድድሩ ምርጥ አሰልጣኝ በሚል እንዲህ ተመልከተናቸዋል፡፡

ውድድሩ በአስር ክለቦች መካከል ጥሩ ፉክክር ሲደረግበት የነበረ ሲሆን ተስፋ የሚሰጡ አዳዲስ ተጫዋቾች ብቅ ያሉበት እንደሆነም በስፍራው በነበርንበት ወቅት በሚገባ አስተውለናል፡፡ በተለይ ከዚህ በፊት ስማቸው ጎልቶ ከሚጠሩ ተጫዋቾች ዕኩል በሜዳ ላይ አዳዲስ ፊቶችን የተመለከትን ሲሆን ለየክለቦቻቸው ካደረጉት አስተዋፅዖ አንፃር በቀጣይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ይህንኑ ብቃት ማስቀጠል ከቻሉ ለውጤታማነት ያለ ጥርጥር መሠረት መሆን እንደሚችሉ መናገር ይቻላል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ይህንን ውድድር ሳታቋርጥ በስፍራው ተገኝታ ሽፋን ስትሰጥ የነበረ ሲሆን ለአንባቢያን ካቀረበቻቸው መረጃዎች በተጨማሪ ከቀናት በፊት የአንደኛውን ዙር ምርጥ 11 ተጫዋቾች ወደ እናንተ ማቅረቧ አይዘነጋም። ዛሬ ደግሞ ከተደረጉ የዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎች ለየክለቦቻቸው ካደረጉት እንቅስቃሴ አንፃር በተለያዩ ዘርፎች ምርጥ ያልናቸውን እነሆ ብለናል።

ምርጥ ግብ ጠባቂ – ታሪኳ በርገና (መከላከያ)

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ላይ በርካታ አዳዲስ ብሎም ጥሩ ብቃት ያሳዩ ግብ ጠባቂዎችን ተመልክተናል፡፡ የሀዋሳ ከተማዋ ዓባይነሽ ኤርቄሎ ፣ የድሬዳዋ ከተማዋ ሒሩት ደሴ ፣ የንግድ ባንኳ ንግስቲ መዐዛ ፣ የጌዲኦ ዲላዋ መስከረም መንግሥቱ እና የአርባምንጭ ከተማዋ ድንቡሽ አባ በውድድሩ ላይ ጎልተው የታዩ ግብ ጠባቂዎች የነበሩ ቢሆንም የታሪኳ በርገናን ያህል ግን በሜዳ ላይ አስደናቂ ብቃቱን ያሳየ አለ ለማለት ያዳግታል፡፡

2007 ላይ ከትምህርት ቤቶች ውድድር ከተገኘች በኃላ በድሬዳዋ ከተማ ፣ ጥረት ኮርፖሬት እና ከተሰረዘው የውድድር ዓመት ጀምሮ ደግሞ በመከላከያ እየተጫወተች የምትገኘው ታሪኳ ከክለብ ህይወቷ ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመመረጥ ሀገሯን አገልግላለች፡፡ በቅርቡ በተደረገው የ2013 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የመጀመሪያው ዙር የሀዋሳ ውድድር ላይ ለመከላከያ ተሰልፋ በመጫወት በሜዳ ላይ ቡድኗ ጎል እንዳይቆጠርበት እንደ ቡድንም ሆነ በአንድ ለአንድ ግንኙነት አጥቂዎችን ኳስ ታስጥል የነበረበት መንገድ እጅጉን አስደናቂ እንደነበር ማየት ተችሏል፡፡ ክለቧ መከላከያ ዘጠኝ ጨዋታዎችን (የፎርፌ ውጤትን ጨምሮ) ሲያደርግ ታሪኳ በመጨረሻ ሳምንቱ ጨዋታ ብቻ በጉዳት ያልተሳተፈች ሲሆን በተሰለፈችባቸው ጨዋታዎች ለንግድ ባንክ አሳልፈው የሰጡትን የፎርፌ ጨዋታ ሳይጨምር በሰባት ጨዋታዎች 6 ጎል ብቻ ተቆጥሮባታል፡፡ ታሪኳ በተሰለፈችባቸው ጨዋታዎች ክለቧ ውጤታማ ከመሆኑ እና በሜዳ ላይ በነበራት ብቃት በመነሳት የ2013 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ምርጥ ግብ ጠባቂ በማለት መርጠናታል፡፡

ምርጥ ተስፈኛ ተጫዋች – አረጋሽ ካልሳ (ንግድ ባንክ)

በውድድሩ ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ሊጉ የመጡ ቁጥራቸው ላቅ ያሉ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች መመልከት ችለናል፡፡ ለአብነትም የጌዲኦ ዲላዋ እፀገነት ግርማ ፣ የአቃቂ ቃሊቲዋ ቤዛዊት ንጉሤ ፣ የአዲስ አበባ ከተማዋ እምወድሽ አሸብር ፣ የድሬዳዋ ከተማዋ ፀሐይነሽ ጁላን በማሳያነት መጥራት ብንችልም የአረጋሽ ካልሳ ግን የተለየ ነበር። በሁለት ጨዋታዎች ላይ በኮቪድ 19 የተነሳ ለክለቧ ተሰልፋ መጫወት ያልቻለች ቢሆንም አገግማ ከተመለሰች በኋላ ግን በማይቋረጥ አቋሟ በማንፀባረቅ ለንግድ ባንክ ጥንካሬን መፍጠር ችላለች፡፡ በተለይ ባንክ እሷን ባጣበት ወቅት የተቸገረባቸው ሁነቶች ጎልቶ መታየቱ ተጫዋቿ በክረምቱ ወደ ክለቡ መቀላቀሏ ለአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ስብስብ ማማር ወደር የሌለው አስተዋጽኦን እንዳበረከተ መመስከር ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን በስተመጨረሻ ለፎርፌ የዳረገ ክስተት በነበረው እና አረጋሽ በተመለሰችበት የመከላከያ ጨዋታ ተቀይራ በመግባት ቡድኑ ላይ የነበረውን ድክመት በሚገባ ታርሞ ወደ ውጤት እንዲያመራ ጎል በማስቆጠርም ጭምር ቡድኗን የታደገችበት መንገድ የዚህችን ተስፈኛ ጥንካሬ የሚያሳይ ነበር፡፡ ተጫዋቿ በሰባት ጨዋታዎች ያገለገለች ሲሆን ሜዳ ውስጥ ከነበረችባቸው 665 ደቂቃዎች ውስጥ ከተለመደው የመሀል ሜዳ ተጫዋችነቷ ወደ ግራ መስመር አጥቂነት በመሸጋገር 6 ኳሶችን በተቃራኒ ቡድን ላይ አስቆጥራ 2 ወደ ጎልነት የተለወጡ ኳሶችን ለቡድን ጓደኞቿ በማቀበል ከነበራት ተፅዕኖ አንፃር የሶከር ኢትዮጵያ የአንደኛው ዙር ምርጥ ተስፈኛ ተጫዋች ተብላ ለመመረጥ በቅታለች፡፡

ምርጥ አሰልጣኝ – ብርሀኑ ግዛው (ንግድ ባንክ)

ለኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ዕድገት የድርሻቸውን ከተወጡ አሰልጣኞች መከከል ይጠቀሳሉ፡፡ ረጅም ዓመታትን በዘለቀው የአሰልጣኝነት ዘመናቸው በሴቶች እግር ኳስ ላይ የነበራቸው ተሳትፎ እና ውጤታማነትም በቀላሉ ተጠቅሶ ብቻ የሚታለፍም አይደለም። በዘንድሮ የአንደኛ ዲቪዚዮን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ በነበረው የአንደኛው ዙር ቆይታ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ውጤታማ እና ጠጣር የነበረ ቡድንን ይዘው በመቅረብ በ100% የድል ጉዞ በመሪነት እንዲያጠናቅቅ የአሰልጣኙ ሚና ከፍተኛ ነበር። በድኑ ዘጠኙንም ጨዋታ አሸንፎ በተጋጣሚ ቡድን ላይ 39 ጎሎችን አስቆጥሮ 4 ብቻ ተቆጥሮበት 35 ንፁህ ጎሎች በመያዝ በ27 ነጥቦች ዙሩን መፈፀሙ አሰልጣኙ የሶከር ኢትዮጵያ የአንደኛው ዙር ምርጥ አሰልጣኝ ተብለው እንዲመረጡ ምክንያት ሆኗል፡፡

ምርጥ ተጫዋች – ማዕድን ሣህሉ (ድሬዳዋ ከተማ)

በሀዋሳ በነበረው የአንደኛው ዙር የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ እንደ ክስተት ከታዩ ተጫዋቾች መካከል የድሬዳዋ ከተማዋ የመሀል ሜዳ ሞተር ማዕድን ሣህሉ ቀዳሚውን ቦታ ትይዛለች፡፡ ድሬዳዋ ከተማ ምንም እንኳን አጀማመሩ ደካማ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ወደ ጨዋታ ጥንካሬን በመያዝ ከነበረበት ድክመት በሚገባ እንዲያገግም የዚህች ወጣት እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ድሬዳዋ የእንቅስቃሴ ብልጫን ሲወስድ ከመሀል ሜዳ ተጫዋችነቷ በዘለለ ወደ ፊት በመሳብ እና ቡድኑ የሜዳውን ስፋት እንዲጠቀም ታደርግ የነበረበት ሂደት እጅጉን አስደናቂ ነበር፡፡ በተለይ ድሬዳዋ በሂደት ቅርፅ እየየያዘ ሲመጣ ኳስን በማደራጀቱ እና ከአጠገቧ ካሉ ተጫዋቾች ጋር በቅብብሎች ወደ ፊት ለመሄድ የምትሞክርበት መንገድ የተጫዋቿን ብልህነት በሚገባ ያሳየ እንዲሁም ለድሬዳዋ ስኬት መነሻ የሆነ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ተጫዋቿ ምንም እንኳን ጎል በማስቆጠሩ ረገድ ድክመት ቢታይባትም የቡድን ጓደኞቿ ጎል እንዲያስቆጥሩ 6 ወደ ጎልነት የተለወጡ ኳሶች በዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ በማቀበል የሚስተካከላት አልተገኘም። ማዕድን ለድሬዳዋ መነቃቃት በግሏም በፈጠረችው ተፅዕኖ የአንደኛው ዙር ምርጥ ተጫዋች ተብላ በድረ-ገፃችን ተመርጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ