የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዕለተ ሰኞ ውሎ

ምድብ ሀ
ረፋድ 04:00 ላይ የተደረገው የገላን ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ጨዋታ በገላን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጅብሪል አህመድ በ17ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ብቸኛ ጎል ገላንን በሰንጠረዡ አናት ላይ በሚደረገው ፉክክር ለመቀጠል የሚያስችለውን ድል እንዲያሳካ ረድታለች።

09:00 ላይ በቀጠለው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ ግብር ሰሜኖ ሸዋ ደብረ ብርሀንን የገጠመው ደሴ ከተማ 2-0 አሸንፏል። ማትያስ መኮንን በ55ኛው እንዲሁም መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ በረከት አድማሱ ለደሴ ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ድሉን ተከትሎም የያሬድ ቶሌራው ደሴ የምድቡን መሪነት ከደሴ ከተማ ተረክቧል።

ምድብ ለ

ማለዳ 2፡00 ሲል የምድቡ መሪዎች አዲስ አበባ ከተማን እና ሀምበሪቾን ዱራሜን አገናኝቷል፡፡ ብርቱ ፉክክር የታየበት ነገር ግን አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች በርክተው በታዩበት ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በመስመር አጨዋወት ሲጫወቱ የነበረበት መንገድ በሀምበሪቾ ላይ ብልጫን ወስደው እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል፡፡ ሀምበሪቾዎች ከዚህ ቀደም ሲጫወቱ የነበረበትን የመሐል ሜዳ እንቅስቃሴ በመገደብ ዛሬ ቁጥብ ሆነው መዋላቸው ለተጋጣሚያቸው ምቾትን የፈጠረ ነበር፡፡በመስመር በኩል የአቡበከር እና ፍፁም ተለዋዋጭ እንቅስቃሴ ጠጣር የነበረው የሀምበሪቾ ተከላካይ ጠንክሮ ባይቀርብ ኖሮ አደጋን ይፈጥሩ ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ወደ ግብ ለመድረስ በመቸገራቸው ከርቀት ብዙአየው ሰይፉ ያደረጋት ሙከራ ለዚህ ማሳያ ነበር፡፡ ከእንቅስቃሴ ውጪ ብዙም የግብ ዕድሎችን ያልተመለከትንበት ቀዳሚው አርባ አምሰት 28ኛው ደቂቃ ላይ የሀምበሪቾው ማሊያዊ ተከላካይ አዳማ ሲሶኮ በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ጥላሁን ከመረብ አሳርፎ አዲስ አበባን መሪ አድርጓል፡፡

ከእረፍት መልስ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ሦስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ለውጠው ከገቡ በኃላ ደካማ ከነበሩበትን የማጥቃት ኃይል በሚገባ ተሻሽለው ወደ ሜዳ በመግባት በተደጋጋሚ ጫናዎችን ሲያሳድሩ የታየበት፤ አዲስ አበባ ከተማዎች በአንፃሩ አመዛኙ ሰዓታቸውን ያስቆጠሩትን ጎል አስጠብቆ ለመውጣት ወደ መከላከሉ አመዝነው በሚገኙ ክፍት አጋጣሚዎች ግን በመልሶ ማጥቃት ወደ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ በመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ብዙዓየው ሰይፉ ጥረት የተወሰኑ ዕድሎችን ለመፍጠር ታይተዋል፡፡ ይሁንና የዕለቱ ዋና ዳኛ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የነበራቸው ደካማ ብቃት ጨዋታው ወደ ሽኩቻዎች እንዲለወጥ ያደረጉ ነበር፡፡

61ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባው ተከላካይ ሳሙኤል የእጅ የወጣን ኳስ ለመወርወር በመዘግየቱ የእለቱ ዳኛ ሆን ብለህ ሰዓት ለመግደል ነው በሚል በሁለት ቢጫ ከሜዳ አስወግደውታል፡፡ ዳኛው ተጫዋቹን የቀይ ካርድ በሚሰጡበት ቅፅበት ዳኛውን በማነቅ ያሳየው ድርጊት የሁለቱም ክለብ ተጫዋቾች ሲያዋክቡበት የነበረበት ክስተት እጅግ አስነዋሪ ከመሆኑ ባለፈ ሊታረም የሚገባው መሆኑን መጠቆም እንወዳለን፡፡ በሌላ በኩል የሁለቱም ክለብ ተጫዋች ሆነው ከሽቦ አጥሩ ውጪ ያሉ ተጫዋቾች ጨዋታው እየተደረገ ባለበት ሰአት ሜዳ ውስጥ ካሉ ተጫዋቾች ጋር እና በዳኛ ላይ ሲያሳድሩ የነበረውም ጫና ፍፁም የጨዋታው ቅርፅ የቀየረ ድርጊት ነበር፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ሀምበሪቾዎች ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን ዳግም በቀለ እና ቢኒያም ጌታቸው በርካታ ጎል የሚሆኑ አጋጣሚዎችን አግኝተው መጠቀም ሳይቸችሉ ቀርተዋል፡፡ጨዋታውም በስተመጨረሻ በአዲስ አበባ ከተማ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የዕለቱ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ 4:00 ሲል ሀላባ ከተማን ከ ካፋ ቡና አገናኝቷል፡፡ የሀላባ ከተማ በዘጠና ደቂቃ ብልጫ የታየበት ነገር ግን ወደ ጎል የሚያደርጉት እንቅሴቃሴ ተዳክሞ የቀረበበት ነበር። በአንፃሩ የሀላባን የቅብብል ስህተት ብቻ ሲያገኙ ለመጠቀም የሚሞክሩት ካፋዎች አብዛኛውን ሰዓት ያገኙት ኳስ ከርቀት ብቻ ሲሞክሩ ውለዋል፡፡

ጥቂት ሙከራን ብቻ የተመለከትንበት እና አሁንም የሀላባን የሜዳ ላይ ብልጫን መመልከት በቻልንበት ሁለተኛ አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የጎል ድርቅ በተወሰነ ረገድ በአጋማሹ የተመለከትንበት ነበር፡፡ 52ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ግሩም ግብ አስቆጥሮ የአሰልጣኝ ደረጀ በላይን ቡድን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ መደበኛው ዘጠና ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሁለት ብቻ እየቀረው ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ አንድ ደቂቃ ያልሞላው ሰለሞን ብሩ በራሱ የግብ ክልል በሰለሞን ብሩ ላይ የሰራሁን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አረጋኸኝ ማሩ ወደ ጎልነት ለውጦት ካፋን 1 ለ 1 በማድረግ ጨዋታውም በዚህ ውጤት ተጠናቋል፡፡

10፡00 ላይ የምድቡ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በነቀምት ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ መካከል ተደርጎ በነቀምቴ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ብልጫን ወስዶ በታየበት እንዲሁም ረጃጅም ኳሶችን አማራጭ የጥቃት መነሻቸው ሲያደርጉ የተስተዋሉት ነቀምት ከተማዎች ወደ ኢብሳ በፍቃዱ እና ጉቱ መላኩ በሚጣሉ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል፡፡ ነቀምት ከተማ ብልጫን ወስደው ቢጫወቱም በመጀመሪያው አጋማሽ ጎል ሳንመለከት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከወትሮ ጠንካራ እንቅስቃሴያቸው ዛሬ ብልጫ ተወስዶባቸው የታዩት አቃቂዎች ኳስን በሚይዙበት ጊዜ ቶሎ ቶሎ መነጠቃቸው በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ጎል በነቀምቴ ተከታትሎ እንዲቆጠርባቸው ሆኗል፡፡ 73ኛው ደቂቃ እስራኤል ታደለ መሬት ለመሬት የላከለትን ቆንጆ ኳስ ፀጋአብ ብርሀኑ በቄንጠኛ እግሩ ጎል አስቆጥሮ ነቀምት መሪ አድርጓል፡፡ አሁንም በጨዋታው ተሽለው ሲያጠቁ የነበሩት ነቀምቴዎች በጭማሪ ደቂቃ በአብዲ ተሾመ አማካኝነት ግሩም ጎል አስቆጥረው ጨዋታው 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ተደምድሟል፡፡

ምድብ ሐ

ጠዋት 2:00 ላይ ኢትዮጵያ መድንን ከጌዴኦ ዲላ ያደረጉት ጨዋታ በመድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃ ከበደ አሰፋ ያስቆጠረው ጎል መድንን ወደ ድል እንዲመለስ አድርጎታል።

ቀጥሎ 04:00 ላይ ቂርቆስን የገጠመው አርባምንጭ ከተማ 3-1 አሸንፏል። ፍቃዱ መኮንን ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጠር አብነት ተሾመ አንዷን ጎል አስቆጥሯል። እስራኤል ሻጎሌ ደግሞ የቂርቆስን ጎል አስቆጥሯል።

የምድቡ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነገሌ አርሲን ከባቱ ከተማ ያገናኘው ሲሆን 1-1 ተጠናቋል። ሂሳ ሁሴን በ25′ ኛው ደቂቃ አርሲን ቀዳሚ ሲያደርግ ሚካኤል ዓለማየሁ ባቱን በ70ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ