የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የማክሰኞ ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አምስተኛ ሳምንት የምድብ ለ በሀዋሳ እና የምድብ ሐ በድሬዳዋ ቀጥለው ተደርገዋል፡፡

ምድብ ለ

ረፋድ 4፡00 ሲል ሻሸመኔ ከተማ እና ቤንች ማጂ ቡናን አገናኝቷል፡፡ ብርቱ ፉክክር ባስተዋልንበት መርሀ ግብር ለዕይታ ሳቢ የሆኑ የማጥቃት አካሄዶችን የተመለከትን ቢሆንም ከግብ ጋር ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ግን ቡድኖቹ ሲቸገሩ ነበር፡፡ ከእረፍት በፊት ሻሸመኔ ከተማዎች ከእረፍት መልስ ደግሞ ቤንች ማጂ ቡና ተሽለው የታዩበት አጋማሽ የነበረ ቢሆንም የጠሩ የጎል ዕድሎችን ከእንቅስቃሴ ውጪ መመልከት ሳንችል 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

10፡00 ጋሞ ጨንቻ እና ኢኮሥኮ የምድቡን የዕለቱ ሁለተኛ እና የሳምንቱን የመጨረሻ ጨዋታ ያደረጉ ክለቦች ነበሩ፡፡ ጋሞ ጨንቻዎች ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶችን በመጠቀም ወደ ቀኝ መስመር ባደላ መልኩ ጥቃት ሲሰነዝሩ የታዩ ሲሆን በአንፃሩ ኢኮሥኮዎች ኳስን ባደረገ የመሀል ሜዳ አጨዋወት ትግበራን ለመከተል ጥረት ቢያደርጉም ኳሶቻቸው የመጨረሻ ማረፊያቸው ለስኬት የበቁ አልሆነላቸውም በተለይ ኳስን በሚይዙበት ወቅት በተደጋጋሚ የሚቆራረጥ ወጥነት የጎደለው አካሄድን ስለሚከተሉ ለጋሞ ጨንቻ ፈጣን የረጃጅም ኳስ ጨዋታ አመቺ ሆኖላቸዋል፡፡ በዚህም ሂደት ተሳክቶላቸው 12ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ በኩል በተገኘ አጋጣሚ ያገኛትን ኳስ ዘላለም በየነ ወደ ጎልነት ለውጧት ጨንቻን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከጎሉ በኃላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ሲታይባቸው የነበሩት ጨንቻዎች በኢኮሥኮ በተወሰነ መልኩ ለትንሽ ደቂቃ ለመበለጥ ተገደዋል፡፡ ቤዛ መድህን ከቅጣት ምት አክርሮ መቶ የላይኛው የግቡ ብረት ከመለሰበት አራት ደቂቃዎች በኃላ ማለትም 25ኛው ደቂቃ ዳንኤል ከበደ ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ቤዛ መድህን አመቻችቶ ሰጥቶት ተጫዋቹም በግሩም አጨራረስ በማስቆጠር ኢኮሥኮን አቻ አድርጓል፡፡

ጨዋታው በዚህ ውጤት ቀጥሎ 40ኛ ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳ ላይ ኳስን ለመሻማት የሁለቱ ክለብ ተጫዋቾች በአየር ላይ በሚነሱበት ጊዜ የጋሞ ጨንቻው ለገሰ ዳዊት ጉዳት በጭንቅላቱ ላይ ጉዳች ደርሶበት ህክምና በፍጥነት በማግኘት በጤንነት ከሜዳ ተቀይሮ የወጣ ሲሆን የጋሞ ጨንቻው አሰልጣኝ ማቲዮስ ለማ ግን ሆን ተብሎ ነው የተመታው በሚል በዳኛው ውሳኔ ላይ የቴክኒክ ክስን አስይዘው ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ አሰልጣኙ በተወሰነ መልኩ ያሳዩት ስሜታዊነት ያልተገባ እና ሊታረም የሚገባው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ መግለፅ እንወዳለን።

የጨዋታው ሌላኛው አስገራሚ ጉዳይ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ተጫዋች ለመቀየር በተደጋጋሚ የመቀየሪያ ቦርዱን በሚያነሱበት ጊዜ የተሰባበረ በመሆኑ ሲቸገሩ የተመለከትን ሲሆን በአፋጣኝ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ የጋሞ ጨንቻ ረጃጅም ኳሶች ለኢኮሥኮዎች በተደጋጋሚ ስጋት ቢፈጥርም የግብ ጠባቂው አላዛር መርኔ ድንቅ ብቃት ግን ጎል እንዳይሆኑ አግዷቸዋል፡፡ኢኮሥኮዎችም የጋሞ ጨንቻን የስህተት ኳሶች ሲያገኙ በረጅሙ በየኃላሸት ሰለሞን አማካኝነት ጥቃት ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተደምድሟል፡፡

ምድብ ሐ

ጠንካራ ፉክክር ከጅምሩ እያስተናገደ በሚገኘው የምድብ ሐ ጠዋት 2:00 ላይ ደቡብ ፖሊስ ከካምባታ ሺንሺቾ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። ልዑል ኃይሉ እና ካሣሁን ገብረሚካኤል የደቡብ ፖሊስን ጎሎች ሲያስቆጥሩ ሞገስ ቱሜቻ እና ምንተስኖት ታምሬ የሺንሺቾ አስቆጣሪዎች ናቸው።

ቀጥሎ የተደረገው የስልጤ ወራቤ እና መሪው ኮልፌ ቀራኒዮ ጨዋታ አንድ አቻ ተደምድሟል። ወራቤ በተመስገን ዱባ ጎል ቀዳሚ ቢሆንም ብሩክ ሙሉጌታ በሁለተኛው አጋማሽ የኮልፌን የአቻነት ጎል አስቆጥሯል።

09:00 ላይ የካን የገጠመው ቡታጅራ ከተማ 2-0 በማሸነፍ ከመሪዎቹ ተርታ ተሰልፏል። ክንዴ አቡቹ በሁለቱም አጋማሾች ያስቆጠራቸው ጎሎች ለአሰልጣኝ ካሊድ መሐመድ ቡድን ሦስት ነጥቦች አስገኝተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ