የዐበይት ጉዳዮች የዚህ ሳምንት ጥንቅራችንን የምናገባድደው እንደተለመደው ሌሎች ትኩረት ያገኙ ጉዳዮችን በአራተኛው ክፍል በማንሳት ነው።
👉እንከን ያላጣው የቅድመ ጨዋታ ዝግጅት
በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እየተካሄደ የሚገኘው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር በየጨዋታ ሳምንቱ ጅማሮ የቅድመ ዝግጅት ክፍተቶች እየታዩበት ቀጥሏል። ከዚህ በፊት በነበሩት ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ዘግይቶ ስለተሰቀለው መረብ እና ከጨዋታ መጀመር ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ስለተሰመሩት የሜዳ ላይ መስመሮች አንስተን ነበር። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የመጫወቻ ኳሶችን የሚመለከት ክፍተት ተስተውሏል።
የቅድመ ጨዋታ ዝግጅት ወሳኝ አካል የሆኑት ኳሶች በሚፈለገው ብዛት እና የአየር መጠን ተሞልተው መዘጋጀት እንደሚገባቸው ይታወቃል። ታድያ ሲዳማ ቡና ከሰበታ ከተማ ባደረጉት የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ የጨዋታ ኳሶቹ በሚፈለገው የአየር መጠን ተዘጋጅተው ባለመቅረባቸው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሦስት ያክል አጋጣሚዎች ሲቋረጥ የጨዋታ ኳሶቹም በጨዋታው ወቅት እየተዞረ አየር የተሞሉበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነበር።
👉ተቀናቃኝ ትጥቅ አምራቾች በአንድ ክለብ መለያ
በሀገራችን እግርኳስ ያለው ደካማ የፕሮፌሽናሊዝም አስተሳሰብ በብዙ መልኩ ይገለፃል። አንደኛው መገለጫም ለጉዳዮች ያለን ቸልተኛነት አንዱ ሲሆን ይህም በእግርኳሱ ዙርያ ባሉ ፈርጀ ብዙ ጉዳዮች ላይ በጉልህ የሚስተዋል ነው። ለማሳያነትም ከሁለት ዓመት ወዲህ ኢትዮጵያ ቡና ከጣሊያኑ “ኤሪያ” ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈፀሙ ይታወሳል። በዚህም ቡድኑ በአሁኑ ወቅት እየተገለገለባቸው የሚገኙትን መለያዎች ፣ ቱታዎች እንዲሁም የልምምድ መስሪያ ቁሶችን ጨምሮ የተቋሙ ስም እና መለያ ያረፈባቸውን ቁሶች በመጠቀም ላይ ይገኛል።
በዚህ ሳምንት ቡድኑ በወላይታ ድቻ 2-1 በተረታበት ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ የኤሪያ ቀጥተኛ ተፎካካሪ የሆነውን ግዙፉ የጀርመን ትጥቅ አምራች ኩባንያ “አዲዳስ” ምርት የሆነ ትጥቅ ተጠቅሟል። በተመሳሳይ አሰልጣኙ ካሣዬ አራጌ የአዲዳስ መለያ በጉልህ ያረፈበትን ኮፍያን ለብሰው ተመልክተነዋል።
መሰል ክስተቶች በሀገራችን እግርኳስ የተለመደ ቢሆንም በዘመነ ሱፐር ስፖርት ግን ጨዋታዎች በሰሀራ በታች እና በመላው ዓለም በተለያዩ አማራጮች እንደመተላለፉ መሰል ችላ የሚባሉ ጉዳዮች መዘዝ ይዘው መምጣታቸው አይቀሬ ነው።
በቀጥታ ከዚህ ጉዳይ ጋር ባይገናኝም በፋሲል ከነማ በኩል ሁለተኛ መለያቸውን ጨምሮ እንዲሁም የቡድኑ አባላት የጃኮ ትጥቅ አቅራቢ ምርት የሆኑ የስፖርት ቲሸርቶችን በናይክ ጃኬት እና ቱታዎች ሲጠቀሙ የመስተዋላቸው ነገር የተለመደ ነው። ታድያ ከትጥቅ አቅራቢ ተቋማት በቀጥታ በሚደረጉ ስምምነቶች ከሚገኙ ትጥቆች ይልቅ በጨረታ በሀገር ውስጥ ትጥቅ ከሚያስመጡ ሱቆች አልያም በክለቡ የግዢ ሰዎች ከገበያ ትጥቆች ገዝቶ መጠቀም በተለመደበት የሀገራችን እግርኳስ ለመሰል ጥቃቅን ጉዳዮች ትኩረት መሰጠት መጀመር ይኖርበታል።
👉የሆሳዕና እና ሀዋሳ ኃይል ያመዘነበት ጨዋታ እና የዳኛው ዝምታ
በ9ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ሀዋሳ ከተማን ከሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው ጨዋታ በሜዳ ላይ ለመሸናነፍ ከተደረገ ፉክክር ይልቅ አካላዊ ፍትጊያዎች የበዙበት ነበር። በጨዋታውም በድምሩ በሁለቱ ቡድኖች በኩል በሱፐር ስፖርት እንደተመዘገበው ቁጥር ከሆነ 42 ያክል ጥፋቶችን የተመለከትንበት ነበር። እንቅስቃሴን ለማቋረጥ እና ኳስ ለመንጠቅ ከሚከወኑ ጥፋቶች በተጨማሪ እጅግ አደገኛ ጥፋቶች እንደመበርከታቸው የከፉ ጉዳቶች አለመኖራቸው በራሱ እንደ ዕድል የሚታይ ነው።
ታድያ ጨዋታውን የመሩት የመሀል ዳኛ ዮናስ ማርቆስ ይህን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ካርዶችን እንደ መሳሪያ ከመጠቀም ይልቅ ዝምታን መምረጣቸው አስገራሚ አድርጎታል።
👉የጎል ድርቅ የመታው ሳምንት
የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀደሙት ዓመታት አንፃር በግቦች የተንበሸበሸ አጀማመርን አድርጓል። በዚህም መነሻነት ያለ ግብ በአቻ የሚጠናቀቁ ጨዋታዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ ተስተውሏል።
ነገርግን ይህኛው የጨዋታ ሳምንት ከቀደሙት ሳምንታት በተለየ በንፅፅር በግብ ድርቅ የተመታ ሳምንት ነው የሚባል ነው። በዚህኛው ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ሲጠናቀቁ በተመሳይይ ሁለት ጨዋታዎች 1-0 በሆነ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ሦስት ግቦች ተስተናግበውባቸዋል።
ይህም በድምሩ በሳምንቱ የተቆጠሩት ግቦች ብዛት ስምንት እንዲሆን አስችሏል። ይህም በየሳምንቱ ከ10 በላይ ግቦችን ያስተናግድ የነበረው ሊጉ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ እጅግ ዝቅተኛ ግብ የተስተናገደበት ሳምንት እንዲሆን አድርጎታል።
👉ሊታረም የሚገባው የተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና አመራሮች አስተያየትን የማስተናገድ ድክመት
ደካማ የሆነውን እግርኳሳችንን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ልንጋፈጣቸው ይገባል። በዚህም ሒደት ውስጥ በሜዳ ላይ ካሉ ተዋንያን እስከ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ብሎም ሁሉም በእግርኳሱ ዙርያ የሚገኙ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። የዚህ ሂደት አንዱ አካል ደግሞ በእግርኳሱ ከተለመደው ከንቱ የመሞጋገስ አስተሳሰብ ወጥተን ባሉት ችግሮች ዙርያ የጋራ መግባባት በመፍጠር ለተግባራዊ ለውጥ መንቀሳቀስ ይገባል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በእግርኳሱ ዙርያ ያሉ አካላት ከየትኛውም አካል የሚሰጥ አዎንታዊ ሆነ አሉታዊ አስተያቶችን በቀና መንፈስ የሚያስተናግድ ሰፊ ትከሻን መላበስ ይጠበቅባቸዋል።
ነገርግን ከዚህ ይልቅ የሚሰነዘሩ ሀሳቦች የተወሰነን አካል ለማጥቃት ፣ ጫና ውስጥ ለመክተት ታሳቢ ተደርገው እንደሚቀርቡ በማሰብ ሀሳብ የሚሰነዘርባቸው ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እና አመራሮች እነዚህን አስተያየቶችን በአዎንታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነው በመመልከት ቅሬታን ብሎም ተቃውሞን ሲያስነሱ ይስተዋላል።
ተቃውሞዎቹ ብሎም ቅሬታዎቹ በራሳቸው ችግር ባይኖራቸውም እነሱን ተከትሎ የሚመጡት ድርጊቶች ግን ለአላስፈላጊ ሁኔታዎች ሲዳርጉ ይስተዋላል። በመሆኑም ከጨዋታ ሳምንታት መጠናቀቅ በኃላ በዓብይት ጉዳዮች የሚቀርቡ ፅሁፉች ዋነኛ አላማቸው ውድድሩን የተሻለ ለማድረግ ተቀዳሚ አለማ ሲሆን በሂደቱ ውስጥ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እና የክለብ አመራሮችን በተሻለ መጠን የተሻለ እና ተራማጅ እንዲሆኑ የማድረግ እንጂ የትኛውንም አካል ለማጥቃት ብሎም ጫና ውስጥ ለመክተት አላማ ያደረጉ አለመሆናቸው ሊታወቁ ይገባል።
© ሶከር ኢትዮጵያ