ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በዘጠነኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ተመርኩዘን የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተናል።

👉 ለፈተናዎቹ ምላሽ እየሰጠ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ያደረጋቸውን የሊጉን መክፈቻ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከተ ዘንድሮ በሊጉ ስለመቆየቱ ጥርጣሬ ቢገባው አይገርምም፡፡ ቡድኑ ተከታታይ ሽንፈቶች ማስተናገዱ ብቻ ሳይሆን ተጋጣሚዎቹ ሰበታ እና ጊዮርጊስ በድምሩ ሰባት ጎሎች ያስቆጠሩብት መሆኑ እንዲሁም በጨዋታዎቹ የተወሰደበት ከፍተኛ ብልጫ ቀጣይ ጉዞው ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነበር፡፡ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ይህ ነው የሚባል የተደራጀ አጨዋወት ያልነበረው ይህ ቡድን አሁን ላይ ስንመለከተው እያስመዘገበ ያለው ውጤት እና የቡድን አወቃቀሩ ከመጀመሪያው ጋር ፈፅሞ የማይገናኝ ሆኗል፡፡

ከሁለቱ ሽንፈቶች በኋላ ስድስት ጨዋታዎች ያደረገው ሀዋሳ ምንም ሽንፈት ያለገጠመው ሲሆን መረቡ የተደፈረው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት ከቀዳሚዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በግማሽ ያነሰ ቁጥር ነው፡፡ ቡድኑ ራሱን መልሶ ባገኘባቸው እነዚህ ጨዋታዎች ተለዋዋች አቀራረብ ይዞ በመግባት በተጋጣሚቹ ላይ ከፍተኛ ብልጫን ሲያስመዘግብ ሲታይ ‘ውድድሩ ሲጀምር ምን ነክቶት ነበር ?’ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከተጋጣሚዎቹ ውስጥ ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና የሚገኙ መሆኑ ደግሞ ተጋጣሚዎቹ ከነበሩበት ጥሩ አቋም በዘለለ የተለያየ ባህሪ ባላቸው ቡድኖች መፈተኑንም ያሳያል። ኳስን መሰረት አድርጎ ከሚጫወት ፣ በፈጣን ሽግግር ጎል ጋር ከሚደርስ እና ኃይል የቀላቀለ አቀራረብ ካላቸው ቡድኖች ጋር ተገናኝቶም ሀዋሳ እጅ አልሰጠም።

ከባዱ ጊዜ ያለፈ ቢሆንም ሁለት የተለያየ መልክ ያለው የሀዋሰ የእስካሁኑ ጉዞ በቡድን አባላቱ ላይ ቁጭትን የሚፈጥር ይመስላል፡፡ ከሁለቱ ሽንፈቶቹ በተጨማሪ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ ከጣለበት ጨዋታ ሌሎች ነጥቦችን ማግኘት ችሎ ቢሆን ኖሮ አሁን ካለበት ደረጃም ከፍ ብሎ ከዋናዎቹ ተፎካካሪዎች ውስጥ በተካተተ ነበር፡፡ ያም ቢሆን የቡድኑ ተጫዋቾች በራሳቸው ላይ ያሳደሩት ዕምነት እና ተፎካካሪ መሆን እንደሚችሉ ገብቷቸው በሜዳ ላይ እየተንቀሳቀሱ ያሉበት መንገድ በደካማ ጉዞ ላይ ላሉ ሌሎች ቡድኖችም ትምህርት የሚሆን ነው።

👉 ሲዳማ ቡና “አሸንፏል”

በ7ኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን አሸንፎ ከአስከፊ አጀማመሩ የነቃ የመሰለው ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በከተማ ተቀናቃኙ ሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ያገገመበትን ድል በዚህኛው ሳምንት ሰበታ ከተማ ላይ አስመዝግቧል። በጨዋታው ጎል ሊሆኑ የተቃረቡ መከራዎች ሳይቆጠሩበት በድል መወጣቱም አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ “እድለኞች ነበርን” እንዲሁ ያስባለ ነበር።

በጨዋታው ሲዳማ ቡና በተጋጣሚያቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ቀጥተኝነትን ከመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጋር ቀይጠው የተጫወቱት ሲዳማ ቡናዎች በ59ኛው ደቂቃ ግዙፉ ማሊያዊ አጥቂ የሰበታው የመሀል ተከላካይ ወደ ግብ ጠባቂው ለመስጠት አስቦ ከመንገድ የቀረችውን ኳስ ተጠቅሞ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።

ሲዳማዎች ተጨማሪ ግቦችን ሊያገኙባቸው የሚችሉ አስደናቂ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን መጠቀም ባለመቻላቸው በተለይ በመጨረሻው 20 ደቂቃዎች በሰበታ ከተማዎች ከፍተኛ ጫና ስር ለመውደቅ ተገደዋል። በዚህም ምስጋና ለግብጠባቂያቸው መሳይ አያኖ ይግባና የፍፁም ገ/ማርያም የፍፁም ቅጣት ምትን ጨምሮ ሌሎች የግብ ሙከራዎችን በማምከን ቡድኑን ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ አስችሏል።

በውድድር ዘመኑ እስካሁን የዚህኛውን ሳምንት ውጤት ጨምሮ ሦስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ከተከታታይ ድሎች ከራቁ ሰንበትበት ብለዋል። ከሁለቱ ድሎች ማግስት ሽንፈትን ያስተናገደው ቡድኑ በሦስተኛው ድል ማግስት አዎንታዊውን ውጤት የማስቀጠል ጠንካራ ፈተና በቀጣይ ይገጥማቸዋል።

👉ለማሸነፍ ተቃርቦ የነበረው ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ተጋርቷል

ተለዋዋጭነት መገለጫው እየሆነ የመጣው ባህር ዳር ከተማ በ9ኛ ሳምንት ከሰሞነኛ አቀራረቡ በተለየ ጥንቃቄን ጨምሮ በቀረበበት ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።

ባህር ዳር ከተማዎች በዘጠና ደቂቃ የጨዋታ እንቅስቃሴ የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቂያ አማራጮችን በሙሉ በመቆጣጠር ረገድ እጅግ ውጤታማ ቀንን አሳልፈዋል። ነገርግን ወደ ማጥቃት ያደረጓቸው የነበሩት ሽግግሮች ፈጣን ያለመሆናቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። ነገርግን በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ አወዛጋቢ በሆነ መልኩ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምንይሉ ወንድሙ መጠቀም ሳይችል ቀረ እንጂ ጨዋታውንም አሸንፈው ለመውጣት ቀርበው ነበር።

👉 “ዕድል ፊቱን ያዞረበት” ሰበታ ከተማ

ካለፈው ሳምንት ወዲህ የማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ የተሻለ መነቃቃት ያሳየው ሰበታ ከተማ በዚህ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር በተደረገው ጨዋታ በርካታ የጎል እድሎችን ብሎም የፍፁም ቅጣት ምትን ቢያገኝም መጠቀም ሳይችል 1-0 ተሸንፎ ወጥቷል። ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ነጥቦች ይዞ ሊወጣ የሚችልበት እድሎችን የጎል አጋጣሚዎች በማምከን፣ በቀይ ካርድ ምክንያት በጎዶሎ ቁጥር በመጫወት እንዲሁም በዳኝነት ስህተቶች ምክንያት አለመጠቀሙ አድለኛ ያልሆነው ክለብ ያስብለዋል።

ከደሞዝ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የቡድን ትኩረቱ የተበታተነው ቡድኑ ኳስ ለመቆጣጠር ባይቸገርም ወደ ማጥቃት ወረዳው መድረስ ላይ እንዲሁም የጠሩ የጎል እድሎችን መፍጠር ላይ ችግር እንዳለበት በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። በዚህ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎች ማድረጋቸው ግን ለቀጣይ ጨዋታዎች ተስፋ የሚሰጥ ነው። 

እድሎችን ወደ ጎልነት የመጨረስ ብቃት ማሻሻል እና በተጫዋቾች ስሜታዊነት በሚታዩ የቀይ ካርዶችን ማስወገድ በቀጣይ የአብርሀም መብራቱ ቡድን የሚጠብቀው የቤት ሥራ ነው።

👉ወላይታ ድቻ ከስድስት የጨዋታ ሳምንት በኃላ ድል አድርጓል

በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ባህርዳር ከተማን ከረቱ ወዲህ ማሸነፍ ተስኗቸው የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው ዘላለም ሽፈራው እየተመሩ ባደረጉት ሁለተኛ ጨዋታቸው ኢትዮጵያ ቡናን ከአስደናቂ የቡድን እንቅስቃሴ ጋር ከመመራት ተነስተው 2-1 በማሸነፍ ከድል ጋር ታርቀዋል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ወደ አሰልጣኝነት መንበሩ ካመጡ ወዲህ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ከጠንካራው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረገው ቡድኑ በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ የበላይነት ቢወሰድባቸውም በሁለት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ያገኟቸውን እድሎች በአግባቡ ተጠቅመው ከጨዋታው ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሌላኛው የመዲናዋ ጠንካራ ክለብ ከሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጥሩ መልኩ ተከላክለው ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው ለማግኘት ተቃርበው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ የነበራቸውን የመከላከል ጥንካሬ አስቀጥለው በዚህኛው ሳምንት ደግሞ የመልሶ ማጥቃት ስልነትን ጨምረው በመቅረብ አሸንፈው ለመውጣት ችለዋል።

👉ፋሲል ከነማ በመሪነቱ ቀጥሏል

ሊጉን ከአናት ሆነው በመምራት ላይ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ከፍተኛ ፈተና ቢገጥማቸውም በ82ኛው ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ከፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን ያስቀጠሉበትን ድል አስመዝግበዋል።

ሱራፌል ዳኛቸውን በተጠባባቂ ወንበር አስቀምጠው ወልቂጤ ከተማን የገጠሙት ፋሲል ከነማዎች የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ብቻ የተገደበው የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ በመግታት ወደ መሀል ከተጠጋው የወልቂጤ ከተማ ተከላካዮች ጀርባ በርከት ያሉ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ፋሲል ከተማዎች የወልቂጤውን ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰውን ለማለፍ ተቸግረው ቢቆዩም በ82ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብ ሲልክ በኃይሉ ተሻገር በእጅ በመንካቱ የተሰጣቸውን የፍፁም ቅጣት ምትን ልማደኛው አጥቂ ሙጂብ ቃሲም አስቆጥሮ ቡድኑን ሊጉን እየመራ እንዲዘልቅ አስችሏል።

በአስረኛው ሳምንት አራፊ የሆነው ቡድን ሌሎቹ የሚያስመዘግቡት ውጤት በመሪነቱ ላይ ለውጥ የማይፈጥር በመሆኑ ዘና ባለ መንፈስ ቀጣይ ተጋጣሚዎቹን የመገምገም እና ለተጫዋቾቹ እረፍት የመስጠት ጥሩ አጋጣሚን አግኝቷል።

👉 ድሬዳዋ ከተማ ከጫና የተላቀቀበትን ድል አስመዝግቧል

ተከታታይ ጨዋታዎችን ሽንፈት በማስተናገድ ጫና ውስጥ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘውን አዳማ ከተማን 3-0 በመርታት ለጊዜውም ቢሆን ከጫና ተንፈስ ያሉበት እና አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን “ከማጥ ውስጥ መውጣት” ያሉትን ድል አስመዝግበዋል።

ከሰሞነኛ ደካማ እንቅስቃሴያቸው አንፃር እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በደካማው አዳማ ከተማ ላይ ከፍ ያለ ጫናን ማሳደር ችለዋል። ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን አጥቂዎቻቸው መጠቀም ሳይችሉ ቀሩ እንጂ ጨዋታውን በሰፊ የጎል ልዩነት ባሸነፉ ነበር።

ሙኽዲን ሙሳ ሁለት እንዲሁም አስቻለው ግርማ ባስቆጠሯቸው ግቦች 3-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች ለቀጣይ ጨዋታ መነሳሻ የሚሆናቸውን ተስፋ ሰጪን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ማሳየት ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ