ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ9ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የግቦች ቁጥር እና የተጨዋቾች የግል ብቃት ከወትሮው በተለየ መልኩ ቀንሶ ቢታይም ከጥቂት አማራጮች ውስጥ ለሳምንቱ ምርጥነት ይመጥናሉ ያልናቸውን ተጫዋቾች አካተን ተከታዩን ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ: 4-3-3

ግብ ጠባቂ

መሳይ አያኖ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና ሰበታን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ውጤቱን ለማስጠበቅ የመሳይ ልዩ ብቃት አስፈልጎት ነበር። መሳይ የፍፁም ገብረማርያምን ፍፁም ቅጣት ምት ከማዳኑ በተጨማሪ ዱሬሳ ሹቢሳ ሰበታን አቻ ሊያደርግ የተቃረበባትን ከባድ የቅርብ ርቀት ኳስ እና የፍፁምን በሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራን በመመለስ ቡድኑን ታድጓል።

ተከላካዮች

ሱሌይማን ሀሚድ – ሀዲያ ሆሳዕና

የወትሮው የማጥቃት ተሳትፎው እምብዛም ቢሆንም ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት ለመላክ ይሞክር የነበረው ሱሌይማን በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ጨዋታ አሳልፋል። የሀዋሳ ከተማ አስፈሪ ጎን የሆነው የመስመር ጥቃት ፍሬ እንዳያፈራ ጥንቃቄ ላይ ያተኮረው የቡድኑን ዕቅድ በአግባቡ መተግበር ችሏል።

አንተነህ ጉግሳ – ወላይታ ድቻ

ከማዕዘን በተነሳ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረው የመሀል ተከላካዩ የግብ ክልሉን ከጥቃት በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ጊዜ አሳልፏል። የኳስ ንክኪ በሚበዛው የተጋጣሚው አጨዋወት ውስጥ የመጨረሻ ቅብብሎችን በማቋረጥ እና የቡድኑ መነሳሳት አካል በነበረ ትጋት እስከመጨረሻው በመዝለቅ ድቻ የተጠማውን ድል እንዲያገኝ አግዟል።

ምኞት ደበበ – ሀዋሳ ከተማ

ብዙ ትግል ይጠይቅ በነበረው ጨዋታ ግዙፎቹን የሀዲያ ሆሳዕና አጥቂዎች በመቆጣጠሩ ረገድ ምኞት የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። ከላውረንስ ላርቴ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠርም የአየር ላይ ኳሶችን በመከላከል እና አደጋ የሚፈጥሩ ጥቃቶችን አቋርጦ በማራቅ ቡድኑ አንድ ነጥብ እንዲያገኝ ማድረግ ችሏል።

አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ወልቂጤ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ እንደወትሮው መዳረሻቸውን ወደ ሳጥን ውስጥ ያደረጉ ቀጥተኛ ሩጫዎችን በማድረግ ከፍ ያለ የማጥቃት ተሳትፎ የነበረው አምሳሉ ቡድኑ ካደረጋቸው አደገኛ ሙከራዎች ውስጥ አንድ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን ሲያስጀምር ሱራፌል ዳኛቸው ሞክሮት በግቡ ቋሚ የተመለሰውን ያለቀለት የግብ ዕድል መፍጠርም ችሎ ነበር።

አማካዮች

ሀብታሙ ተከስተ – ፋሲል ከነማ

በወጥነት ቡድን እያገለገለ የሚገኘው ቀጭኑ ጠንቃቃ አማካይ ከይሁን እንዳሻው ጋር በፈጠረው ጥምረት ጥሩ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል። ለኳስ ቁጥጥር የተመቹ የወገብ በላይ ተሰላፊዎችን የያዘው ተጋጣሚው የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ እንዲታፈን የሀብታሙ ሚና ከፍ ያለ ነበር።

ኤፍሬም ዘካሪያስ – ሀዋሳ ከተማ

እጅግ ፍትጊያ በበዛበት የሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ለተጋጣሚው ኃይል የቀላቀለ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ኤፍሬም በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ ሰጥቷል። የቡድኑን ብቸኛ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ የቻለው ኤፍሬም በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ ሀዋሳ ወደ ፊት ሊሄድ የሚችልባቸውን ቀዳዳዎች በመፈለግ ብዙ ለፍቷል።

ሱራፌል ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ

የቡድኑ ዋነኛ የጥቃት መነሻ የሆነው ኤልያስ ማሞን ሚና ይዞ የገባው ሱራፌል በጨዋታው በነበረው እንቅስቃሴ ለድሬዳዋ ሌላ ገፅታ አላብሶታል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ትኩረቱን ያደረገ ቀጥተኛ ጥቃትን በማስጀመር ቡድኑ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ አብዛኛው ደቅቃዎች በአዳማ ሜዳ ላይ እንዲያሳልፍ አግዟል።

አጥቂዎች

ጁኒያስ ናንጄቦ – ድሬዳዋ ከተማ

ከተከላካዮች አምልጦ በፍጥነት ወደ ሳጥን ውስጥ መግባት የሚያውቅበት ናሚቢያዊው አጥቂ ያገኛቸውን ዕድሎች ወደ ጎልነት መቀየር ባይችልም የቡድኑ ጥቃቶች ላይ ሁሉ ተሳታፊ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ለሙኸዲን ሙሳ የመጀመሪያ ጎል እና አስቻለው ግርማ ላስቆጠረው ጎል ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ፀጋዬ ብርሀኑ – ወላይታ ድቻ

የጨዋታውን የመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ አድርጎ የነበረው ፀጋዬ የኃላ ኋላ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ወላይታ ድቻን ከድል ጋር አስታርቋል። ተጨዋቹ የነበረውን ከፍተኛ ተነሳሽነት ከምንም ተነስቶ ያስቆጠራት እና ቡድኑን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ወሳኝ የነበረችውን የመጀመሪያ ግቡን ያስቆጠረበትን መንገድ መመልከት በቂ ነው።

ሙኸዲን ሙሳ – ድሬዳዋ ከተማ

በቁመቱ አጠር የሚለው የድሬዳዋው አጥቂ በሦስት የውጪ ሀገር አጥቂዎች መሀል ሆኖም መድመቁን ቀጥሏል። በአዳማው ጨዋታ ናንጄቦ ዕድሎችን ሲያባክን ቢታይም በተቃራኒው ሙኸዲን ሙሳ በሁለት የተለያየዩ መንገዶች ድንቅ ጨራሽነቱን ያሳዩ ግቦችን በማስቆጠር በድኑን በመጀመሪያው አጋማሽ ብቻ የ 2-0 መሪ ማድረግ ችሏል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኃላ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አደጋ ውስጥ የነበረው ቡድን ላይ ነፍስ ዘርተውበታል። ከጨዋታው በኃላ እንደሰጡት አስተያየት እና በጨዋታው ላይም በግልፅ እንደታየው ሳምንት ጊዮርጊስን ከገጠመው ቡድን አቀራረብ በተለየ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ቡና ተዘጋጅተው በመምጣት ያልተገመተ የጨዋታ ዕቅድ ይዘው ገብተዋል። ካደረጓቸው ውጤታማ ቅያሬዎች ጋርም ቡድኑ ከስድስት ጨዋታዎች በኃላ የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን እንዲያሳካ አድርገዋል።

ተጠባባቂዎች

ምንተስኖት አሎ – ሰበታ ከተማ
ቶማስ ስምረቱ – ወልቂጤ ከተማ
አይዛክ ኢሲንዴ – ሀዲያ ሆሳዕና
እንድሪስ ሰዒድ – ወላይታ ድቻ
ዱሬሳ ሹቢሳ – ሰበታ ከተማ
አንዳለ ከበደ – ድሬዳዋ ከተማ
ቢኒያም ፍቅሬ – ወላይታ ድቻ


© ሶከር ኢትዮጵያ