የሳምንቱ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የትኩረት ነጥቦች

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2013 የውድድር ዓመት የአምስተኛ እና ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፉት ቀናት ሲካሄዱ ቆይተዋል። በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸውን ጉዳዮችም እንዲህ አሰናድተንላችኋል።

👉ወልዲያ የመጀመርያ ድል አሳክቷል

በወሎ ኮምቦልቻ ፣ መከላከያ ፣ ገላን ከተማ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን ተከታታይ ሽንፈቶች ደርሰውበት ያለውጤት የቆየው ወልዲያ በዚህ ሳምንት የመጀመሪያ ሦስት ነጥቦችን ማሳካት ችሏል። በ2010 የውድድር ዓመት ከሊጉ የወረደው ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ የዘንድሮ አጀማመሩ ስጋት ላይ የሚጥል ዓይነት ነበር። ትናንት ለገጣፎ ለገዳዲን በገጠመበት ጨዋታም በመጀመሪያው አጋማሽ ለመመራት ተገዶ የነበረ ቢሆንም ከኃላ ተነስቶ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ከኃላ ተነስቶ ማሸነፍ ችሏል። በአሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ እየተመራ የሚገኘው ወልዲያ በሄኖክ አቻምየለህ እና ፍፁም ደስይበለው ጎሎች ከመመራት ተነስቶ ከድል ጋር መገናኘቱ በቀጣይ ጉዞውም ለማንሰራራት እንደሚረዳው ይጠበቃል።

👉”ወደታች ያደገው” ለገጣፎ ለገዳዲ

ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ብርቱ ፉክክር ከሚያደርጉ ቡድኖች ተርታ የነበረው ለገጣፎ ለገዳዲ የቀደመ ተፎካካሪነቱን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለማስቀጠል ተቸግሮ እየተመለከትን እንገናኛለን።

በተሰረዘው የውድድር ዘመን እስኪቋረጥ ድረስ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚደረገውን ጉዞ በምድብ ሀ እየመሩ የነበሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ዘንድሮ ግን ከ5 ጨዋታዎች በኋላ በ2 ነጥብ እና በአራት የግብ ዕዳ በምድብ ሀ ግርጌ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አስደንጋጭ የቁልቁለት ጉዞ በስተጀርባ በርካታ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንደምክንያትነት እየቀረቡ ይገኛሉ። ክለቡን በበላይነት በሚመሩት አካላት ትኩረት የተነፈገው ነው በሚል የተሰላቹ የሚመስሉት የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙም በዚህኛው ሳምንት ቡድኑ ያደረገውን ጨዋታ በአካል ተገኝተው እስካለመምራት ደርሰዋል።

ከአሰልጣኙ አለመገኘት በስተጀርባ ቡድኑ ሊያሟላ የሚገባቸው መሰረታዊ ነገሮች መሞላት ባለመቻላቸው ለማስልጠን መቸገራቸው እና በዚህ መነሻነት የቡድኑ አባላት ከሚገኙበት ከፍተኛ የሞራል ስብራት አንፃር ለመስራት አለመቻላቸው ተሰምቷል። ይህን ጉዳይ ለመቅረፍ በክለቡ ስራ አስኪያጅ እና ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የተጀመረው ጥረት ፍሬ ባያፈራም ቡድኑ ግን በቀደመው ተፎካካሪነት እንዲቀጥል ከታሰበ የክለቡ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ አስፈላጊ ርብርብ ሊያደርጉ ግድ ይላል።

👉የአዲስ አበባ ከተማ እና የኮልፊ ቀራኒዮ መልካም አጀማመር

በአሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር የሚመራው አዲስ አበባ ከሌሎች ቡድኖች እጅጉን ዘግይቶ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ቢገባም በተቃራኒው ግምቶችን አፋልሶ መልካም የሚባልን የውድድር ዘመን ጅማሮ እያደረገ ይገኛል። ከጥቂት ወራት በፊት ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘ የክለቡ ህልውና አደጋ ውስጥ የገባ ቢመስልም ቡድኑ ግን በሜዳ ላይ እያስመዘገበ የሚገኘው ውጤት ከነበረበት ስጋት ተላቆ በብዙዎች ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገ ነው። አዲስ አባባ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥብ አስራ ሦስቱን አሳክቶ ‘ምድብ ለ’ን በመምራት ላይ ይገኛል።

በተመሳሳይ ሌላኛው የርዕሰ መዲናይቷ ክለብ የሆነው እና ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአንደኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደረገው ኮልፌ ቀራንዮ በ2013 የከፍተኛ ሊግ ውድድር አስደናቂ አጀማመርን እያደረገ ይገኛል። በአሰልጣኝ መሀመድ ኑር የሚመሩት ኮልፌዎች በዘንድሮው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ክስተት መሆናቸውን እያስመሰከሩ ናቸው። በአነስተኛ በጀት ከፍ ባለ የመጫወት ፍላጎት ባላቸው ወጣት ተጫዋቾች እና ልምድ ባላቸውም ጭምር የተገነባው ቡድኑ በ11 ነጥቦች ‘ምድብ ሐ’ን እየመራ ይገኛል።

👉የደጋፊዎች በቁጥር በርክቶ መገኘት

እንደሚታወቀው በሀገሪቱ እየተደረጉ የሚገኙ ውድድሮች በኮቪድ ፕሮቶኮል ስር እየተከናወኑ ይገኛሉ። በመሆኑም በጨዋታዎች ላይ የሚታደሙ አካላት ቁጥር ተገድቦ ውድድሮች እንደቀጠሉ ናቸው። ነገር ግን በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ተሳታፊ ክለቦች በኩል እየተሰማ ያለው ቅሬታ ከዚህ የተለየ ነው። በምድቡ በሚደረጉ ጨዋታዎች ደጋፊዎች ከፍ ባለ ቁጥር በውድድሩ ቦታ ላይ እየተገኙ መሆኑ ስጋት እንዳሳደረባቸው የገለፁት ተሳታፊ ክለቦች አወዳዳሪው አካል ለጉዳዩ መፍትሄ እንዲሰጥ እየወተወቱ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታ በአግባቡ ትኩረት ካልተሰጠው የጤና ጥበቃ ሚኒስተርን ትኩረት ሊስብ እና ውድድሮችን እስከማቃረጥ ሊያደረስ ከመቻሉ በላይ በውድድሩ ላይ የሚገኘውን የእግር ኳስ ቤተሰብ ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ በፍጥነት መፍትሄ ያስፈልገዋል።

👉የመጫወቻ ኳሶች ጉዳይ

የጨዋታ ቀን ዝግጅቶች ጉደለት በብዛት የሚታይበት ከፍተኛ ሊጉ አሁንም ችግሮች አላጡትም። ለውድድሩ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ከአወዳዳሪው አካል የሚጠበቁ ቢሆንም ለጨዋታዎች ዋነኛ ግብዓት የሆኑት የመጫወቻ ኳሶች ነገር ችላ የተባለ ይመስላል። በምድብ ሐ በዚህ ሳምንት በጨዋታዎች ላይ የነበረው የመጫወቻ ኳሶች አቅርቦት ጥራት የሌላቸው ሆነው በመገኘታቸው ክለቦች በራሳቸው ኳስ ለመጠቀም ተገደዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ