ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ በድል ዙሩን ቋጭቷል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የዘጠነኛ ሳምንት መርሀ ግብር የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ 10:00 ላይ ተካሂዶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 ረቷል፡፡

የኢትዮ ኤሌክትሪክ የቡድን አጨዋወት የተስተዋለበት እና አዳማ ከተማዎች በአንፃሩ ግላዊ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሲተገብሩ በታየበት ጨዋታ አዳማ ከተማዎች የምስራች ላቀው እና ምርቃት ፈለቀ በግል ከሚያደርጉት አልፎ አልፎ ሙከራ ውጪ ፈታኝ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ሆነ ሙከራዎችን ማድረግ ያልቻሉበት፤ ያገኟቸውንም መልካም ዕድሎች በቀላሉ ሲያመክኑ የታየበት የዘጠና ደቂቃ የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የምስራች ላቀው ከርቀት ባደረገችው ሙከራ ወደ ግብ በመድረስ አዳማ ከተማዎች ቀዳሚ የነበሩ ቢሆንም በቡድን ውህደት በሚገባ የተቀናጁት ኤሌክትሪኮች ኳስን ሲያገኙ በቀላሉ ለስህተት ተጋላጭ የነበረውን የአዳማን የተከላካይ ክፍል በተደጋጋሚ ለማለፍ ጥረዋል፡፡

ከምንትዋብ ዮሐንስ እና ዮርዳኖስ ምዑዝ ተደጋጋሚ ጥረቶች በኃላ 27ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ አስገራሚ ጎል አስቆጥረዋል፡፡ ከመስመር ተከላካይነት ወደ መሀል ሜዳ ክፍል ተቀይራ መጫወት ከጀመረች ወዲህ እጅግ ድንቅ አቋም እያሳየች የምትገኘው እፀገነት ብዙነህ ከማዕዘን ምት በቀጥታ መታ በማስቆጠር ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ከዚህች ጎል በኃላ በመልሶ ማጥቃት ፈጣን የአጨዋወት መንገድ ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል በምርቃት ፈለቀ አማካኝነት መድረስ የቻሉት አዳማዎች አጥቂዋ በረጅሙ የተሰጣትን ኳስ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ወደ ሳጥን እየገፋች ገብታ ተጫዋቾችን ጭምር በማለፍ በቀጥታ ከግብ ጠባቂዋ ትዕግስት ጋር ተገናኝታ ብትመታውም ትዕግስት አበራ በሚገርም ብቃት አድናባት አጋማሹ ተገባዷል፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በተለየ መልኩ ከቆሙ ኳሶች አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የጣሩ ሲሆን አዳማ ከተማዎች በየምስራች ላቀው እና አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ግላዊ እንቅስቃሴ ላይ በምታተኩረው ምርቃት ፈለቀ ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት አማራጭን ሲከተሉ ተመልክተናል። ከቅጣት ምት የምስራች ላቀው አክርራ መታ ትዕግስት ያዳነችባት፣ ሰርካለም ጉታ በክፍት የጨዋታ መንገድ ያገኘችውን ነፃ ኳስ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

52ኛው ደቂቃ ምንትዋብ ከመስመር መሬት ለመሬት ስታሻግር ዮርዳኖስ ምዑዝ ጋር ደርሶ ተጫዋቿ ነፃ ለነበረችው ሳራ ነብሶ አሳልፋላት ተጫዋቿም በቀላሉ ወደ ጎልነት ለውጣው የኤሌክትሪክን የግብ መጠን ከፍ አድርጋለች፡፡በቀሩት ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በኤሌክትሪክ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ሳራ ነብሶን ከኤሌክትሪክ የጨዋታው ምርጥ ብሎ ሸልሟታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ