በዳኞቹ ላይ የተወሰነው ውሳኔ የደብዳቤ ለውጥ ተደረገበት

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ባህር ዳር ከተማ እና ሰበታ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ላይ ግድፈት ፈፅመዋል በተባሉት ዳኞች ላይ የተወሰነው ደብዳቤ ለውጥ ተደረገበት።

ሰበታ ከተማ ከባህር ዳር ጋር በነበረው ጨዋታ በዳኞች የደረሰበትን በደል ተንተርሶ አቤቱታ ማቅረቡን ተከትሎ ጉዳዩን የመረመረው የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ሥነ ስርአት ኮሚቴ ጨዋታውን በመሩት ሁለቱ ረዳት ዳኞች አሸብር ታፈሰ እና ባደታ ገብሬ ላይ የስድስት ወራት የእግድ ውሳኔ ማስተላለፉ እና ዳኞቹ ከሆቴል እንዲወጡ መደረጉ ሲነገር ቆይቷል።

ሆኖም የተወሰነውን ውሳኔ ዳኞቹ የሰሙት ከሚዲያ እንደ ሆነና ምንም መረጃ እንዳልነበራቸው እንዲሁም ከሆቴል እንዲወጡ ተደርጓል ተብሎ የተሰራጨው ዘገባ ስነ ልቦናቸውን የጎዳ መሆኑን በተጨማሪም ውሳኔም ካለ ከሚያስተዳድራቸው የዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ውሳኔውን የሚገልፅ ደብዳቤ ሊደርሳቸው ሲገባ በሊግ ካምፓኒው የወጣ ደብዳቤ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም የዳኞቹ ቅሬታ ተገቢ መሆኑን ከግምት አስገብቶ የደብዳቤ ለውጥ በማድረግ በዛሬው ዕለት በዋና ፀሐፊው አቶ ባህሩ የተፈረመ አዲስ ደብዳቤ ለዳኞቹ መስጠቱን ለማወቅ ችለናል። ዳኞቹም ውሳኔ ከተወሰነባቸው ጥር 14 ቀን ጀምሮ እስከ ትናንትናው ዕለት ድረስ በጅማ ሴይፍ ሆቴል እንደነበሩ ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ