ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ በ100% ድል የመጀመርያውን ዙር አጠናቀቀ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ዘጠነኛ ሳምንት ንግድ ባንክ አዲስ አበባ ከተማን 5 ለ 1 በመርታት ዙሩን በመሪነት ቋጭቷል፡፡

10፡00 የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ መካከል ሲደረግ ጨዋታውን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር ምክትል ኮሚሽነር፣ አቶ ዱቤ ጅሎ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባሎች ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ እና አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ በስታዲየሙ በመገኘት ታድመውታል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ንግድ ባንኮች በአዲስ አበባ ሲፈተኑ የታዩ ሲሆን ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ግን ወደ ጨዋታ ሲስተም በመግባት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ከቀኝ አቅጣጫ አረጋሽ ወደ ጎል አክርራ መታ ገና በ6ኛው ደቂቃ ባንክን መሪ አደረገች ተብሎ ቢጠበቅም ረዳት ዳኛዋ ልደት ዋልተንጉስ አወዛጋቢ በሆነ መልኩ ከጨዋታ ውጪ በማለት ሽራዋለች፡፡ ከቀኝ የአዲስ አበባ የግብ ክልል የመጣን ኳስ ሰናይት ቦጋለ ጋር ደርሶ አማካዩዋን ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረችው አረጋሽ ካልሳ ሰጥታት አስገራሚዋ ተጫዋች በድንቅ አቅሟ ታግዛ ጎል በማስቆጠር ባንክን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ጎል አስቆጥረው መሪ ይሁን እንጂ የጎላ ክፍተት ይታይባቸው የነበሩት የብርሀኑ ግዛው ልጆች ከትርሲት መገርሳ የርቀት ሙከራ በኃላ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። ከግራ በኩል ከክፍት የጨዋታ መንገድ የመጣችን ኳስ ቤተልሄም ታምሩ ስታሻግር ፈጣኗ ተጫዋች እምወድሽ አሸብር የንግድ ባንክን የተከላካይ እና ግብ ጠባቂ አቋቋም ስህተተትን ተጠቅማ አዲስ አበባን አቻ አድርጋለች፡፡

በአዲስ አበባ የጨዋታ አካሄድ ቢፈተኑም ጠንካራ የፊት መስመር ያላቸው ንግድ ባንኮች የመጀመሪያው አርባ አምስት ተጠናቆ በተሰጠ ጭማሪ ደቂቃ ላይ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት ሎዛ አበራ ሳይታሰብ አክርራ መታ በማስቆጠር ክለቧን 2 ለ 1 መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ ክፍተታቸው ምን ቦታ እንዳለ የተረዱት ንግድ ባንኮች በቀኝ መስመር እና በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ ገነሜ ወርቁ እና አለምነሽ ገረመውን ካስገቡ በኃላ በመጀመሪያው አጋማሽ የታየባቸውን ክፍተት በተወሰነ መልኩ ቀርፈዋል፡፡ 50ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ አክርራ መታ ግብ ጠባቂዋ ቤተልሄም ዮሐንስ ስትመልሰው አረጋሽ እግር ስር ገብቶ ታታሪዋ ተጫዋች ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች፡፡

አዲስ አበባ ከተማዎች ለማጥቃት ጥረት በሚያደርጉበት ሰዓት የኃላ መስመራቸውን ለማስጠበቅ በነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ አራተኛ ጎል ሊቆጠርባቸው ችሏል፡፡ በዚህ ሂደት ወደ ማዕዘን የወጣችዋን ኳስ ዓለምነሽ ገረመው በቀጥታ ስታሻማ አየር ላይ እያለች ሎዛ በማስቆጠር መሪነታቸውን አጠናክረዋል፡፡ 85ኛው ደቂቃም ረሂማ ከተደጋጋሚ ሙከራ በኃላ ሎዛ የሰጠቻትን ኳስ አስቆጥራ በቀሪው ደቂቃ አዲስ አበባዎች ምንም ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችሉ በንግድ ባንክ የበላይነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አረጋሽ ካልሳ በልሳን የሴቶች ስፖርት የጨዋታው ምርጥ በመባል ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አቶ ኤልያስ ሽኩር እጅ ሽልማቷን ተቀብላለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ