“…ሰውነትህ ደቃቃ ስለሆነ ሁሌም በአዕምሮህ መጫወት አለብህ ይለኛል” – ሀብታሙ ተከስተ

በፊት ከሚታወቅበት እንቅስቃሴው በተለየ ሁኔታ በብዙ መልኩ ተቀይሮ ብቅ ያለውና በዐፄዎቹ የእስካሁን ጉዞ ውስጥ ትልቅ አበርክቶ እያደረገ ከሚገኘው ሀብታሙ ተከስተ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በዚህ ወቅት ጥሩ ከሚባሉ የተከላካይ አማካዮች መካከል ሀብታሙ ተከስተ ይገኝበታል። ከመቐለ 70 እንደርታ አምርቶ መቐለን ፕሪምየር ሊግ በማስገባት እና በቀጣይ ዓመት በሊጉ ድንቅ ጊዜ እንዲያሳልፍ አስተዋፅኦ አድርጓል። ከሁለት ዓመት የመቐለ ቆይታ በኋላ በ2011 ወደ ጎንደር በመመለስ ፋሲል ከነማን ተቀላቅሎ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ሀብታሙ የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከቡድኑ ጋር ማሳካት ችሏል። በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስብስብ ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው ቀጭኑ አማካይ ስለ ወቅታዊ አቋሙ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

“ከባለፉት ዓመታት የተለወጥኳቸው ለውጦች አሉ። ተለወጥኩም ብዬ የማስበው ልምምድ ላይ የማላደርግ የነበረውን አሁን በጣም ነው የምሰራው ከዚህ በተጨማሪም በግሌ ተጨማሪ ልምምዶችን እሰራለው። እነዚህ ነገሮች ሜዳ ውስጥ ተለውጬ እንድመጣ አስተዋፅኦ አድርገውልኛል።

“በአዕምሮ የመጫወቱ ነገር የመጣው ከልጅነቴ ጀምሮ ነው። ይህን የሰራብኝ አንደኛ አሰልጣኝ ተገኝ እቁባይ ነው። ‘አንተ ሰውነትህ ደቃቃ ስለሆነ በአዕምሮህ መጫወት አለብህ’ ይለኛል። እናም እዚህ ላይ ያሰራኝ ነበር። ይበልጥ ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱን ሳገኝ ይበልጥ ተረዳኝ እና ለዛ ነው ከጉልበት ይልቅ ቀድሞ የማሰብ ጨዋታን እየተጫወትኩ ያለሁት።

” እኔ ኳስን ስጫወት ሁሌም አልሸነፍ ባይነት እመርጣለው። በዚህም የተነሳ ከሚመጣ ስሜት አንዳንዴ አላስፈላጊ ነገሮች አድርጋለው፤ ይህም ይገባኛል። አንዳንዴ ከተጫዋቾች ጋር ሜዳ ውስጥ እልህ ውስጥ እጋባና ከወጣሁ በኃላ ለምን ይሄን አደረግኩ ብዬ ራሴን እጠይቃለው። ይህ ከአልሸነፍ ባይነት የሚመጣ እንደሆነ አስባለሁ።

“ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ቡድን እየተጠራው የመጫወት እድል በስፋት አላገኘሁም። ግን ምን አስባለሁ መሰላችሁ፤ ይህ የሆነው በራሴ ድክመት እንደሆነ ነው። ምክንያቱም እኔ ጥሩ አቋም ባሳይ አሰልጣኙ የሚያጫውተኝ ይመስለኛል። ያንን ነገር ስላላደረኩ ነው ያላጫወተኝ ብዬ እረዳለው። ከዚህ በኃላ አሁን ያለውን ነገር አስቀጥዬ ከፈጣሪ ጋር ለብሔራዊ ቡድን ቋሚ ሆኜ ሀገሬን መጥቀም እፈልጋለው።

” ከዚህ ቀደም ሻምፒዮን የሆኑ ቡድኖችን ስታይ ጥሩም ሆነው ያሸንፋሉ፤ ጥሩም ሳይሆኑ አሸንፈው ይወጣሉ። አሁንም የእኛ ቡድን ጋር ያለው ይሄ ነው። ጥሩ ሆነን እናሸንፋለን፤ ጥሩ ባልሆንበትም ሁኔታ ደግሞ ውጤት ይዘን እየወጣን ነው። ይሄ ደግሞ ምን ያሳያል ቡድናችን ውስጥ ያለው መንፈስ ነው። ቡድናችን ውስጥ ያለው ሀሳብ ሁሉም ተጫዋች በርትቶ ታሪክ መስራት ነው የምንፈልገው።

” እስካሁን ፈተነኝ የምለው ተጫዋች የለም። ሲጀመር ተጫዋች አክብጄም አቅልዬም አላይም። ሜዳ ውስጥ ስገባ ለቡድኔ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሁሉ ሳልሳሳ እሰጣለው። ይሄን ያህል እስካሁን የቀለለኝም የከበደኝ ተጫዋች የለም።

“በመጨረሻም ዕድሉን ስላገኘሁ ማመስገን የምፈልገው አለ። የኢትዮጵያ እናት እመብርሃንን ማመስገን እፈልጋለው። አሁን ላለሁበትም፤ ከዚህ በፊት ለመጣሁበት ነገር ሁሉ እርሷ ናት ያመቻቸችልኝ እና እርሷን ማመስገን እፈልጋለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ