ረፋድ ላይ ከተደረገው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ይህንን ብለዋል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ
የአስገዳጅ የተጫዋቾች ለውጡ ውጤት
በመጀመሪያ ተጫዋቾቼን ማመስገን እፈልጋለሁ። ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት የነበራቸው ተነሳሽነት እጅግ የሚያስደስት ነው። ሜዳ ውስጥ ተገደህ ተጫዋቾችን የምትቀይርበት አጋጣሚ ይኖራል። እንደዛም ቢሆን ግን የሰጠናቸውን ታክቲክ ለመተግበር የነበራቸው ቁርጠኝነት የተሻለ ተንቀሳቅሰን ውጤት ይዘን እንድንወጣ አግዞናል።
ስለአጨዋወት ለውጡ
ስንገባ ለመጫወት አስበን የነበረው 4-2-3-1 ነበር። የአሳሪ መጎዳት የታክቲክ ለውጥ እንድናደርግ አስገድዶናል። ሆኖም የቀየርነው ለውጥ የተሻለ ውጤታማ አድርጎናል። ሁሉም ግን ተጫዋቾቹ እንደቡድን ለማሸነፍ የሄዱበት ርቀት እያንዳንዱ የሜዳ ክፍል ላይ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል እና በሽግግሮች ላይ የነበራቸው ተሳትፎ የተሻለ ተንቀሳቅሰን ውጤት ይዘን እንድነወጣ አግዞናል።
የመጨረሻዋ ጎል ከጫና ከመውጣት አንፃር ስለነበራት ሚና
ከዚያ በፊትም እንደዚሁ የጨዋታውን መንፈስ ልትቀይር የምትችል ንፁህ የጎል ዕድል አባክነናል። እየመራህ ስትሄድ በድጋሚ ማጥቃቱ ላይ የበለጠ ውጤታማ የሆንክበትን ስራ ማስቀጠል ፣ ይበልጥ ኳሱን ተቆጣጥረህ የምታጠቃ ከሆነ በተዘዋዋሪ መከላከልንም እየሰራህ ነው። እንደሚመራ ቡድን የተከላካይ ባህሪ ያለው ተጫዋች ማስገባት አልፈለግንም። ጫና ለመፍጠር አሁንም ያስገባነው የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋች ነው። በአጠቃላይ ቀኑ የእኛ ነበር ማለት እችላለሁ።
አሰልጣኝ ፍሰሐ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ
በጨዋታው መጀመሪያ ስለተሳቱ ኳሶች
መጀመሪያም ከዕረፍት በፊት ጨዋታውን መጨረስ ነበር የፈለግነው። እውነትም ያሰብነው ነገር ደርሶ ነበር። ነገር ግን ኳሶቹ ኢላማቸውን አልመቱም። ሁለት ሦስት ኳስ ሳትን ፤ የማሸነፍ ጉጉት ነው እኛም እነሱም ጓጉተን ነበር። ግን በሰራነው ስህተት አንድ ኳስ ገባብን። እየተመራን ነበር ዕረፍት የወጣነው። ከዕረፍት በኃላ ግን እግር ኳስ ሳይሆን ሪፈራል ሆስፒታል ነው የመሰለኝ። መአት ሰው ይተኛል ፣ መአት ሰው ይተኛል ፤ እግር ኳስ እንደዚህ አይደለም። በዚህ ምክንያትም ተሸንፈን ወጥተናል።
የተጋጣሚ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ መውደቅ ስለፈጠረው ተፅዕኖ
ተጫዋቾቼም ወደ እልህ ውስጥ ገቡ ትንሽ ፤ ህግም ጠበቅ አላለም ነበር። ብዙ ተጫዋቾች ናቸው የሚተኙት። ሳይነኩም ተነክተውም ይተኛሉ። በዚህ ሰዓቱም አለቀ የተጨመረው ግን አምስት ደቂቃ ነው። እንደዚህ በሆነ ቁጥር ደግሞ እየወረድክ ነው የምትሄደው።
ጀማል ሲጎዳ ተንበርክከው ስላሳዩት አካላዊ እንቅስቃሴ
አዎ የምታየው ነገር ያሳዝናል። አሁን ጀማል ኳስ አወጣ እና ወደቀ እና ተኛ ፤ ምንም አልሆነም። ዞሮ ዞሮ ሦስት ጎል ነው የገባብን። ተጫዋቾቻችን ስሜታዊ ሆኑ ከዳኛ ጋር ጭቅጭቅ ጀመሩ። መጨረሻ ላይ ለማጥቃት ስንሄድ በመልሶ ማጥቃት እየገባብን መጣ።
ስለፍሬዘር ስህተት
እኛ አንድ እንዳገባን ሌላ ጎል ለማግባት እየፈጠንን ነበር። የፍሬዘር ስህተት ሁለተኛ ጊዜው ነው። መጀመሪያም የገቡት ኳሶች በተከላካዮቻችን ስህተት ነው። እየነቀሉ እየሄዱ ነው በስህተት ነው የገባው። ግን ዞሮ ዞሮ ተሸንፈናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ