ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የኢትዮጵያ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በ 2-2 የአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ቡና በወላይታ ድቻ ከተሸነፈበት ጨዋታ ባደረገው አንድ ለውጥ ሚኪያስ መኮንን በአቤል ከበደ ቦታ ሲጠቀም ባህርዳር ከተማ ግን ቅዱስ ጊዮርጊስን በገጠመበት ጨዋታ የነበረውን አሰላለፍ ሳይለውጥ ቀርቧል።
ጨዋታው በመጀመሪያው ደቂቃዎች ጎሎችን ያገኘ ነበር። ገና በ2ኛው ደቂቃ ቡናዎች ኳስ ከኋላ ለመመስረት ባደረጉት ጥረት ተክለማርያም ሻንቆ ወደፊት ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ዓለሙ አግኝቶ በቀላሉ አስቆጥሯል። ቡናዎች ከአራት ደቂቃ በኋላ በሰጡት ምላሽም ሚኪያስ መኮንን ከመሐል ሜዳ የቀኝ ክፍል ኳሱን በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደፊት በማምራት በቀጥታ ወደ ጎል የላከው ኳስ ከመረብ አርፏል።
ተጋጣሚያቸውን በራሱ ሜዳ አፍኖ ኳስ በመንጠቁ የተዋጣላቸው ባህር ዳሮች ሌሎች አደገኛ ዕድሎችንም መፍጠር ችለው ነበር። 11ኛው ደቂቃ ላይ ከግርማ ዲሳሳ የማዕዘን ምት በግንባሩ ሌላ ሙከራ ያደረገው ፍፁም 23ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ በግንባር የጨረፈለትን ኳስ ይዞ በመግባት ተከላካዮችን አልፎ ለጥቂት ስቷል። ያም ቢሆን ከ1 ደቂቃ በኃላ አህመድ ረሺድ ቀኝ መስመር ላይ ያስጣለውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ሳጥን ውስጥ ተቀብሎ ተከላካዮችን አሸማቆ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
ከተከላካይ ጀርባ ያለው የተለመደው ክፍተታቸው ለተደጋጋሚ ጥቃት ያጋለጣቸው ቡናዎች ሦስተኛ ግብ ለማስተናገድም ተቃርበው ነበር። 32ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም ፍፁም ከመሀል የተላከለትን ኳስ ረጅም ርቀት ነድቶ በተክለማርያም አናት ላይ የማስቆጠር ሀሳቡ ሳይሳካ ኳስ ወደ ውጪ ወጥታበታለች። በኳስ ቁጥጥራቸው የባህርዳርን የመከላከል አቋቋም ሰብሮ ማለፍ የቸገራቸው ቡናዎች ወደ መጨረሻው ላይ ተጋጣሚያቸው በራሱ የግብ ክልል ላይ አመዝኖ ቢታይም ከአንድ ሙከራ ውጪ አቻ መሆን አልቻሉም። አስራት ቱንጆ ከመስመር ያደረሰውን ኳስ አበበ ጥላሁን መትቶ የግቡ ቋሚ ከመለሰበት በኋላም ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ረመዳን ናስርን በአማኑኤል ዮሃንስ ቀይረው ያስገቡት ቡናዎች በተሻለ ጫና ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በቆዩባቸው ደቂቃዎችም ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሰንዝረው 52ኛው ደቂቃ ላይ መናፍ ዐወል ዊሊያም ሰለሞን ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አቡበከር ናስር የመጀመሪያው ምቱ በፂዮን መርዕድ ቢመለስበትም ግብ ጠባቂው መስመሩን በመልቀቁ ደግሜ እንዲመታ ሲደረግ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ባህር ዳሮች ቀስ በቀስ ከሜዳቸው መውጣት ቢችሉም የመጀመሪያው አጋማሽ ዓይነት አጋጣሚዎችን መልሰው ማግኘት አልቻሉም።
ከታፈሰ ሰለሞን የ58ኛው ደቂቃ የርቀት ሙከራ በኋላ በተደጋጋሚ በባህር ዳር ሳጥን ዙሪያ በቁጥር በርክተው መገኘት የቻሉት ቡናዎችም የመጨረሻ የግብ አጋጣሚ መፍጠር ቀላል አልሆነላቸውም። ተደጋጋሚ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ያቋርጡ የነበሩት ባህር ዳሮችም አደገኛ የሚባል መልሶ ማጥቃት ሳይሰነዝሩ ጨዋታው ወደ መጨረሻው ተቃርቧል። 89ኛው ደቂቃ ላይ ተክለማርያም ሻንቆ ከግብ ክልሉ ውጪ ኳስ በእጅ በመንካቱ የቀይ ካርድ ሰለባ ሲሆን እሱን ተከትሎ ሳሙኤል ተስፋዬ የመታው የቅጣት ምት ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። በዛው ቅፅበት ወደ ግብ የደረሱት ቡናዎችም ያለቀለት የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ከአቡበከር ናስር የተነሳውን ኳስ አቤል ከበደ ከግብ አፋፍ ላይ ስቶ ጨዋታው 2-2 ውጤት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።
© ሶከር ኢትዮጵያ