የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 2-2 ባህርዳር ከተማ

ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ሁለት አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ባህርዳር ከተማ

የፈለግከውን አግኝተሃል?

ጎሉን ሊገባብን አካባቢ ወደኋላ ከመሸሻችን በስተቀር በተለይ የመጀመርያ አጋማሽ ላይ የምፈልገውን አግኝቻለሁ። ሁለተኛው አጋማሽ ግን አንዳንድ ጊዜ ሜዳ ላይ መቆጣጠር አልችልም። ወደ ኋላ ትንሽ መሸሻችን ሁለተኛ ጎል እንድናስተናግድ አድርጎናል።

የአጨራረስ ችግሮችን እንደ ድክመት የሚነሱ ከሆነ?

በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ እድሎችን በምንፈልገው መልኩ ፈጥረናል። ምናልበት እነዛን መጠቀም ብንችል ውጤቱ የተለየ ይሆናል። ግን ከሁሉም በላይ ቡድኔ የጎል እድል መፍጠሩን እንደ ጠንካራ ጎን እመለከተዋለሁ። በየጨዋታው እድሎችን ፈጥረን መጠቀም አለመቻልችንም ውጤት እንዳናስመዘግብ ተፅዕኖ አሳድሮብናል። እዛ ላይ ጠንክረን እንሰራለን።

ውጤቱ ፍትሀዊ ነውን?

እኔ ደስተኛ አይደለሁም ማሸነፍ ነበረብን ብዬ አስባለሁ።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

በመጀመሪያው አጋማሽ ለጎሎቹ መንስኤ የሆኑት ስህተቶች እንደ ድክመት የሚታዩ ከሆነ

አዎ! እንደ ድክመት ነው። ነገርግን እኔ የማየው ነገሩን ማስቀጠል የሚችል ነገር ነበር ወይንስ አልነበረም በሚለው ነው። ነበር፤ ስለዚህ አሁንም እዛ ውስጥ ነው የምናርመው ድክመት ነው። እንደነዚህ አይነት ስህተቶች ሌላኛው የሜዳ ክፍል ላይም ይሰራሉ። ነገርግን እዛ ጋር የሚሰሩ ስህተቶች ግን ለጎል የቀረቡ ስለሚሆኑ ተጋጣሚ መሰል እድሎችን ሊያገኝ ይችላል። ነገርግን ስህተቱን ስናርም ቅድሚያ የምናየው ነገር ከእንቅስቃሴው ሳንወጣ ያንን ስህተት እንዳይፈጠር ማረግ እንችላለን ወይ ነው። ያ መፍትሔ ካለ ግን እዛ ላይ ነው እርምት የምንወስደው።

ባህር ዳር ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ ጫና ፈጥሮ መጫወት ከመፈለጉ አንፃር ለማስተካከል ስላለመሞከራቸው

እንዳንጀምር አያደርጉንም፤ እንድንጀምር እድል ይሰጡናል። ከዛ በኃላ ኳሱ ወደ መስመር ሲወጡ እና ቦታዎች ሲጠቡ ለመንጠቅ ይሞክራሉ ለዚህም ተክለማርያምን እንጠቀም ነበር። ብዙ ስህተቶች ሲፈፀሙ ተጫዋቾች ጋር ያለው በራስ መተማመን እንዳይወርድ እንጂ ብዙ የሚያስፈራ ነገር አልነበረውም። ከዛ በኃላ እንዳየኸው 90 ደቂቃ በዚያ መዝለቅ አልቻሉም። ተመልሰው ወደ ሜዳቸው ገብተዋል።

ስለመጨረሻዋ ቅያሬ

ለነገሩ መቀየር የፈለግነው ሀብታሙን ነበር። አቤል በዚህኛው መስመር የቀኝ እግር ተጫዋቾች ስለሆነ ኳስ ሲያዝ ሰውየው በኳሱ ሳይድ ነው የሚሆነው። እሱም በሰየው እና በኳሱ መካከል መሆን አልቻለም። ስለዚህ አላዛርን ቀይረን አቤልን በዚያኛው መስመር ለማድረግ ነበር ሀሳባችን። ነገርግን በተፈጠረው ክስተት ይህን ማድረግ ሳንችል ግብጠባቂ ለማስገባት ተገደናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ