ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ድሬዳዋ ከተማ የዙሩ የመጨረሻ ጨዋታውን በድል አጠናቋል

የመዝጊያ ፕሮግራም በተደረገበት የመጨረሻው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 3 ለ 1 ጌዲኦ ዲላን በማሸነፍ አንደኛውን ዙር በድል ፈፀመ፡፡

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን አቶ ኤልያስ ሽኩር፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ እና የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች ክብርት ሶፊያ አልማሙ እና ዘሪሁን ቀቀቦ በስታዲየሙ ተገኝተው በተከታተሉት ጨዋታ የመጀመሪያው አርባ አምስት ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ እንቅሴቃሴ ያደረጉ ቢሆንም በይበልጥ ግን በሙከራ ድሬዳዋዎች ተሽለው በሜዳ ላይ ታይተዋል፡፡ 3ኛው ደቂቃ ላይ በጌዲኦ የግብ ክልል በአጨቃጫቂ መልኩ የተሰጠውን የቅጣት ምት ፀጋነሽ ወራና በቀጥታ መታ በማስቆጠር ድሬዳዋን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ድሬዳዋ ከተማዎች በእንቅስቃሴ ሻል ብለው ቢታዩም በመልሶ ማጥቃት በቱሪስት ለማ አስፈሪነታቸው ይስተዋልባቸው የነበሩት ጌዲኦ ዲላዎች 9ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት መንደሪን ስታሻማ ቱሪስት ለማ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ክለቧን 1 ለ 1 አድርጋለች፡፡ ጨዋታው በዚህ ውጤት ቀጥሎ ጌዲኦ ዲላዎች ኳስን ሲይዙ በሚያደርጉት ቅብብል ወጥ የሆነ ባለ መሆኑ ለድሬዳዋ ተጫዋቾች ምቾትን የፈጠረላቸው ሆኗል፡፡በእፀገነት ግርማ ሁለቴ የርቀት ሙከራን ቢያደርጉም ጎል ማስቆጠር የተሳናቸው ጌዲኦ ዲላዎች በአንፃሩ 28ኛው ደቂቃ ከተቋረጠ ኳስ ማዕድን ሳህሉ የሰጠቻትን ኳስ ፀጋነሽ ወራና በግሩም አጨራረስ ወደ ጎልነት ለውጣው ድሬዳዋን 2 ለ 1 በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእንቅስቃሴ ውጪ ብዙም የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት ባልቻልንበት ሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች የበላይነታቸውን ያሳዩበት ጌዲኦ ዲላዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ አቋማቸው ወርደው የታየበት ነበር። በተለይ አጥቂዋ ቱሪስት ለማ በተደጋጋሚ ጥፋት ይሰራባት ስለነበር የሷ ጉዳት ማስተናገድ የቡድኑን እንቅስቃሴ ዝቅ ለማድረጉ ዋነኛ ማሳያ ነበር፡፡ ሆኖም 70ኛው ደቂቃ ከመስመር ማዕድን ስታሻግር የዲላ ተከላካዮች የሰሩት ስህተት ተጠቅማ ትንቢት ሳሙኤለል ወደ ጎልነት በመለወጥ ድሬዳዋን 3 ለ 1 አሸናፊ በማድረግ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ አመቱን በሽንፈት የጀመረው ድሬዳዋ ከተማን አንደኛውን ዙር በስኬት ደምድሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለአንደኛው ዙር አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እና ድርጅቶች ሰርተፊኬትን አበርክተዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ዕውቅና ተሰጥቷታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ