የጨዋታ ሳምንቱ ሁለተኛ ቀን የሚጀመርበትን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሊጉ መሪዎች ተርታ ላለመራቅ ሲዳማ ቡና ደግሞ በመጠኑ ከሸሸው የአደጋ ዞን ይበልጥ ከፍ ለማለት የሚረዷቸውን ነጥቦች ፍለጋ ነገ ይገናኛሉ።
ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን ያሳኩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻዎቹ ሁለቱ ግባቸውንም ሳያስደፍሩ መውጣት ችለዋል። ከአምስት ጨዋታዎች በኃላ ያሳኩት ይህ ተከታታይ ሪከርድ ቀጣይነት በአስቻለው ታመነ ቅጣት ምክንያት ነገ ይዘውት በሚገቡት አዲስ የተከላካይ መስመር ጥምረት ላይ የሚወሰን ይሆናል። በእርግጥ ቡድኑ ግብ አያስተናግድ እንጂ ከተከላካዮች አምልጠው ከኋላ ያለውን ሰፊ ክፍተት የጥቃት ማዕከል ያደረጉ አጋጣሚዎችን ለተጋጣሚዎች ሳይፈጥር ቀርቷል ማለት አይቻልም። በዚህ ረገድ በሳጥኑ ዙሪያ ባለው የነቃ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ምቹ ያልሆነው የሲዳማው ማማዱ ሲዲቤ ከፈረሰኞቹ የኋላ ተሰላፊዎች ጋር የሚገናኝባቸው ቅፅበቶች ወሳኝ ይሆናሉ።
ሁነኛ ጥምረትን መፍጠር ያልቻለው የሲዳማ የተከላካይ ክፍልም እንዲሁ በመጨረሻው ጨዋታ ዕድለኛ ሆኖ ግብ አይቆጠርበት እንጂ ለሰበታ አጥቂዎች በጣሙን ተከፍቶ ታይቶ ነበር። በተለይም ከመስመር ለሚነሱ ኳሶች ደክሞ መታየቱ በሄኖክ አዱኛ የሜዳው ቁመት ሩጫ ላይ ለታመሰረተው የጊዮርጊስ የቀኝ መስመር ጥቃት ሊያጋልጠው ይችላል። በዚህ ረገድ ከተሻጋሪ ኳሶች በፊት ሄኖክ አዱኛን ከግሩም አሰፋ የሚያገናኙ ቅፅበቶች ወሳኝነታቸው ከፍ ያለ ነው። ጊዮርጊሶች ሰሞኑን ከቆሙ ኳሶች አስፈሪ ዕድሎችን ሲፈጥሩ መታየታቸውም ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በድን የስጋት ምንጭ የሚሆን ሌላው ጉዳይ ነው።
በያስር ሙገርዋ እና ዳዊት ተፈራ የሳጥን ውጪ ሙከራዎች እንዲሁም ለፈጣን ሽግግር የሚሆኑ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ጥቃት ሲጥሉ የሙታዩት ሲዳማዎች ይህ አጨዋወታቸው በናትናኤል ዘለቀ መመለስ መረጋጋት በታየበት የፈረሰኞቹ አማካይ ክፍል ውስጥ የሚኖረው እንቅስቃሴ ሌላኛው ተጠባቂ ጉዳይ ነው። ወዳረሻውን ወደ ሳጥን ውስጥ ሲያደረግ የሚታየው የመስመር አጥቂዎቻቸው የማጥቃት ሂደት ግን ከጊዮርጊስ የቦታው ጫን ያለ ማጥቃት ምርጫ አንፃር ሊታፈን ይችላል። በዚህም ከሀብታሙ ገዛኸኝ ይልቅ በተመስገን በጅሮንድ በኩል የተሻለ የፊት መስመር ጥቃት ሊያስመለክቱን ይችላሉ።
በሌላ በኩል በተጋጣሚዎቻቸው ላይ የተረጋገጠ ብልጫ ሲወስዱ የማይታዩት የሁለቱ በድኖች አማካይ ክፍሎች እንቅስቃሴዎችን ወደ መስመር የማውጣት አዝማሚያ ሊኖራቸው እንደሚችል ይታሰባል። በግል ደረጃ የጊዮርጊስ የማጥቃት አማካዮች ከብርሀኑ አሻሞ ጋር የሚገናኙባቸው ቅፅበቶች ዓይን ሊስቡ ይችላሉ። ከዛ ባለፈ ግን በሰበታው ጨዋታ ጥሩ የግብ ዘብነቱን ያሳየው መሳይ አይኖ ነገ በተመሳሳይ አቋም ቡድኑን ከነጌታነህ ከበደ ኳሶች ያድናል ወይ የሚለው ከጨዋታው ምላሽ ከሚያገኙ በርካታ ጉዳዮች አንዱ ይሆናል።
በነገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሀል ተከላካዩ አስቻለው ታመነን በቀጥታ ቀይ ካርድ ቅጣት የማይጠቀም ሲሆን ሙሉዓለም መስፍንም በግል ጉዳይ ምክንያት ከስብስቡ ጋር አይገኝም። በሲዳማ በከል ጉዳት ካይ የሰነበቱት አዲሱ አቱላ ፣ ይገዙ ቦጋለ ፣ ዮናታን ፍሰሀ እና ፍቅሩ ወዴሳ ከጉዳት ወደ መደበኛ ልምምድ የተመለሱ ሲሆን የመሰለፋቸው ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ነው። ጫላ ተሺታ ግን አሁንም ጉዳት ላይ እንዳለ ሰምተናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 20 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 ጊዜ በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ያለው ሲሆን ሲዳማ ቡና አንድ ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በግንኙነቶቹ ጊዮርጊስ 30 ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና 8 አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ፓትሪክ ማታሲ
ሄኖክ አዱኛ – አማኑኤል ተርፋ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ
ሀይደር ሸረፋ – ናትናኤል ዘለቀ
ጋዲሳ መብራቴ – ሮቢን ንግላንዴ – አቤል ያለው
ጌታነህ ከበደ
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
መሳይ አያኖ
አማኑኤል እንዳለ – ፈቱዲን ጀማል – ጊት ጋትኮች – ግሩም አሰፋ
ዳዊት ተፈራ – ብርሀኑ አሻሞ – ያስር ሙገርዋ
ተመስገን በጅሮንድ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
© ሶከር ኢትዮጵያ