ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የጨዋታ ሳምንቱ ሁለተኛ ቀን የከሰዓት ግጥሚያ ላይ የሚያተኩረውን ዳሰሳችን እንዲህ አሰናድተነዋል።

ከድል ጋር ከተፋታ ስድስት የጨዋታ ሳምንታትን ያሳለፈው ሰበታ ምንአልባትም ከነገው ፍልሚያ የሚገኙትን ነጥቦች ከተጋጣሚው በላይ ይፈልጋቸዋል። በባህር ዳሩ እና በሲዳማው ጨዋታ የነበረበትን የማጥቃት ድክመት አሻሽሎ የታየው ሰበታ የመጨረስ አቅሙ መዳከም ሌላ ችግሩ ሆኖ የመጣ ይመስላል። ከበፊቱ በተሻለ የቡድኑ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚገቡ ቅብብሎች በርከት ብለው በታዩባቸው በነዚህ ጨዋታዎች በተለይም በሲዳማው ግጥሚያ ቡድኑ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ዕድለኛ አልነበረም ማለት ይችላል።

ይህ ሂደት በነገውም ጨዋታ ቀጥሎ ሰበታ የቅብብሎቹን ቀጥተኛነት ጨምሮ አጥቂዎቹን ከባድ የተከላካይ መስመር ካለው ሀዲያ ሆሳዕና የኃላ ክፍል ጋር የሚያገናኝባቸው ቅፅበቶች ሊበረክቱ ይችላሉ። ይህን ለማድረግ ግን ጉሽሚያ ሊበረከትበት የሚችለውን የአማካይ ክፍል ፍልሚያ ማለፍ የግድ ይለዋል። ሆኖም በጉዳት እና ቅጣት የሳሳው የአማካይ ክፍል ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንደሚችል ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ ነው። መነቃቃት እየታየባቸው ያሉት የቡድኑ መስመር ተከላካዮችም የሆሳዕናን ከባድ የመስመር ጥቃት በመመከት እና ማጥቃቱን በማገዝ መሀል ጥንቃቄ የሚጠይቅ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። በሌላኛው ደካማ ጎኑ የመጀመሪያ አሰላለፍ ምርጫ መረጋጋት የማይታይበት ሰበታ እንደ ዱሬሳ ሹቢሳ ላሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች ነገ የተሻለ ዕድል ሊሰጥ እንደሚችልም ይገመታል።

ካለፉት አራት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦች ብቻ ያሳኩት ነብሮቹ በላይኛው ፉክክር ውስጥ ለመዝለቅ ከፈለጉ በመሰል ጨዋታዎች ላይ ብልጫን ወስደው ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። ከሦስት ቀናት በፊት እጅግ እልህ አስጨራሽ በነበረው የሀዋሳ ጨዋታ ብዙ ጉልበት ያወጣው ሆሳዕና ነገ የኳስ ቁጥጥርን ከሚያዘወትር ቡድን ጋር ይገጥማል። ብዙ ደቂቃዎችን በተጋጣሚው ኳስ ከተያዘበትም በቂ ያልሆነው የዕረፍት ጊዜ ከኳስ ውጪ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለሚያስፈልገው ጉልበት እክል እንዳይሆንበት ያሰጋዋል።

የነገው ጨዋታ ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስብ የቡድኑ ጠጣር የመከላከል መስመር ካለ ተስፋዬ አለባቸው የአማካይ ክፍል ሽፋን ምን ዓይነት አቀራረብ ሊኖረው እንደሚችል የሚያሳይበት ጨዋታ ነው። ከሰሞኑ ተቀዛቅዞ የታየው የቡድኑ የሦስትዮሽ የአጥቂ መስመር በአንፃሩ ከተጋጣሚው ተከላካይ ክፍል ደካማነት አንፃር ወደ ውጤታማነቱ ሊመለስ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። በሌላኛው የሜዳ ላይ ፍልሚያ እንደ አማኑኤል ጎበና ባሉ ታታሪ ተጫዋቾች የተሞላው እና ጉሽሚያንም የሚያዘወትረው የቡድኑ የመሀል ክፍል የሰበታን ተመሳሳይ ክፍል የኳስ ፍሰት በዚሁ አኳኋን ከማቆም ሌላ በፈጣን ሽግግር ሦስቱን አጥቂዎች ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ሰበታ ከተማ ያሬድ ሀሰን እና ዳንኤል ኃይሉን በቀይ ካርድ ቅጣት ሳቢያ ሲያጣ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፣ ፉዓድ ፈረጃ እና ታደለ መንገሻንም በጉዳት ምክንያት መጠቀም አይችልም። በአንፃሩ ቀለል ያለ ልምምድ የጀመረው ዳዊት እስጢፋኖስ የጨዋታ ደቂቃዎች እንደሚኖሩት ይገመታል። ጉዳት ገጥሞት የነበረው እና ያገገመው መሀመድ ሙንታሪን የማሰለፍ ዕድል ያለው ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ተስፋዬ አለባቸውን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ሳቢያ የሚያጣ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በተሰረዘው የውድድር ዓመት ሰበታ ከተማ 2-1 ያሸነፈበትን ጨዋታ ሳይጨምር ቡድኖቹ በሉጉ የመጀመሪያ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት ዓሎ

ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – አብዱልባስጥ ከማል – መስዑድ መሐመድ

ዱሬሳ ሹቢሳ – ፍፁም ገብረማርያም – ቡልቻ ሹራ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-4-2)

መሀመድ ሙንታሪ

ሱለይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ቢስማርክ አፒያ – አማንኤል ጎበና – አዲስ ህንፃ – መድሀኔ ብርሀኔ

ሳሊፉ ፎፋና – ዳዋ ሆቴሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ