ሪፖርት | ሆሳዕና እና ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

ረፋድ 04፡00 ላይ የተገናኙት ሀዲያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከሰበታው ጨዋታ አዲስ ህንፃ ፣ አልሀሰን ካሉሻ እና ሚካኤል ጆርጅን በሄኖክ አርፌጮ ፣ ዳዋ ሆቴሳ ፣ ሳሊፉ ፎፋና ቦታ ሲለውጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማን ሲገጥም የተጠቀመበትን አሰላለፍ ሳይቀይር ጨዋታውን ጀምሯል።

የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴን ያስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አልተደረገበትም። በተጨዋች ምርጫ ደረጃ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያላቸው ይመስሉ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ብቸኛው ለግብ የቀረቡበት አጋጣሚ 43ኛው ደቂቃ ላይ አይዛክ ኢሴንዴ ከአዲስ ህንፃ የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት ነው። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ጊዮርጊሶችም ጠንካራውን የሀዲያ ሆሳዕናን የኃላ ክፍል አልፎ መግባት ቀላል አልሆነላቸው። ካገኟቸው የቆሙ ኳሶችም ከባድ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩት ጊዮርጊሶች 27ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከቀኝ መስመር አሻግሮት ፍሪምፖንግ የሞከረው እና በግቡ አግዳሚ ተፈጭቶ በወጣው ኳስ ለመሪነት ተቃርበው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው የተሻለ የማጥቃት ተነሳሽነት ታይቶባቸዋል። በቀዳሚዎቹ ደቂቃዎች ወደ ፊት ገፍተው ሲጫወቱ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ አፒያ በተከላካዮች መሀል ያሳለፈለትን ኳስ ካሉሻ አልሀሰን ጨርፎ ለማስቆጠር ቢሞክርም ለዓለም ብርሀኑ ቀድሞ ኳስን ተቆጣጥሯል። ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ቀስ በቀስ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ለማገኘት ጥረት ሲያደርጉ 64ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዘለቀ ከግማሽ ጨረቃው ላይ አክርሮ የመታውን ኳስ መሀመድ ሙንታሪ አድኖበታል።

በተመጣጠነ የጥቃት ሙከራ የዘለቀው ጨዋታ 78ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግዷል። የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ዳዋ ሆቴሳ ተቀይሮ ከገባ ደቂቃዎች በኃላ ኤድዊን ፍሪምፖንግ ኳስ በእጁ ምክንያት በመንካቱ የተገኘውውን ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት አስቆጥሯል። ሆኖም ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ጊዮርጊስ
ባደረገው የአደራደር ለውጥ ወደ ቀኝ መስመር ተመላላሽነት የተቀየረው ሄኖክ አዱኛ ቴዎድሮስ በቀለ በግንባሩ ወደ ግብ ጠባቂ ለማሳለፍ የሞከረውን ኳስ ቀድሞ በመገኘት አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጎታል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ቡድኖቹ ጨዋታውን ለማሸነፍ በተለይም ረጃጅም ኳሶችን በመጣል ብርቱ ፉክክር ቢያደርጉም 86ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከሱሌይማን ሀሚድ ተቀብሎ ከቅርብ ርቀት ካደረገው ሙከራ ሌላ ከባድ የማጥቃት አጋጣሚ ሳይፈጠር ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ