የዕለቱ ሁለተኛ የነበረው የሰበታ ከተማ እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።
ሰበታ ከተማ በሲዳማ ከተሸነፈበት ጨዋታ ባደረጋቸው አራት ለውጦች ዓለማየሁ ሙለታ ፣ መሳይ ጳውሎስ ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና እስራኤል እሸቱን ቅጣት ላይ በሚገኘው ዳንኤል ኃይሉ ፣ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ አብዱልባስጥ ከማል እና ፍፁም ገብረማርያም ቦታ ተጠቅሟል። በአንፃሩ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከሀዋሳ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ያደረጉት ብቸኛ ለውጥ የአምስት ቢጫ ቅጣት ያለበት ተስፋዬ አለባቸውን በተስፋዬ በቀለ ተክተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ አቀራረብ ወደ ሜዳ የገቡበት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የተቀዛቀዘ ሆኖ ያለፈ ነበር። ጥንቃቄን መሰረት ያደረግው የቡድኖቹ አቀራረብ በፈጣሪ አማካይነት የሚጠቀስ ተጫዋች ይዘው ወደ ሜዳ ካለመግባታቸው ጋር ተዳምሮ በሁለቱም የሜዳ አጋማሾች የመጨረሻ የግብ ዕድል የሚፈጥሩ ኳሶችን ማግኘት ከተሳናቸው የፊት መስመር ተሰላፊዎች ይልቅ ተከላካዮች የበላይ ሆነው ታይተዋል።
የእስራኤል እሸቱ እና ቡልቻ ሹራ ፍጥነት ላይ ተመስርተው ወደ ፊት ኳሶችን ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ሰበታዎች የኳስ ፍሰታቸው ወደ ሳጥኑ ዘልቆ ሲገባ አይታይም ነበር። ሀዲያ ሆሳዕናዎችም ቢሆኑ 32ኛው ደቂቃ ላይ ከሱሌይማን ሀሚድ የማዕዘን ምት ቴዎድሮስ በቀለ በግንባሩ ከሞከረው እና በዛው ደቂቃ ሱሌይማን ከሳጥን ውጪ ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ሌላ አደገኛ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። የፊት መስመር ሦስቱ ተሰላፊዎቻቸውም የወትሮው ተፅዕኗቸው ሳይታይ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ሀዲያ ሆሳዕናዎች አዲስ ህንፃ እና ካሉሻ አልሀሰንን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለመደገፍ ሞክረዋል። በመሆኑም በአጋማሹ ከመጀመሪያው በተሻለ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። 49ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱልሀፊዝ ቶፊቅ በተቀማ እና ወደ ፊት በተላከ ኳስ ቢስማርክ ከተከላካይ ጋር ታግሎ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ዳዋ ሆቴሳም እንዲሁ በሁለት አጋጣሚዎች በግንባሩ ያደረጋቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። በሌላ ቡድኑን ለግብ ባቀረበ አጋጣሚ 71ኛው ደቂቃ ላይ ካሉሻ አልሀሰን ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት ወጥቷል።
ተሻሽሎ በገባው ተጋጣሚያቸው ጫና የማጥቃት ሂደታቸው ይበልጥ ተቀዛቅዘው የነበሩት ሰበታዎች ዳግም በአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔ ለሽንፈት ሊዳረጉ ይችሉበት የነበረ ክስተት ተፈጥሯል። በ87ኛው ደቂቃ ዱላ ሙላቱ በቀኝ የሜዳው ክፍል ከመሳይ ቀድሞ ኳስ ለማግኘት ባደረገው ጥረት በመውደቁ የመሐል ዳኛው ተካልኝ ለማ ከረዳት ዳኛው ትግል ግዛው ጋር ተማክረው የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ሆኖም ምንተስኖት አሎ የዳዋ ሆቴሳን ፍፁም ቅጣት ምት አድኖ ቡድኑን ከሽንፈት መታደግ ችሏል። በቀሩት ደቂቃዎችም ቡድኖቹ ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ፍትጊያ ሳይሳካ ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ