“አውቅ ነበር ኋላውን ከፍተው እንደሚሄዱ፤ አስቤበት ነው የገባሁት” – አብዲሳ ጀማል

በውጤት ማጣት ሲንገዳገድ የቆየው አዳማ ከተማን በአስደናቂ ብቃቱ በሀዋሳ ከተማ ላይ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሐት ትሪክ በመስራት ቡድኑን ወደ አሸናፊነት ከመለሰው አብዲሳ ጀማል ጋር ቆይታ አድርገናል።

ሻሸመኔ ከተማ የተወለደው አጥቂው በከተማዋ በሚገኝ ፕሮጀክት ከነበረከት ደስታ፣ ጫላ ተሺታ እና ከሌሎቹም ወጣቶች ጋር በተለያያ አጋጣሚ በፕሮጀክት ውድድር ተጫውቷል። አጭር በሆነው የእግርኳስ ህይወቱ በአርሲ ነገሌ ከብሔራዊ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ በማሳደግ የክለብ ህይወቱን በስኬት ጀምሯል። ከሁለት ዓመት ነገሌ ቆይታ በኃላ ወደ ለገጣፎ ያመራው አብዲ በከፍተኛ ሊግ የነበረው ጥሩ የአጥቂነት ባህሪ በለገጣፎ አንድ ዓመት በላይ እንዳይቆይ አድርጎት በዘንድሮ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ወደሚሳተፈው አዳማ ከተማ መቀላቀል ችሏል። በመክፈቻው ጨዋታ ለአዳማ ሁለት ጎሎች ጅማ አባ ጅፋር ላይ በማስቆጠር የፕሪምየር ሊግ የጎል አካውንቱን በመክፈት ጥሩ ጅማሮ ቢያደርግም ጉዳት የሚያስበውን ያህል እንዳያደርግ አግዶት ቆይቶ በዛሬው ዕለት ሀዋሳ ከተማ ላይ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሐት ትሪክ በመስራት ወደ ፊት ምርጥ አጥቂ እንደሚሆን ራሱን ለማሳየት ችሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሐት ትሪክ የሰራበትን ኳስ ይዞ ከሄደው አብዲሳ ጀማል ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ቆይታ አድርገናል።

” ዛሬ ለኔ የተለየ ቀን ነው። ጎል ከማግባቴ በላይ ቡድናችን ውጤት ያስፈልገው ስለነበረ በሁላችንም ላይ ኃላፊነት ነበር። እኔ ደግሞ ጎል አስቆጥሬ ቡድኔን የመታደግ ኃላፊነት ነበረብኝ። በአላህ ፍቃት ይህ ተሳክቶልኝ ሦስት ጎል ለማስቆጠር ችያለው።

” ዛሬ እንደ ቡድን ተነጋግረን ነው የገባነው። አውቅ ነበር ከፍተው እንደሚሄዱ አስቤበትም ነው የገባሁት። የመስመር ተከላካዮቹ ነቅለው እንደሚሄዱ ስለተነገረን እና ሁለት የመሐል ተከላካዮች ብቻ ስለሚቀሩ እነርሱን እንደማልፋቸው እርግጠኛ ነበርኩኝ። እኔም አቅሜን ሰብስቤ በመጠቀም ሐት ትሪክ ልሰራ ችያለው።

” በመጀመርያው ሳምንት ጅማ ላይ ጎል ካስቆጠርኩ በኃላ ልምምድ ላይ ባጋጣመኝ ጉዳት የነበረኝን አቅም አውጥቼ ለመጠቀም ትንሽ ፈተና ሆኖብኛል። ቡድኑ አሁን ካለበት ሁኔታ እንጂ ዛሬም ከእነ ጉዳቴ ሳይሻለኝ ነው የተጫወትኩት። ሜዳ ላይ እንቅስቃሴዬን አይታቹ ከሆነ የህመም ስሜት ይሰማኝ ነበር። ያው ለቡድኑ የዛሬው ውጤት ስለሚያስፈልግ ነው። ከነ ጉዳቴ ለመጫወት የቻልኩት። በቀጣይ ራሴን አስታምሜ በወጥነት አዳማን ማገልገል አስባለሁ።

” እቅድ አለኝ፤ በእግርኳሱ ትልቅ ደረጃ ለመድረስ እፈልጋለው። ይህ ከልጅነቴ ጀምሮ ያለኝ ምኞት ነው። ደግሞ ይህን እንደማሳካ እርግጠኛ ነኝ። ራሴን በሊጉ ለማሳየት ከማደርገው ጥረት በተጓዳኝ ከሀገር ወጥቶ የመጫወት እቅድ አለኝ። ፈጣሪም እንደሚረዳኝ እምነት አለኝ።

” እስካሁን አምስት ጎል አለኝ። ለሊጉ አዲስ ነኝ፤ ከታችኛው ሊግ ነው የመጣሁት። ገና በጅማሬዬ አምስት ጎል ማስቆጠር በጣም ትልቅ ነገር ነው። ከዚህ በኃላም ራሴን በከፍተኛ ጎል አግቢ ፉክክር ውስጥ ማቆየት አስባለሁ።

” በከፍተኛ ሊግም ሆነ በታችኛው ሊግ በጣም አቅም ያላቸው ዕድሉን ያላገኙ ማደግ የሚችሉ ልጆች አሉ። ዋናው ጠንክሮ መስራት እና አዕምሮን ማሳመን ነው። ምንም የተለየ ነገር የለም። በጣም ቀላል ሊግ ነው። ዋናው ጠንክሮ መስራት ብቻ ነው።

“በመጨረሻም ሐት ትሪክ የሰራሁባትን ኳስ ለማስታወሻ ወስጃለው። ይህ ሌላው የዛሬው አስደሳች ነገር ነው። ይህም መለመድ ያለበት ጥሩ ነገር ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ