የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 1-3 ወላይታ ድቻ

በ10ኛ ሳምንት የማሳረጊያ መርሐ ግብር ወላይታ ድቻ ጅማ አባጅፋርን 3-1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ተከታዩን ሀሳብ ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

በጨዋታው የመስመር ተጫዋቾች ስለነበራቸው ሚና

አፈፃፀማቸው ትንሽ ደካማ ነው። ምክንያቱም በ3-5-2 ፎርሜሽን የመስመር ተጫዋቾች ናቸው 100% ስኬት የሚያስመዘግቡት። ነገርግን የእኛ ተጫዋቾች በምንፈልገው መጠን አማካዩንም ተከላካዮቹንም ሲያግዙልን አልነበረም። የእነሱ መስመሮቹን የመጠቀም ነገር ጨዋታው ደካማ መሆኑ እንጂ ጥሩ አልነበሩም።

በሽግግሮች ወቅት ችግሮች ስለመኖራቸው

ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አንደኛ እኛ ከጅማ ጨዋታ አንፃር የፈለግነው ኳሱን ተቆጣጥረን የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ነው። ምናልባት ከማዕዘን ምቱ ጎል ውጭ ጎሎቹ ሲሄዱ የነበረው በዛ ልክ ነበር። ነገርግን ልጆቻችን የጋራ ኳስን ነበር ይወረውሩ የነበሩት። ያ ደግሞ ውጤታማ አያደርገንም። ስለዚህ በትክክል ችግሮች ነበሩ።

ሜዳን አስፍቶ ስለመጫወት

እንዳለህ አቅም ነው። ተጫዋቾችህ ያንን አድርገህ እንድትጫወት የሚፈቅዱ ከሆነ ትጫወታለህ። አሁን ያለን አቅም ይህ ነው። ስለዚህ በዚህ መልኩ እየተጫወትን ነው። በቀጣይ እንደምናመጣቸው ተጫዋቾች አጨዋወታችን ይወሰናል።

አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባጅፋር

የተከታታይ ሽንፈቶች ተፅእኖ

ያው መጀመሪያው ከዋናው አሰልጣኝ ጋር በነበርንበት ሰዓት የነበረው ነገር ነው የተከሰተው። ይሄ የድግግሞሹ ነገር ለማስተካከል ነበር ጥረት ያደረግነው። ከሦስት አራት ጨዋታ በፊት ተስተካክሎ ነበር። አሁን ወደ ፊት መሄድ እንዳለብን ተነጋግረን ነበር። ነገርግን ተከላካዮቻችን ላይ በነበሩ ስህተቶች ነበር ጎሎች ሲቀጠሩ የነበሩት። ኳሱን በምንፈልገው መንገድ ነበር ልጆቼ ሲጫወቱ የነበረው። እኛ በተደጋጋሚ ሰው ጎል ጋር ባንሄድም በመጡበት አጋጣሚ የተቆጠሩብን ጎሎች ተጫዋቾችን እያወረደብን መጣ።

በመጀመሪያው እና በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው ቡድን በጉልበት ረገድ የተለያየ ስለመሆኑ

በመጀመሪያ የተጠቀምናቸው ተጫዋቾች ልምምድ ሙሉ ለሙሉ አላሟሉም ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በ4-2-3-1 ነበር የተጠቀምነው። ያው ጎሎች መቆጠር ሲበዙብን ወደ 4-3-3 ቀይረነዋል። ለዛም ነበር በተደጋጋሚ ጎል ጋር ለመድረስ ጉልበት ያላቸው ተጫዋቾችን ስንጠቀም የነበረው።

በቀጣይ

ያው ያለን አማራጭ ወደሚቀጥለው ማሰብ የቀረችውን ሦስት ነጥብ ይዘን ከዚህ ለመሄድ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ