አስረኛ ሳምንት ላይ የደረሰው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዚህ ሳምንት ዐበይት ክለብ ነክ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
👉 ያለወሳኝ ተጫዋቾቹ ያሸነፈው ወልቂጤ ከተማ
በ10ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጨዋታ ሳምንቱ የመክፈቻ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 3-1 በመርታት ከሽንፈት መልስ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑት ተስፋዬ ነጋሽ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና ፍሬው ሰለሞንን በጉዳት መጠቀም አለመቻላቸው ተከትሎ በርከት ያሉ የተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በጨዋታው 30ኛው ደቂቃ ከቅጣት መልስ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ጨዋታ ያደረገውን አልሳሪ አልመህዲንም በጉዳት ቀይረው ለማስወጣትም ተገደው ነበር።
ሆኖም ምስጋና ቡድኑ ለያዘው የስብስብ ስፋት ይግባና ከባድ ይመስል የነበረውን ፈተና በአግባቡ መወጣት ችሏል። በዚህም አሜ መሐመድ ተቀይሮ ገብቶ አንድ ጎል በማስቆጠር እና ሌላኛውን ደግሞ ለአቡበከር ሳኒ በማመቻቸት ወልቂጤን ለድል ሲያቃርብ ከሙኸዲን ሙሳ የ75ኛ ደቂቃ ጎል በኃላ ጫና ውስጥ እንዳይገባ ያሰጋ የነበረው ቡድን አብዱልከሪም ወርቁ የፍሬዘር ካሳን ስህተት ተጠቅሞ ባስቆጠራት ተጨማሪ ግብ አሸናፊነቱን አረጋግጧል።
ከጨዋታው በፊት በወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ጉዳት ጨዋታውን በምን መልኩ ይወጡታል የሚለው ነገር ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ቡድኑ ከሁኔታዎች ጋር ራሱን አስካክሎ ከጨዋታው ወሳኙን ሦስት ነጥብ ማሳካት መቻሉ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው አጋጣሚ ነበር።
👉በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ የጣለው ኢትዮጵያ ቡና
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በወላይታ ድቻ ሽንፈትን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና በዚህ የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርቷል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ከባህር ዳር ከተማ ጋር 2-2 አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ከራሳቸው የግብ ክልል መስርተው እንዳይወጡ በባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዲገቡ በመገደደዳቸው መነሻነት ሁለት ግቦችን አስተናግደዋል። ግቦቹ በመጀመሪያው የኳስ ምስረታ ሂደት ላይ ተክለማርያም ሻንቆ እና ወንድሜነህ ደረጀ በሰሯቸው የማቀበል ስህተቶች የተገኙ ነበሩ። ባህር ዳር ከተማዎች በሁለት አጋጣሚ ጨዋታውን መምራት ቢችሉም ኢትዮጵያ ቡናዎች በሚኪያስ መኮንን አስደናቂ ግብ እና በአቡበከር ናስር የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ወደ ጨዋታው ተመልሰው አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ችለዋል።
የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከወዲሁ ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቅ በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር ጠንካራ ጨዋታ የሚጠብቀው ይሆናል።
👉የማይገባበት እና የማያገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለግብ የተለያዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ሲዳማ ቡናን በገጠሙበት ጨዋታ አዲስ ግደይ ፣ አቤል ያለው ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ጌታነህ ከበደን በአንድነት በተጠቀሙበት ጨዋታ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድልን ከክፍት ጨዋታ መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሊያጠናቅቁ ችለዋል።
በመከላከል ረገድ የነበረበትን መዳከም በተወሰነ መልኩ እያሻሻለ የሚገኘው ቡድን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱ በመልካም ጎኑ የሚጠቀስ ቢሆንም በሁለቱም ጨዋታዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገር መስተዋሉ ደግሞ ለአሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ እና ረዳቶቻቸው ስጋትን የሚያጭር ክስተት ነው።
👉እየተቀዛቀዘ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና
በሊጉ አስደናቂ ጅማሮን ያደረገው እና ከተወሰኑ የጨዋታ ሳምንታት በፊት በፋሲል ከተማ የ100% ያለመሸነፍ ግስጋሴው ከተገታ ወዲህ ሀዲያ ሆሳዕና የቀደመ ተነሳሽነቱን ለማስቀጠል የተቸገረ ይመስላል።
ቡድኑ በፋሲል ከነማ ከተረታበት ጨዋታ ወዲህ ባደረጋቸውን ጨዋታው በአንዱ ብቻ በጠባብ ውጤት ሲያሸንፍ በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።
ሆሳዕና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም እንደ ባለፈው ሁሉ እጅግ ፈታኝ ጨዋታ ሲያሳልፍ ከሰበታ ከተማ ጋር 0-0 ለመለያየት በቅቷል። ነብሮቹ ጨዋታውን አሸንፈው ሊወጡበት የሚችሉትን አጋጣሚ በፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ዳዋ ሆቴሳ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።
በዚህም ቡድኑ ከሽንፈት መልስ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በቀደሙት የጨዋታ ሳምንታት እንደነበረው ለማጥቃት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ ይበልጡኑ ጥንቃቄ ጨምሮ መቅረብን ምርጫው አድርጓል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቹ ያስቆጠረው አንድ ግብ ብቻ መሆኑን እና በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ አስፈሪነቱ እየቀነሰ የመጣው የቡድኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በግልፅ የሚያሳዩት ይህንን እውነታ ነው።
በዚህም ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ቀስ በቀስ እየሰፋ መጥቶ አሁን ላይ ወደ አራት ከፍ ብሏል። ቡድኑ ይህን ልዩነት ለማስቀጠል ብሎም ለማጥበብ በ11ኛው ሳምንት ከጠንካራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ግጋር ብርቱ ፈተና የሚገጥመው ይሆናል።
👉አዳማ ከተማ ከስምንት ጨዋታ በኃላ አሸንፏል
በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐግብር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብጠባቂውን በቀይ ካርድ አጥቶ የሜዳ ላይ ተጫዋችን ለአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በግብ ጠባቂነት የተጠቀመውን ጅማ አባ ጅፋርን ከረቱበት ውጤት ወዲህ ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታ በአንዱ ብቻ የአቻ ወጤት አስመዝግበው በቀሩት ሽንፈት እየገጠማቸው በአራት ነጥብ እና በአስራ አንድ የግብ ዕዳ ወደዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አምርተው ነበር። በዚህኛውም የጨዋታ ሳምንት ከሰሞኑ አስደናቂ ግስጋሴ ላይ የነበረው ሀዋሳ ከተማን እንደመግጠማቸው ወደ ጨዋታው ሁለተኛ የማሸነፍ ዕድልን ይዘው ቢገቡም ግምቶችን አፋልሰው ያልተጠበቀ የ3-1 ድልን ሀዋሳ ከተማ ላይ መቀዳጀት ችለዋል።
ለወትሮው የነበራቸው ጥንካሬ አብሯቸው ያልነበረው ሀዋሳ ከተማዎች ለአዳማ ከተማ አስደናቂ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እጅ ሰጥተዋል። አብዲሳ ጀማል ሐት-ትሪክ በሰራበት ጨዋታ ላለፉት የጨዋታ ሳምንታት በቀላሉ ለተጋጣሚዎች እጅ ይሰጥ የነበረው አዳማ ፍፁም በተለየ የተነሳሽነት መንፈስ አስደናቂ ውጤት ማስመዝግብ ችሏል።
በዚህም ድል ደረጃቸውን ማሻሻል ባይችሉም ነጥባቸውን ወደ ሰባት በማሳደግ ከአናታቸው ከሚገኘው ሰበታ ከተማ ጋር መስተካከል ችለዋል። በቀጣይ የጨዋታ ሳምንትም አዳማ ከተማ እና ሰበታ ከተማ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ጨዋታ በሁለቱ ቡድኖች ደረጃ ላይ የሚፈጥረው ለውጥ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።
👉ወላይታ ድቻ ራሱን እያደላደለ ይገኛል
ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት ቀውስ ውስጥ የነበረው ወላይታ ድቻ በጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ልዩነት ቀስ በቀስ ራሱን በሊጉ እያደላደለ ይገኛል። በ10ኛው የጨዋታ ሳምንት የማሳረጊያ መርሐግብር ጅማ አባ ጅፋርን የገጠመው ቡድኑ 3-1 በሆነ ውጤት በመርታት በማንሰራራት ጉዞው ቀጥሎበታል።
ፈጠን ባለ የማጥቃት ፍላጎት ጨዋታቸውን የጀመሩት ወላይታ ድቻዎች በተጋጣሚ ሳጥን አካባቢ የነበራቸው ደካማ ውጤታማነት ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ አግዷቸው ቢቆይም በ30ኛው ደቂቃ ደጉ ደበበ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠራት ግብ መምራት ችለዋል። በ43ኛው ደቂቃ መላኩ ወልዴ ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት ጎል ቢያስቆጥርባቸውም ድቻዎች ያሉበትን የተነሳሽነት ደረጃ በሚገልፅ መልኩ በመሳይ አገኘሁ የመልሶ ማጥቃት ጎል መሪነታቸውን ወዲያውኑ አስመልሰዋል። በሁለተኛው አጋማሽም የጨዋታው ሚዛን ወደ ጅማዎች ቢያጋድልም በጠንካራ መከላከላቸው አልቀመስ ብለው በመቆየት በአንተነህ ጉግሳ ሌላ የግንባር ጎል ጨምረው በ3-1 ውጤት ዳግም ድል አድርገዋል።
ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የነበረው ቡድን ከአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሹመት ወዲህ ቀስ በቀስ ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት በአሁኑ ሰዓት በከአስር ጨዋታዎች አስር ነጥብ በመሰብሰብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅቷል።
👉የድሬዳዋ ከተማ የተለያዩ ገፅታዎች
ድሬዳዋ ከተማ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማን ገጥሞ 3-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ዓለሙ በሙሉ የሰመረለት ይመስል ነበር። ከወልቂጤው ጨዋታ በፊት አሰልጣኝ ፍሰሀ “አፑስቶ ሆኗል” ሲሉ የገለፁት ቡድኑ አዳማን ሳይቸገር ሲያሸንፍ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣ ዕለትን ማሳለፉ አይዘነጋም።
ታድያ ይሄው ቡድን ከቀናት በኃላ በ10ኛ የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም ደግሞ እጅግ ግራ የተጋባ ቡድን ሆኖ ተመልከትነዋል። በወልቂጤ ከተማ 3-1 በተረቱበት ጨዋታ ሁለቱ ግቦች በግለሰባዊ ስህተቶች መቆጠራቸው ለቡድኑ ውጤት ማጣት በምክንያትነት ቢቀርቡም የቡድኑ አጠቃላይ መዋቅራዊ እንቅስቃሴ ግን በቀደመው የጨዋታ ሳምንት በነበረው ደረጃ ላይ አልነበረም። ታድያ በአዳማ ጨዋታ በተመለከተነው እንቅስቃሴ ተገርመን ሳንጨርስ በቀናት ልዩነት ቡድኑ በዚህ ደረጃ ተዳክሞ መቅረቡ ምን ይባል ይሆን ?
© ሶከር ኢትዮጵያ