ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የዐበይት ጉዳዮች ሦስተኛ ክፍል አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዋና ዋና አስተያየቶች ላይ ያተኩራል።

👉የፍሰሀ ጥዑመልሳን አዝናኝ አስተያየቶች

የርዕሰ ዜናው ሰው ፍሰሀ ጥዑመልሳን በቅድመ እና ድህረ ጨዋታ አስተያየቶቻቸው የሚያነሷቸው ሀሳቦች በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጨዋታ ቀናት በጉጉት ከሚጠበቁ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል።

በዚህኛው ሳምንት በወልቂጤ ከተማ 3-1 ከተረቱበት ጨዋታ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ሰዓት ለማባከን በተደጋጋሚ መውደቃቸውን ለመግለፅ የተጠቁመበት አገላለጽ እጅግ አዝናኝ ነበር።

አሰልጣኙ በንግግራቸው “ከዕረፍት በኃላ ግን እግር ኳስ ሳይሆን ሪፈራል ሆስፒታል ነው የመሰለኝ። መአት ሰው ይተኛል ፣ መአት ሰው ይተኛል ፤ እግር ኳስ እንደዚህ አይደለም።” በማለት የገለፁበት መንገድ ትኩረትን የሳበ ነበር።

👉ቀጣይ ተጋጣሚ አሰልጣኞች በጋራ ጨዋታን መመልከት

በ11ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እርስ በእርስ የሚፋጠጡት የድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከተማ አሰልጣኞች በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማ ያደረጉትን ጨዋታ አብረው በጋራ ተቀምጠው ሲመለከቱ አስተውለናል።

የዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ የውድድር ቅርፅ ሁሉም ተካፋይ ክለቦች መቀመጫቸውን በአንድ ከተማ ማድረጋቸው አሰልጣኞች የእያንዳንዱን ቡድን ጨዋታ በአካል ተገኝተው ለመከታተል የሚያስችል ዕድልን የፈጠረ ሲሆን ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በርካታ አሰልጣኞች በጋራ እና በተናጥል በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ሲመለከቱ ይታያል። ነገር ግን በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት የሚጋጠሙ ሁለት አሰልጣኞች በጋራ ሆነው ጨዋታ ሲመለከቱ ማየት እምብዛም የተለመደ ነገር አይደለም።

👉 አስደናቂ የሰው በሰው መከላከልን የተገበሩት ዘርዓይ ሙሉ

ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች በመከላከል ወቅት የተጠቀሙት የሰው በሰው የመከላከል ዘዴ ትኩረትን የሚስብ ነበር።

በ4-2-3-1 አደራደር የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይ በአጥቂ ስፍራ ላይ ያሏቸውን አስፈሪ ተጫዋቾችን እንዲሁም ሁነኛ የማጥቃት አማራጫቸው የነበረውን ሄኖክ አዱኛን ለመቆጣጠር ሲዳማ ቡናዎች የዘየዱት የመስመር ተመላላሹን በተመስገን በጅሮንድ ፣ የመስመር አጥቂዎቹ አዲስ ግደይ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤልን ደግሞ በአማኑኤል እንዳለ እና ጊት ጋትኮች፣ ጌታነህ ከበደን በሰንደይ ሞቱኩ ፣ አቤል ያለውን ደግሞ በፈቱዲን ጀማል ሰው በሰው በማስያዝ የቅዱስ ጊዮርጊስን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አድርጓቸዋል።

ከእነዚህ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች በተጨማሪ ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች ዮሴፍ ዮሐንስ እና ብርሃኑ አሻሞ በእነዚህ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ላይ ድጋፍ በማድረግ እና ወሳኝ የማጥቃት ሽግግሮችን በማቋረጥ የሲዳማን የጨዋታ ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆን አስችለዋል፡፡ በተለይም ገጊት ጋት በጥልቀት ወደ ራሱ ሜዳ ኳሶችን ለመቀበል ይመጣ የነበረው አማኑኤል ገ/ሚካኤልን እንቅስቃሴ ተከትሎ ያደርገው የነበረው የማቋረጥ ጥረት እንዲሁም ሰንዴይ ሙቱኩ ጌታነህ ጋር ኳስ እንዳይደርስ ያደረገበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነበር።

👉ፋሲል እና ካሣዬ – የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ምስረታ እና የባህርዳር ከተማ ጫና

ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት እና ሁለት ለሁለት በተለያዩበት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች ያስቆጠሯቸው ሁለቱም ጎሎች የተገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው ምዕራፍ የኳስ ምስረታ ወቅት የባህርዳር ከተማ ተጫዋቾች ባሳደረሩባቸው ጫና በፈጠሯቸው የማቀበል ስህተቶች ምክንያት ነበር።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን በሚመሰርቱበት ወቅት በተደጋጋሚ ሁለቱን የመስመር ተከላካዮች በሜዳው ጠርዝ ወደ መሀል ሜዳ አስጠግተው ሲቆሙ፤ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች በግራ እና ቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ለጥጠው የመሀል ተከላካዮቹ ወደ ሳጥኑ ቀረብ ባለ አቋቋም ኳስን ከራሳቸው ሜዳ ለመመስረት ተደጋጋሚ ጥረትን ያደርጋሉ። ታድያ ይህ ሒደት ጫና የማሳደር ፍላጎት ከሌላቸው ተጋጣሚዎች ጋር በቀላሉ ውጤታማ ሲሆን ይስተዋላል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንደተመለከትነው ከፍ ባለ ጀብደኝነት ጫና ፈጥሮ ኳሱን መንጠቅ የሚፈልግ ተጋጣሚ ሲገጥማቸው ግን ሂደቱ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል፡፡ ባህር ዳር ከተማ በዚህኛው ጨዋታ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ በተለይ ኳስ የያዘውን የመሀል ተከላካይ ሲጫን ፍፁም ዓለሙ ደግሞ የተከላካይ አማካዩ አማኑኤል ዮሐንስን የማቀበያ አማራጭ በመዝጋት ጫና ሰፈጥሩ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች በማቀበያ አማራጭ እጦት ኳስን ከግብ ጠባቂያቸው ጋር በድግግሞሽ ሲቀባበሉ ተስተውሏል።

በዚህ ሒደት ግብ ጠባቂው ለመስመር ተከላካዮቹ እንዳያቀብል እነሱም በተጋጣሚ ተጫዋቾች በቅርብ ርቀት ጫና ውስጥ በመግባታቸው ተክለማርያምን ጨምሮ ሁለቱ አማካዮች አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል፡፡ ታድያ ይህንን የጫና ወጥመድ ለማለፍ ኢትዮጵያ ቡናዎች አማራጮችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልተስተዋለም። ይባስ ብሎ ይህ የአማራጭ እጦት ተጫዋቹችን ለስህተት ዳርጎ ቡድኑ ግብ እንዲያስተናግድ ሆኗል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ከግምት ሊገባ የሚገባው ነገር ኳሱ በረጅሙ ተለግቶ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ እንዲደርስ እስካልተደረገ በቀር ኳስን መስርቶ መጫወት የሚያስብ ቡድን ተቀዳሚ አላማው ኳሱ ሳይባክን በቅብብሎች ተመስርቶ ከራሳ የግብ ክልል እንዲወጣ ማድረግ መሆኑ እየታወቀ የምሰረታው ሂደት ለአራት የቡድኑ ተጫዋቾች ተትቶ የተቀሩት ሰባት የቡድኑ አባላት ከዚህ እንቅስቃሴ ተነጥለው መገኘታቸው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ማመዘኑ አይቀሬ መሆኑን የባህርዳሩ ጨዋታ ማሳያ ነው።

በተጨማሪም በኳስ ምሰረታ ለመጫወት የሚያስቡ ቡድኖች ላይ የስድስት ቁጥሩ ጫናን ተቋቁሞ ኳስን የመቀበል እና የማቀበል አቅሙ እጅግ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ምንም እንኳን ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸውን የጫና መጠን በሁለተኛው አጋማሽ በሜዳው የላይኛው ክፍል ለማስቀጠል ቢቸገሩም ሬድዋን ናስር አማኑኤል ዮሐንስን ተክቶ ከገባ ወዲህ የተመለከትነው መሻሻል ለዚህ ማሳያ ነው።

ዓበይት አስተያየቶች

👉ደግአረገ ይግዛው በሁለተኛው አጋማሽ ሳላደጉት ቅያሬ እና ስለመጨረሻዋ ግብ

“ከዚያ በፊትም እንደዚሁ የጨዋታውን መንፈስ ልትቀይር የምትችል ንፁህ የጎል ዕድል አባክነናል። እየመራህ ስትሄድ በድጋሚ ማጥቃቱ ላይ የበለጠ ውጤታማ የሆንክበትን ስራ ማስቀጠል ፣ ይበልጥ ኳሱን ተቆጣጥረህ የምታጠቃ ከሆነ በተዘዋዋሪ መከላከልንም እየሰራህ ነው። እንደሚመራ ቡድን የተከላካይ ባህሪ ያለው ተጫዋች ማስገባት አልፈለግንም። ጫና ለመፍጠር አሁንም ያስገባነው የማጥቃት ባህሪ ያለው ተጫዋች ነው። በአጠቃላይ ቀኑ የእኛ ነበር ማለት እችላለሁ።”

👉ፋሲል ተካልኝ የአጨራረስ ችግሮችን እንደ ድክመት የሚነሱ ከሆነ?

“በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ዕድሎችን በምንፈልገው መልኩ ፈጥረናል ምናልበት እነዛን መጠቀም ብንችል ውጤቱ የተለየ ይሆናል። ነገር ግን ከሁሉም በላይ ቡድኔ የጎል ዕድል መፍጠሩን እንደ ጠንካራ ጎን እመለአከተዋለሁ፡፡ በየጨዋታው ዕድሎችን ፈጥረን መጠቀም አለመቻልችንም ውጤት እንዳናስመዘግብ ተፅዕኖ አሳድሮብናል እዛ ላይ ጠንክረን እንሰራለን።”

👉ካሣዬ አራጌ በመጀመሪያው አጋማሽ ለጎሎቹ መንስኤ ስለሆኑት የቅብብል ስህተቶች እንደ ድክመት የሚታዩ ከሆኑ

“አዎ እንደ ድክመት ነው ፤ ነገርግን እኔ የማየው ነገሩን ማስቀጠል የሚችል ነገር ነበር ወይንስ አልነበረም በሚለው ነው። ነበር ! ስለዚህ አሁንም እዛ ውስጥ ነው የምናርመው ድክመት ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ስህተቶች ሌላኛው የሜዳ ክፍል ላይም ይሰራሉ።ነ ገርግን እዛ ጋር የሚሰሩ ስህተቶች ግን ለጎል የቀረቡ ስለሚሆኑ ተጋጣሚ መሰል ዕድሎችን ሊያገኝ ይችላል። ነገር ግን ስህተቱን ስናርም ቅድሚያ የምናየው ነገር ከእንቅስቃሴው ሳንወጣ ያንን ስህተት እንዳይፈጠር ማድረግ እንችላለን ወይ ነው። ያ መፍትሔ ካለ ግን እዛ ላይ ነው እርምት የምንወስደው።”

👉ማሒር ዴቪድስ ስለ መጫወቻ ሜዳው…

“መጫወቻ ሜዳው ለመጫወት በጣም የሚያስቸግር ነው። ኳስ ለመቀባበል፣ ተጋጣሚ ሳጥን ደርሶ ሙከራ ለማድረግ እና ለመሳሰሉት ሜዳው አስቸጋሪ ነው።”

👉ሙሉጌታ ምህረት ለመስመር ጥቃታቸው መዳከም የአዳማ የመከላከል ብቃት ምክንያት ስለመሆኑ

“አይ አይመስለኝም። ዛሬ ከወትሮው የነበረን እንቅስቃሴ ጥሩ አይደለም። ሙሉ ቡድናችን ትክክል አይደለም። የእሱ ብቻ ሳይሆን የሚገቡትም ልጆችም እንደነሱ ባይሆንም የመሄድ አቅም አላቸው። ግን በጥቅሉ ጨዋታውን ራሱ መቆጣጠር አቅቶናል ዛሬ። ወይ ለክለቡ የሰጠነው ግምትም ሊሆን ይችላል። ያም ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል። ከተጨዋቾቼ ጋር ተነጋግሬ ሜዳ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ቀርፈን እንመጣለን።”

👉 አስቻለው ኃይለሚካኤል ቡድኑ በሚፈልጉት መጠን ስለማጥቃቱ

“አዎ ያየነውም ይሄንን ነው። ሁሉም ቡድን እዚሁ እየተገማገመ ነው ለሚቀጥለው ጨዋታ የሚዘጋጀው። ሀዋሳ ጠንካራ ቡድን ነው ፤ የተሟላ ቡድን ነው። ወጣቶች አብረው የቆዩበት ጥሩ ቡድን ነው። ያንን የእነሱን ጠንካራ ጎን አክሽፈን ውጤታማ የምንሆንበትን ስራ ነው ስንሰራ የነበረው ፤ ያ ተሳክቶልናል። ከዚህ በፊት ጉዳቶችም ነበሩ። አብዲሳ ጉዳት አጥቅቶት የነበረ ተጫዋች ነው ፤ ስገልፅ ነበር በፊትም። ሙሉ ሲሆን ግን ለሀገርም ሀብት ነው ፤ እንደገና ልጅ ነው። ፍሰሀም ልጅ ነው ከታች ነው የመጡት እና ጉዳት ላይ ነበሩ። በፊት የምናገረውም ያን ነበር። ባላን አቅም የምንሰበስባቸው ልጆች ተስፋ ሰጪዎች ናቸው።”

👉ዘላለም ሽፈራው ስላላቸው ስብስብ አቅም እና ቀጣይ የጨዋታ አቀራረቦች

“እንዳለህ አቅም ነው ተጫዋቾችህ ያንን አድርገህ እንድትጫወት የሚፈቅዱ ከሆነ ትጫወታለህ። አሁን ያለን አቅም ይህ ነው ስለዚህ በዚህ መልኩ እየተጫወትን ነው በቀጣይ እንደምናመጣቸው ተጫዋቾች አጨዋወታችን ይወሰናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ