ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ተጠባቂውን የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲህ አንስተናል።

በዘጠነኛው እና አስረኛው ሳምንት ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ሳምንት መክፈቻ ተገናኝተዋል። ፋሲልን ተከትለው ተከታታይ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ሆሳዕና እና ጊዮርጊስ የሚያገናኘው የዚህ ጨዋታ ውጤት ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ከማጥበብ አንፃር ለሁለቱም ወሳኝ ይሆናል።

ሆሳዕና የሊግ አጀማመሩን መንፈስ ዳግም መልሶ ለማግኘት መሰል ትልቅ ጨዋታዎችን በድል መጨረስ ይጠበቅበታል። ይህን ለማድረግ ትልቅ እንቅፋት ሊሆንበት የሚችለው ግን የማጥቃት አቅሙ እየተዳከመ የመሄዱ ጉዳይ ነው። ቡድኑ ጨዋታዎችን ሲጀምር ጥንቃቄ አዘል አቀራረብን ይዞ በመግባት እንደ ጨዋታው ሂደት ቅያሪዎችን አድርጎ ወደ ማጥቃቱ የሚያጋድልበት መንገድም በሰበታው ጨዋታ ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። ይህ የሁለተኛ አጋማሽ የሚታየው መጠነኛ የቡድኑ የማጥቃት ማንሰራራት ከመጀመሪያውም እንዲኖር ግን የተሻለ ድፍረት የተላበሰ አቀራረብን መከተል ያለበት ይመስላል። የአጥቂዎቹ ቀስ በቀስ ከግብ እየራቁ መሄድም በነገው ጨዋታ ለጊዮርጊስ ተከላካዮች ቁጥጥር ቀላል ሊያደርጋቸው ይችላል። በመከላከሉ ረገድ ግን በተቃራኒው ያለውን ጥንካሬ ይዞ እንደቀጠለ ነው። መስመሩን ለሚጠቀሙም ሆነ መሀል ለመሀል በቅብብሎች ላይ ተመስርተው ለሚያጠቁ ቡድኖች የሆሳዕና የኋላ ክፍል የሚቀመስ አልሆነም።

ቅዱስ ጊዮርጊስም እንደተጋጣሚው ሁሉ ግቡን በቀላሉ የማያስደፍር ሆኖ ቢሰነብትም ወደ ግብ የመድረስ አቅሙን እያጣ መጥቷል። በአጥቂነት የሚታወቁ አራት ተጫዋቾቹን በተጠቀመበት የመጨረሻው ጨዋታም ከባድ ሙከራዎችን እንኳን ማድረግ አለመቻሉ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ቡድኑ በዋና የማጥቂያ መንገድነት የሚጠቀምባቸው አማራጮቹ በተጋጣሚዎች ዘንድ ተገማች እየሆኑ መምጣታቸው አንዱ የችግሩ መንስኤ ይመስላል። ነገም አዲስ ዓይነት የማጥቃት አካሄድን ይዞ ካልቀረበ በግብ ፊት ያለውን አስፈሪነት መልሶ ለማግኘት ሊቸገር ይችላል። ጊዮርጊስ ከያዘው ስብስብ አንፃርም ከመስመር ጥቃቱ በተጨማሪ ከመሀል የሚነሱ ኳሶችን በምን አግባብ መጠቀም እንደሚችል አስቦ መቅረብ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ተደጋጋሚ ለውጦች እየተደረገበት ያለው የመሀል ክፍሉ የነገ ተጋጣሙውን የተደራጀ መከላከል ለማስከፈት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው መናገር ይቻላል።

በጨዋታው ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ ከፍ ያለ የማጥቃት ፍላጎት ያለው በጀብደኝነት የተሞላ ቡድን ይዘው እንደሚቀሩቡ ይጠበቃል። በሌላ ወገን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በተለመደው ሁኔታ የተጋጣሚያቸውን አኳኋን እስኪገመግሙ ክፍተቶችን የማይሰጥ ምንአልባትም በሦስት የመሀል ተከላካዮች የሚጀምር የአደራደር ምርጫም ሊኖራቸው ይችላል። ሆሳዕና ከሚያዘወትረው አጨዋወት አንፃር የነበረው ጉልበት ቀንሶ ቢታይም ነገም አማካይ ክፍል ላይ ኃይል የቀላቀለ አካሄድ ሊከተል እንደሚችልም ይታሰባል።

ሀዲያ ሆሳዕና ልምምድ ላይ ጉዳት ያስተናገደው ተስፋዬ አለባቸውን አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል ያለ ሲሆን ከተዘራ አባቴ ሌላ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች ግን አይኖርም። አስቻለው ግርማን በቅጣት ምክንያት የማይጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ጨዋታ በግል ጉዳይ ያልነበረው ሙሉዓለም መስፍን ለዚህ ጨዋታም የማይደርስለት ሲሆን ዛሬ በተሰማው ዜና ደግሞ ሳላዲን ሰዒድ በዲስፕሊን ግድፈት ከቡድኑ ጋር አይገኝም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በ2008 የውድድር ዓመት የተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት የተጠናቀቁ ነበሩ። ጊዮርጊስ ጨዋታዎቹን በተመሳሳይ የ2-0 ውጤት ነበር ያሸነፈው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-4-2)

መሐመድ ሙንታሪ

ሱለይማን ሀሚድ – ኢሴንዴ አይዛክ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

ቢስማርክ አፒያ –ተስፋዬ አለባቸው – አማኑኤል ጎበና – መድሀኔ ብርሀኔ

ሳሊፉ ፎፋና – ዳዋ ሆቴሳ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ደስታ ደሙ – አማኑኤል ተርፋ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ናትናኤል ዘለቀ

ጋዲሳ መብራቴ – ሮቢን ንጋላንዴ – አቤል ያለው

ጌታነህ ከበደ
© ሶከር ኢትዮጵያ