ሪፖርት | ጅማ እና ባህር ዳር ነጥብ ተጋርተዋል

አራት ግቦች በታዩበት ድንቅ የመጀመሪያ አጋማሽ ባስመለከተን ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር እና ባህር ዳር ከተማ 2-2 ተለያይተዋል።

ባህር ዳር ከተማ ነጥብ ከተጋራበት የቡናው ጨዋታ ወሰኑ ዓሊ እና በረከት ጥጋቡን ወደ አሰላለፍ በማምጣት ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ግርማ ዲሳሳን አሳርፏል። ጅማዎች ደግሞ ከድቻው ሽንፈት ውስጥ ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜን በአቡበከር ኑሪ ሲተኩ ሳዲቅ ሴቾ ፣ ሮባ ወርቁ እና ውብሸት ዓለማየሁ ደግሞ በቤካም አብደላ ፣ ሙሉቀን ታሪኩ እና ብዙዓየሁ እንዳሻው ቦታ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከጨዋታው በፊት የከተማው ከንቲባ አቶ ቲጃኒ ናስር በመልበሻ ክፍል የጎበኟቸው ጅማ አባ ጅፋሮች በጎሎች በታጀበው አጋማሽ ላይ ድንቅ አጀማመር ማድረግ ችለዋል። ከጅምሩ መላኩ ወልዴ በቅጣት ምት እና ከማዕዘን በመጣ የግንባር ኳስ ያደረጋቸው ከባድ ሙከራዎች በፂዮን መርዕድ ጥረት ነበር ግብ ከመሆን የዳኑት። 14ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተመስገን ደረሰ በቀኝ በኩል ከወንድምአገኝ ማርቆስ የእጅ ውርወራ ያገኘውን ኳስ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ በመግባት ከመስመር ተከላካይነት ወደ አጥቂነት መመለሱን የሚያበስር ጎል ከመረብ አገናኝቷል።

እጅግ በተቀዛቀዘ መንፈስ ጨዋታውን የጀመሩት ባህር ዳሮች ከተመሩ በኃላ መነቃቃትን ያሳዩ ሲሆን አቻ ለመሆንም ሦስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር ያስፈለጓቸው። የጨዋታ ውጪ አቋቋሙን በማሳመር የአህመድ ረሺድን ረጅም ኳስ እየነዳ ግብ ላይ የደረሰው ፍፁም ዓለሙ በድንቅ አጨራረስ ጨዋታውን ወደ 1-1 አምጥቷታል።

ከአቻነት ጎሉ በኃላ የጅማ የኋላ መስመር እጅግ የተዘበራረቀ አቋቋም የባህር ዳሮች ቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶችን አደገኝነት እያጎላው ሄዷል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ሳላምላክ ተገኘ ከቀኝ መስመር ሲያሻማም ምንይሉ ወንድሙ ያለምንም ጫና በተከላካዮች ፊት ሆኖ በግንባሩ አስቆጥሯል። ባህር ዳሮች በቀጣይ ደቂቃዎች ግብ አፋፍ የደረሱበት ሌላ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚም በአፈወርቅ ኃይሉ ወደ ግብ ሊለወጥ ተቃርቦ ነበር። ከዛ ግን ኳስ ወደ መያዙ እና ጨዋታውን ወደ ማረጋጋቱ ባመዘኑበት ሰዓት ላይ በረጅሙ ወደ ሳጥን የተላከውን የሱራፌል ዓወልን ኳስ ከሳሙኤል ተስፋዬ ጋር በመታገል እና ተረጋግቶ በመቆጣጠር ተመስገን ደረስ ሌላ አስገራሚ ጎል አስቆጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ ተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶችን ሲያገኙ የነበሩ ጅማዎች በመላኩ ወልዴ ድንቅ የርቀት ቅጣት ምት ሌላ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ፂዮን መርዕድ በድጋሚ አድኖባቸዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዞ ሲጀምር ባህር ዳር ከተማ ኳስ በመያዝ እና ክፍተቶችን በመፈለግ ጅማ ደግሞ በራሱ ሜዳ ላይ ቆይቶ ጥንቃቄን በመምረት ተንቀሳቅሰዋል። በመጀመሪያው ከባድ ሙከራም 56ኛው ደቂቃ ላይ ወሰኑ ዓሊ መናፍ ዓወል በረጅሙ ያደረሰውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ተከላካዮችን ጥሎ ወደ ግብ የላከው ኳስ በአቡበከር ኑሪ ጥረት ለጥቂት ድኖበታል።

የጨዋታ ብልጫን ቢይዙም በቅብብሎች በደፊት መድረስ ቀላል ያልሆነላቸው ባህር ዳሮች ለቀጥተኛ ጨዋታ አመዝነው ታይተዋል። በቀጣዩ ሙከራም 67ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ከማዕዘን በተነሳ እና በምንይሉ የተሞከረውን ኳስ ከቅርብ ርቀር አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ጅማ አባ ጅፋሮች በመከላከል ወቅት የነበረባቸውን ደካማ አደረጃጀት ቀንሰው ወደ ሜዳ ቢመለሱም ከተጋጣሚ ግብ ርቀው ቆይተዋል። ከዕረፍት መልስ ቀዳሚ ሙከራ ሲያረጉም 71ኛው ደቂቃ ላይ መላኩ ወልዴ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የላከው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። የባህር ዳርን የማጥቃት ጉልበት ቀስ በቀስ እያዳከሙ የመጡት ጅማዎች ተቀይረው በገቡት ጀይላን ከማል ፣ ቤካም አብደላ እና ብዙአየሁ እንዳሻው አማካይነት ሙራዎችን በማድረግ ከፍ ያለ ተነሳሽነት አሳይተው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥረው ነበር።

79ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ዲሳሳ ከግራ መስመር ቅጣት ምት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ካረጉ በኃላ የተቀዛቀዙት ባህር ዳሮች ግን ተዳክመው ታይተዋል። በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ያገኙትን ያለቀለት ዕድልም በሙኪያስ ግርማ ሙከራ አባክነው ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።

©ሶከር ኢትዮጵያ