ሪፖርት | ድል ፊቷን ወደ ሰበታ መልሳለች

በዛሬው ሁለተኛ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ከሰባት ሳምንታት በኃላ አዳማ ከተማን 1-0 ያሸነፈበትን ውጤት አስመዝግቧል።

አዳማ ከተማ ሀዋሳን በረታበት ስብስብ ላይ ለውጥ ሳያደርግ ጨዋታውን ሲጀምር በተቃራኒው ሰበታ ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ስድስት ለውጥ አድርጓል። በዚህም ከጉዳት የተመለሱትን ዳዊት እስጢፋኖስ እና ታደለ መንገሻን ጨምሮ ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ቃልኪዳን ዘላለም ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ እና ፍፁም ገብረማርያም ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ መጥተዋል።

ሰበታ ከተማ በከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ክፍተቶችን ሲፈልግ አዳማ ከተማ ደግሞ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ሲጠብቅ ያለቀው የመጀመሪያ አጋማሽ ቀዝቃዛ ነበር። 16ኛው እና 28ኛው ደቂቃዎች ላይ ፍፁም ገብረማርያም ከሳጥን ውስጥ ያደረጋቸው ሙከራዎች የመጀመሪያው በግቡ አግዳሚ ሲመለስ ሌላኛው ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ ሰበታዎች ከሳጥን ውስጥ የፈጠራቸው ዕድሎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ሰበታዎች በግብ ፊት ቶሎ ውሳኔ መስጠት አለመቻላቸው ከሙከራ አርቋቸዋል።

ተጋጣሚያቸውን በአግባቡ መቆጣጠር የቻሉት አዳማዎችም የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚን መፍጠር ቸግሯቸው ቆይተው 39ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድል አግኝተዋል። ታፈሰ ሰርካ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን ያደረሰውን ኳስ አብዲሳ ጀማል ቢሞክርም ምንተስኖት ዓሎ እንደምንም አውጥቶበታል። ሰበታዎችም በታሪክ ጌትነት ተመለሰባቸው እንጂ ጨዋታው ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት ፍፁም በግል ጥረቱ በፈጠረው ዕድል መነሻነት በአንዱልሀቪዝ ቶፊቅ የሳጥን ውስጥ ሙከራ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር።

ከዕረፍት መልስ ሰበታዎች የግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ዱራሳ ሹቢሳ እና ታደለ መንገሻ አከታትለው በሞከሯቸው ኳሶችም ወደ ግብ በመድረሱ በኩል ተሻሽለው ቀርበዋል። ከዕረፍት በኃላ ተፅዕኖው የጨመረው ዳዊት እስጢፋኖስ በመቻቻቸው ኳሶች 51ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውስጥ በተገኙት ዕድሎች ቀዳሚውን ዱራሳ ሞክሮ በታሪክ ሲመለስ ሁለተኛውን ፍፁም ወደ ላይ ልኮታል። ዳዊት 64ኛው ደቂቃ ላይም ከቅጣት ምት ባረገው ሙከራ ታሪክን መፈተን ችሎ ነበር።

በአንፃሩ አዳማዎች ከመልሶ ማጥቃት ሲጠብቋቸው የነበሯቸው ዕድሎች ዘግይተውም ቢሆን መታየት ጀምረው ነበር። 72ኛው ደቂቃ አብዲሳ ጀማል በቃሉ ገነነ ካቀበለው ኳስ ጥሩ ዕድል ቢያገኝም ሙከራው በምንተስኖር ዓሎ ድኖበታል። አጥቂው ከደቂቃ በኃላ ሌላ የመልሶ ማጥቃት ዕድል ቢደርሰውም ለበቃሉ አመቻቻለው ብሎ አባክኖታል።

በቀጣይ ደቂቃዎች ቡልቻ ሹራ እና ኢብራሂም ከድርን ቀይረው በማስገባት ይበልጥ ጫና የፈጠሩት ሰበታዎች በለስ ቀንቷቸዋል። 78ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ጌቻሞ ኢብራሂም ከድር ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ ወደ ግብነት ለውጦታል። በቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታው ቢቀዛቀዝም ሰበታዎች የአዳማን አቻ የመሆን ጥረት ተቆጣጥረው ጨዋታውን ማሸነፍ ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ