ነገ ረፋድ ላይ በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።
ይህ ጨዋታ በሳምንቱ ተመጣጣኝ ፉክክር ሊያስመለክቱን ይችላሉ ተብለው ከተጠበቁት ጨዋታዎች ውስጥ ይካተታል።
ወልቂጤ ከተማ ከሦስት እና አራተኛው ሳምንት በኋላ ተከታታይ ድል በማስዝመዝገብ ወደ ላይኛው ፉክክር ለመጠጋት ወደ ሜዳ ይገባል። በተቀያያሪ አቀራረብ ጠንካራ ተጋጣሚዎችን ውጤት በመቀማት እዚህ የደረሰው ወልቂጤ ነገም የአቀራረርብ ለውጥ አድርጎ ልናየው እንችላለን። አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በድሬዳዋው ጨዋታ በጉዳት በሳሳው ቡድናቸው ላይ ያደረጉት አስገሳጅ ቅያሪ ውጤቱ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ በራሱ ቡድኑ ለተለዋዋጭነት የሚሰጠውን ምላሽ የሚያሳይ ነው። ነገም በይበልጥ ድክመት የተስተዋለበትን የተጋጣሚያቸውን የመስመር ላይ መከላከል ለመጠቀም አልመው ሊገቡ የሚችሉቡት ዕድል ይኖራል።
በድሬዳዋው ጨዋታ እንደ አሜ መሀመድ እና አቡበከር ሳኒ ዓይነት ተጫዋቾች ያሳዩት አቋም ቡድኑ ያሉትን አማራጮች የሚያሰፋለት ነው። በሄኖክ አየለ ላይ ተመርኩዞ የነበረው የግብ ማስቆጠር ኃላፊነትም በእነዚህ ተጫዋቾች እገዛን ያገኘ መስሏል። በመከላከሉ ረገድ ሰራተኞቹ ይዘውት የመጡት ጥንካሬ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደ ሁለተኛ ቡድን የሚያደርጋቸው መሆኑም የተጋጣሚያቸውን የፊት መስመር የመቆጣጠር አቅም ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠቁማል። ይህም ከመስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ የሚገጥማቸውን ፍልሚያ ከወዲሁ ተጠባቂ ያደርገዋል።
በወልቂጤ ከተማ ስብስብ ውስጥ በኃይሉ ተሻገር ፣ አሳሪ አልመሀዲ ፣ ስዩም ተስፋዬ እና ፍሬው ሰለሞን አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ሀብታሙ ሸዋለም ፣ ተስፋዬ ነጋሽ እና ሙኸጅር መኪ ደግሞ ቡድኑን ለማገልገል ብቁ ሆነዋል።
ከስድስት ጨዋታ በኋላ ያልተጠበቀ ሽንፈት የገጠማቸው ሀዋሳ ከተማዎች ነጥቦችን ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ወርዶ መገኘት አስገራሚ ነበር። በአስገዳጅ እና በሌሎች ምክንያቶች በአማካይ ክፍሉ ላይ ሁለት ቅያሪዎችን እንዲሁም የቀኝ መስመር ተከላካዩን ቀይሮ የገባው ቡድኑ ጥንካሬው የነበረውን የመስመር ጥቃት ከማጣቱም በላይ ራሱን በመስመር ከሚመጡ ጥቃቶች መከላከልም አቅቶት ነበር። ይህ ችግር በነገው ጨዋታ ላይም የሚደገም ከሆነ ወልቂጤ ተመሳሳይ ድክመት ከነበረበት ድሬዳዋ ጋር ካሳየው አቋም አንፃር ሀዋሳን ችግር ውስጥ የሚከት ነው።
ሀዋሳ ከኋላ ጥንቃቄ አዘል አቀራረብ የነበረውን የአዳማን የተከላካይ ክፍል ማስከፈት ተስኖት መታየቱም ከወልቂጤ የኋላ ክፍል ጥንካሬ አንፃር ሲመዘን ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ይሆንበታል። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድኑ ከነበረበት የአሸናፊነት መንፈስ እንዳይወጣ ውጤቱን አጥብቀው የሚፈልጉት በመሆኑ ራሱን ለመልሶ ጥቃት ያማያጋልጥ ግን ደግሞ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲገባ በቶሎ ክፍተቶችን የማግኘት አቅም የነበረውን ቡድናቸውን መልሰው ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ለማድረግ ከአሸናፊው ቡድናቸው ላይ የሚኖሩ የጉዳት ክፍተቶችን በጥንቃቄ የመድፈን እና የቡድኑን የሜዳ ላይ የጨዋታ ትኩረት ከፍ እንዲል የማድረግ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
ሀዋሳ ከተማ ወሳኙን የመስመር ተከላካይ ደስታ ዮሃንስ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ እና ሀብታሙ መኮንን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን የዳንኤል ደርቤ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ መድረስም አጠራጣሪ ሆኗል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
በተሰረዘው የውድድር ዓመት ሀዋሳ ከተማ 3-1 ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ቡድኖቹ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወልቂጤ ከተማ (4-2-3-1)
ጀማል ጣሰው
ተስፋዬ ነጋሽ – ቶማስ ስምረቱ – ዳግም ንጉሤ – ረመዳን የሱፍ
ተስፋዬ መላኩ – ሀብታሙ ሸዋለም
አቡበከር ሳኒ – አብዱልከሪም ወርቁ – አሜ መሐመድ
ሄኖክ አየለ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
ሶሆሆ ሜንሳህ
ዘነበ ከድር – ምኞት ደበበ – ላውረንስ ላርቴ –ዮሐንስ ሰገቦ
ኤፍሬም ዘካርያስ – ጋብሬል አህመድ – ወንድምአገኝ ኃይሉ
ኤፍሬም አሻሞ – መስፍን ታፈሰ – ብሩክ በየነ
© ሶከር ኢትዮጵያ