ሪፖርት | ወልቂጤ እና ሀዋሳ ነጥብ ተጋርተዋል

በዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ያለግብ ተለያይተዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከጉዳት የተመለሱት ተስፋዬ ነጋሽ እና ሀብታሙ ሸዋለም እንዲሁም አሜ መሀመድን በአሳሪ አልመሀዲ ፣ ስዩም ተስፋዬ እና ያሬድ ታደሰ ምትክ ተጠቅሞ ጨዋታውን አድርጓል። ሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ ጋብሪል አህመድ እና ሄኖክ ድልቢ ከአሰላለፍ ሲወጡ ከጉዳት የተመለሱት ዳንኤል ደርቤ ፣ ዳዊት ታደሰ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ እና ዘነበ ከድር ጨዋታውን ጀምረዋል።

በርከት ያሉ ጥፋቶችን ያስተናገደው የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ነበር። መሀል ሜዳ ላይ በነበረው ከፍተኛ ፍልሚያ አንዳቸው የሌላኛቸውን የማጥቃት ሂደት እያቋረጡ አብዛኛውን ጊዜ ቢያሳልፉም ወደ ግብ በመድረሱ በኩል ወልቂጤዎች የተሻሉ ነበሩ። 4ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ለአሜ መሀመድ ካሾለከለትን እና አሜ ከሳተው ኳስ በኋላ በ34ኛው እና 43ኛው ደቂቃ ላይ በንክኪዎች ሳጥን ውስጥ መድረስ ችለው የነበሩት ወልቂጤዎች በሀዋሳ ተከላካዮች ጥረቶቻቸው ከሽፈዋል።

ከዚህ ውጪ የሀብታሙ ሸዋለም የ29ኛ ደቂቃ የቅጣት ምት ሙከራ የቡድኑም የጨዋታውም የአጋማሹ ብቸኛ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሆኖ ተመዝግቧል። የነበረውን ፍትጊያ አልፈው ሳጥን ውስጥ መገኘት የከበዳቸው ሀዋሳዎች ወደ ቀኝ አድልተው ጥቃት ለመሰንዘር ቢሞክሩም በወንድምአገኝ ኃይሉ እና ዳዊት ታደሰ ካደረጓቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ የሳጥን ውጪ ሙከራዎች ውጪ ሌላ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ መሀል ሜዳ ላይ የነበረው ፍትጊያ ቀነስ ብሎ አልፎ አልፎ ቀጥተኛ ኳሶችን እያሳየን ጀምሯል። በተለይም ሀዋሳ ወደዚህ የጨዋታ መንገድ ያደላ ሲሆን 50ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ከማዕዘን ምት በመጣ ኳስ ካደረገው የግንባር ሙከራ በኃላ ግን ወደ ግብ መድረስ ቀላል አልሆነለትም። ወልቂጤዎች በአንፃሩ 63ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ሸዋለምን በያሬድ ታደሰ ቀይረው ካስገቡ በኋላ የአደራደር ረውጥ በማድረግ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ኖሯቸው ወደ ፊት ገፍተው ሲጫወቱ ታይተዋል።

ከወልቂጤ የማጥቃት ጫና አንፃር የመልሶ ማጥቃት ዕድልን ሲጠብቁ የነበሩት ሀዋሳዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ከተጣለ እና ብሩክ በየነ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ ያረጉት ሁለተናው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራቸው በጀማል ጣሰው ድኗል። ከዚህ በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ቡድኖቹ የተጫዋቾች ለውጦችን በማድረግ ግብ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጎሎችን ያመለክታል ተብሎ የተተበቀው ጨዋታው ያለግብ ፍፃሜውን አግኝቷል።