ከሱፐር ስፖርት ጋር የነበረው የሁለቱ አሰልጣኞች ቆይታ ይህንን ይመስላል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ
በጨዋታው ጥፋቶች ስለመበራከታቸው
ጨዋታው ጠንካራ ጨዋታ ነው። በሁለታችንም በኩል ሦስት ነጥብ ይዞ ለማውጣት ልጆቹ ሜዳ ላይ የሚያደርጉት ተጋድሎ እጅግ አስደሳች ነበር። እንደነበረን የጨዋታ እንቅስቃሴ ሦስት ነጥብ ይዘን መውጣት ይገባን ነበር። ሆኖም ግን ተጋጣሚያችን ሀዋሳም ጠንካራ ቡድን ነው ፤ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ግን ይዘነው የገባነውን ታክቲክ ልጆቻችን ለመተግበር የሄዱበት ርቀት እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው የነበረው። በኮሪደሮቹ ላይ የመጫወቻ ቦታ በማሳጣት እኛ ኳሶችን ስናገኝ ደግሞ በፈጣን ሽግግር ለመሄድ ነበር ጥረት ስናደርግ የነበረው። ሆኖም ግን በጎል ሊታጀብ አልቻለም ድካማችን። በተረፈ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር።
ስለያሬድ ቅያሪ እና ወደ 4-3-3 ስለተደረገው የአደራደር ለውጥ
ይበልጥ ለማጥቃት ነው ፤ ጨዋታውን እያነበብነው ስለነበር ቶሎ ቶሎ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ። ከዛም ባሻገር ደግሞ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ነበር የሞከርነው። ያሰብነው ተሳክቷል ማለት ይቻላል። ነገር ግን ለጎል ካላቸው ጉጉት የተነሳ ሦስተኛውን ሜዳ በተቀናጀ መልኩ በተረጋጋ ሁኔታ ወደ ጎል የመቅረብ ችግር ይታይብናል። ይሄንን ደግሞ በቀጣይ ጊዜያት እየቀረፍን አሻሽለን ለመምጣት እንሞክራለን።
የተጨዋቾች ጉዳት ስለፈጠረው ተፅዕኖ
ብዙ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች በጉዳት ነው ያሉት። ሆኖም ግን የገቡትም ልጆች በራሳቸው መንገድ ተንቀሳቅሰው ለመውጣት ነው የሞከሩት። አጠቃላይ እንደቡድን የነበረው ጨዋታ የሚያስከፋ አልነበረም። ምንአልባት የሚያስከፋ ነገር ካለ ሦስት ነጥብ ይዘን አለመውጣታችን ነው። በተረፈ ግን ልጆቻችን የነበራቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና የመጫወት ፍላጎት በጣም ደስ የሚል ነው ፤ ደስተኛ ነኝ።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ
ቡድኑ ከሙከራዎች ስለመራቁ
ከሽንፈት ስለመጣን ይሄን ለመያዝ ትልቅ ፍላጎት ስለነበር ችኮላዎችም አሉ። መስራት የሚገባንን ነገር ለማድረግ በቀላሉ እየቻልን ወደ ሌሎች ነገሮች ውስጥ እየገባን ስኬታማ አልሆንም ሙከራዎቹ ላይ። ግን ያው ጅማ በቆየንባቸው ጊዜያቶች ጥሩ ስለነበር የዛሬዋን ደግሞ አሸንፈን በጥንቃቄ ለመውጣት ስልነበር ያም ይመስለኛል ፤ ችኮላ እና ጉጉት ይመስለኛል እንዳንደራጅ ያደረገን እና ሙከራ ያላደረግንበት ምክንያት።
ስለመስመር ተጫዋቾቹ የዕለቱ ብቃት
በእርግጥ እኛ ሁሌም መስመሩን ለመጠቀም እንጥራለን። ክለቦች ግን ትኩረት አድርገው የሚመጡት እነዛ ልጆች ላይ ነው። ጨዋታው እንደውም ብዙ ፋዎሎች አሉት። ዳኞች እንደውም የሚያልፏቸው ነገሮች አሉ ፤ ጥሩ ነው። ያ ይመስለኛል እኔ። ያው አንድ ቡድን የአንድን ቡድን ደካማ ጎን አይቶ ነው የራሱን የሚሰራው። ዛሬ ደስታ ቢኖር ጥሩ ነበር ፤ ዘነበ ግን ሸፍኖታል። እንደበፊቱ እንደደስታ ኳሶች ወደ ፊት ባይወርዱም ጥንቃቄ የመረጥነው አሸንፈን ለመሄድ ነበር። ያም ሆኖ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ቆንጆ ነው ብዬ ነው የማስበው።