ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

የጅማ ቆይታ የተጠናቀቀበት የአስራ አንደኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ተመርኩዘን ክለብ ተኮር ጉዳዮችን አንስተናል።

👉ዐፄዎቹን የሚያቆም አልተገኘም

በ11ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን በገጠመበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የማሳረጊያ ጨዋታ በበዛብህ መለዮ እና በረከት ደስታ ግቦች 2-0 በመርታት የጅማ ቆይታውን በ100% የማሸነፍ ግስጋሴ ደምድሟል።

ገና ከጅምሩ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን ማጥቃት ላይ በማድረግ ወደ ጨዋታው የገቡት ፋሲል ከነማዎች ከነበራቸው ከፍተኛ ግብ የማስቆጠር ጉጉት የተነሳ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ቅርፅ አልይዝ ብሏቸው ከሙከራዎችም ርቀው ቆይተው ነበር።

ነገር ግን የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ቡድኑን ወደ መረጋጋት የመለሰች ጎል ሲያስቆጥር ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ደግሞ በረከት ደስታ በፋሲል ማልያ የመጀመሪያው የሆነውን ጎል ከመረብ በማሳረፍ ልዩነቱን አስፍቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ፋሲል ይበልጥ ተረጋግቶ ለወጣት ተጫዋቾቹ ዕድልን በመስጠት ጭምር ጨዋታውን ፈፅሟል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ላይ ያስመዘገበውን ድል ተከትሎ ፋሲል ከነማ በአስር ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ሠላሳ ነጥብ ውስጥ ሃያ አምስቱን በማሳካት ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና በአምስት ነጥብ ልቆ በመቀመጥ መሪነቱን አስቀጥሏል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ በጨዋታዎቹ አንድም ጊዜ መረቡን አላስደፈረም።

👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ እንቆቅልሽ

በ11ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ በነበረው የሳምንቱ መርሐ ግብር ጫና ውስጥ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አንድ ለአንድ ተለያይተዋል።

ጨዋታውንም ከመካሄዱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወሳል። በዚህም አሰልጣኙ ማሒር ዴቪድስ በአስቸኳይ የቡድኑን ውጤት እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የቡድኑን አጥቂ ሳልሀዲን ሰዒድ ደግሞ በዲሲፕሊን ግድፈት ከዋናው ቡድን ተነጥሎ ከተስፋ ቡድኑ ጋር ልምምድ እንዲሰራ ተወስኗል።

ይህን ተከትሎ በቀናት ልዩነት ሀዲያ ሆሳዕናን የገጠሙበት ጨዋታ በብዙዎች ዘንድ ከወትሮው በተለየ ትኩረት የተጠበቀ ነበር። በጨዋታውም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን የገጠሙበትን እና አራት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ያጣመረውን ፍፁም ማጥቃትን ምርጫው ያደረገ የተጫዋቾችን ምርጫ ይዘው ቢገቡም ዕድሎችን ከክፍት ጨዋታም ሆነ ከቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶች በመፍጠር ረገድ ተዳክመው ታይተዋል፡፡

በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ የኳስ ቁጥጥርን በሁለቱም አጋማሾች መውሰድ የቻሉት ጊዮርጊሶች በተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ ጉዳት መነሻነት ይበልጥ ለማጥቃት የሚረዳ የአደራደር ለውጥ ቢያደርጉም በዳዋ ሆቴሳ ጎል የተመሩበትን ጨዋታ በሄኖክ አዱኛ ጎል አካክሰው ከመውጣት ያለፈ ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኮስታራ የዋንጫ ቡድን ይመስሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስች ቀስ በቀስ ውጤት ማስመዝገብ ተስኗቸዋል። በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የተሳነው ቡድኑ ከሚጠበቅበት ዘጠኝ ነጥብ ሦስቱን ብቻ አሳክቶ ወደ አራተኛ ደረጃ ተንሸራቷል።

👉ከሜዳ ውጪ ያሉ ችግሮች ሀዲያ ሆሳዕና ላይ የፈጠሩት ተፅዕኖ

ከጠንካራ አጀማመሩ ማግስት ቀስ በቀስ የመቀዛቀዝ ምልክቶችን እያሳየ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

በአቀራረብ ደረጃ ከሰሞኑ አሉታዊነት በተወሰኑ መልኩ ለቀቅ ያለ አቀራረብን ይዘው በገቡበት ጨዋታ ሜዳ ላይ ከነበሩት ሁነቶች ይልቅ በአሰልጣኝ አሸናፊ የቅድመ ጨዋታ አስተያየትም ጭምር የተጠቆመው የክለቡ የሜዳ ውጪ ችግር ትኩረት ስቧል።

የሀገራችን የእግር ኳስ ክለቦች ክፉኛ እያጠቃ የሚገኘው የፋይናንስ እጥረት አዲሱ ሰለባ ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕና ሳይሆን አልቀረም። በ10ኛው የጨዋታ ሳምንት ሰበታ ከተማን ገጥመው 0-0 ከተለያዩ ወዲህ እስከ ቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ድረስ ምንም ዓይነት ልምምድ ሳይሰሩ ጨዋታውን ለማድረግ መገደዳቸውን አሰልጣኙ አሸናፊ ተናግረዋል።

ታድያ ያለ ልምምድ ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው ቡድኑ ሦስት ተከታታይ አቻውን ሲያስመዘግብ ከሜዳ ውጪ እየተፈጠሩ የሚገኙት ችግሮች በቡድኑ ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ መሆናቸው እየታየ ይገኛል። ትናንት በተሰማው ሌላ ዜና ደግሞ ክለቡ ከቀድሞው ተጫዋቹ አብዱልሰመድ ዓሊ ጋር የገባበት ውዝግብ ወደ ክስ አምርቶ ከፌዴሬሽኑ የዕግድ ውሳኔ እንዲተላለፍበት ምክንያት ሆኗል፡፡

👉አስደናቂው ኢትዮጵያ ቡና

በካሳዬ አራጌ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የተንገራገጨ የውድድር ዘመን ጉዞ እያደረገ የሚገኘውን ሲዳማ ቡናን አምስት ለባዶ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ አስደናቂ ውጤትን አስመዝግቧል።

ጥሩ ፉክክር ካስተናገደው እና ያለግብ ከተጠናቀቀው የመጀመሪያ አጋማሽ መልስ ሲዳማዎች ነቃ ብለው ቢጀምሩም በመከላከሉ ረገድ የነበራቸውን ትኩረት ማጣት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሳይራሩ ተጠቅመውበታል። ቡድኑ ወደ ግራ ባመዘነ ጥቃት ወደ ተጋጣሚው ሳጥን ከተጠጋባቸው አጋጣሚዎች ብዙዎቹን ወደ ውጤት ቀይሮም ሁለተኛውን አጋማሽ በግቦች የተንበሸበሸ አድርጎታል፡፡

አቡበከር ናስር ሐት-ትሪክ በሰራበት እና አሥራት ቱንጆ ድንቅ ብቃቱን ባሳየበት በዚሁ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና አምስት ግቦችን አስቆጥሮ ምንም ግብ ሳያስተናግድ አስደናቂ የጨዋታ ዕለት አሳልፏል። ቡድኑ ዘንድሮ መረቡን ሳያስደፍር ሲወጣ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።

👉የባህር ዳር በጨዋታዎች መሀል መቀዛቀዝ

የቡድኖች የወጥነት ችግር በሀገራችን እግርኳስ እጅግ ከመለመዱ የተነሳ ብዙም ሲያስገርም አይስተዋልም። ነገር ግን እንደ ባህርዳር ከተማ በአሰልጣኝ እና በስብስብ ጥራት ረገድ ከፍ ያለ ግምት በሚሰጣቸው ቡድኖች ላይ ሲሆን የተለየ ትኩረት የሚሻ ነው።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ከሚገኙ አስደናቂ ቡድኖች መካከል የሚያስመድበውን እንቅስቃሴ ቢያስመለክተንም ይህን አስደናቂነቱን ከጨዋታ ጨዋታ ማስቀጠል ላይ ችግሮች እንዳሉበት በተደጋጋሚ እየተስዋለ ይገኛል።

ቡድኑ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ሲጀመር ጨዋታዎች ሲያደርግ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከፍ ባለ ፍላጎት ወደ ጨዋታዎች በመቅረብ የቤት ሥራውን በመጀመሪያው አጋማሽ በመጨረስ የጨዋታ ውጤቶችን ለመወሰን ይታትራል፡፡ ይህም ቢሆን የሚታይበትን ታታሪነት ለ90 ደቂቃ ለማስቀጠል በተደጋጋሚ ሲከብደው እና ውጤቱን አሳልፎ ለመስጠት ሲገደድ ይስተዋላል።

ይህ ሂደት በቅርብ ጊዜ እንኳን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 2-2 በተለያዩበት ጨዋታ የተስተዋለ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በተመሳሳይ ሁለት አቻ ሲለያዩም ጨዋታውን የጀመሩበት እንዲሁም ጨዋታውን ከመሩባቸው ሁለት አጋጣሚዎች በኃላ በነበሩት የጨዋታ ጊዜያት ቡድኑ በሚያስገርም መልኩ ተቀዛቅዞ ተመልክተናል።

👉የጅማ አባ ጅፋር ተነሳሽነት

በሊጉ ደካማ አጀማመርን አድርጎ በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ካደረጋቸው ጨዋታዎች ከፍ ባለ ተነሳሽነት ባደረገው ጨዋታ ከባህርዳር ከተማ ጋር ድንቅ እንቅስቃሴን ባየንበት የመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ አራት ግቦች ሁለት አቻ ተለያይቷል።

የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የሆኑት አቶ ቲጃኒ ናስር ከጨዋታው መጀመር አስቀድመው ወደ ውጤት ለመመለስ አንዳች ማነቃቂያ የሚፈልግ የሚመስለውን የጅማ አባ ጅፋር ቡድኑን አባላትን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተው ባበረታቱበት እና በስታድየም ተገኝተው በታደሙት በዚሁ ጨዋታ ጅማዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ አጀማመር አድርገዋል፡፡ በተመስገን ደረሰ ግብ መሪ የነበሩት ጅማዎች በተጋጣሚያቸው በተከታታይ ሁለት ግቦችን በተከላካዮቻቸው የተዘበራረቀ አቋቋም ለማስተናገድ ቢገደዱም የዕለቱ ሰው የነበረው ተመስገን ደረሰ ዳግም የአቻነቷን ግብ አስቆጥሮ ቡድኑ ነጥብ እንዲጋራ አሰችሏል።

ጅማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጥንቃቄ ላይ ቢያተኩሩም ወደ ጨዋታው ማበቂያ ላይም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ያሉ በማይመስል መልኩ በርትተው ሙሉ ነጥብ ለመውሰድ ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በአራት ነጥብ በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ቡድኑ ይህን መነሳሳት በሌሎች ጨዋታዎች በማስቀጠል ራሱን ከወራጅ ቀጠና ለማላቀቅ መጣር ይኖርበታል፡፡



👉የሰበታ ወደ ድል መመለስ እና በመሻሻል መቀጠል

የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያፍር የነበረው ሰበታ ከተማ መሻሻሉን ባስቀጠለበት ጨዋታ ከረጅም የጨዋታ ሳምንት በኃላ ከድል የታረቀው አዳማን ገጥሞ ዳዊት እስጢፋኖስ ከፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡

ከቀደመው የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ በተለየ ሙሉ ለሙሉ ማጥቃትን ታሳቢ ያደረገ የተጫዋቾች ምርጫ ያደረጉት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሰባት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል፡፡ በውጤቱም ቡድኑ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠሩ ባሻገር በአመዛኙ በተጋጣሚው ሳጥን ዙሪያ አመዝኖ መጫወቱ ከጎንዮሽ ኳሶች እየተላቀቀ መምጣቱን የሚያሳይ ነበር፡፡

ቡድኑ ወደ ድል መመለሱ እና በሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ሲመዘንም በቀጣይ ጊዜያት እስካሁን እንደድክመት ለሚነሳበት የመጀመሪያ ተመራጭ ተጨዋቾችን የመለየት ችግር መፍትሄ የአዳማው ጨዋታ ፍንጭ የሚሰጥ ሆኖ አልፏል፡፡ በፈጠራው ረገድ ችግሮች ይስተዋልበት የነበረው ሰበታ በድሉ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት የቻለ ሲሆን ይበልጥ ለመረጋጋት የዳዊት እስጢፋኖስን ብቃት መልሶ ያገኘበትን ይህንን የጨዋታ ሂደት በሌሎች ተጋጣሚዎች ላይም ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ