የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ሁለተኛ ዙር የሚደረግበት ስፍራ ሲታወቅ ክለቦች ተቃውሞ አሰምተዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የመጀመርያ ዙር ዛሬ ሲጠናቀቅ የሁለተኛ ዙር የሚጀምርበት ጊዜ እና የሚካሄድበት ስፍራ ቢወሰንም ተሳታፊ ቡድኖች ግን ከአሁኑ ቅሬታ እያሰሙ ይገኛሉ።

ባቱ (ዝዋይ) በሚገኘው የሼር ኢትዮጵያ ስታዲየም እየተከናወነ የሚገኘው የ2013 የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሦስት የትግራይ ክለቦች በወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ባለመሳተፋቸው በዘጠኝ ክለቦች መካከል እየተከናወነ ይገኛል። የመጀመርያው ዙር ውድድር በኢትዮኤሌክትሪክ መሪነት ትናንት መጠናቀቁም ይታወሳል።

የወድድሩ አዘጋጅ አካል ለቡድኖቹ የ20 ቀናት ዕረፍት የሰጠ ሲሆን በዚህም ጊዜ ዝውውር እንደሚያከናውኑ ታውቋል። የካቲት 20 ላይ የሁለተኛው ዙር ውድድር የሚጀምር ሲሆን ሀዋሳ ውድድሩ የሚከናወንበት ስፍራ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

የውድድር ስፍራውን እና የዝውውር ጊዜውን አስመልክቶ ገሚሶቹ ክለቦች ቅሬታቸውን ያሰሙ ሲሆን ዋና ዋና ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው።

” በጣም አነስተኛ የዝውውር ጊዜ ነው የተሰጠን። አሁን ላይ ከምድብ ለ እና ሐ ተጨዋች ማዘዋወር ብንፈልግ እንኳን አንችልም፤ ምክንያቱም ተጫዋቾች የሚገኙት ውድድር ላይ ነው። እንደዚሁም ከአንደኛ ሊግ ማዘዋወር ብንፈልግ አንችልም። ”

” በዕጣ ማውጣቱ ስነ ስርዓት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ቀጣይ ውድድር የሚደረግበት ቦታ በጋራ ለማውጣት ነበር የተስማማነው። ኮሚቴው በሦስቱ የውድድር ስፍራዎች ተበትኖ ነው ያለው። ውሳኔው የተላለፈውም በአንድ ወይም በሁለት ሰዎች ፍላጎት ነው። ይህም አንድ ቡድን ለመጥቀም ዓይን ያወጣ ስራ ነው። ክቡር ፕሬዝዳንቱ ይህን ጉዳይ ተመልክተው ከምንም ነፃ የሆነ እግርኳስ እንዲኖር ቢያደርጉልን ነው ጥያቄችን። አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ባህርዳር፣ ሀዋሳ፣ ወላይታ ሶዶ እና ወልድያ ስታዲየሞች ውድድሩን ማስተናገድ የሚችሉ ቦታዎች ናቸው። ለምን እነዚህን ቦታዎች ለምርጫ አላቀረቡም። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *