አፍሪካ | የካፍ ፕሬዝዳንት ዕግድ ተነሳ

ከወራት በፊት ከካፍ ፕሬዝዳንትነታቸው በእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ የእግድ ውሳኔ የተላለፈባቸው አህመድ አህመድ የተላለፈባቸው የእግድ ውሳኔ ተነስቶ ወደ ፕሬዝዳንትነት መንበራቸው መመለሳቸው ታውቋል።

የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ኅዳር ወር ላይ የመተዳደሪያ ደንብን በመጣስ የካፍን ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድን ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ማገዱን ይፋ መደረጉ ይታወቃል። ይህንን እግድ ተከትሎም ማዳጋስካራዊው ፕሬዝዳንት በቀጣዩ ምርጫ መወዳደር አይችሉም የሚሉ መረጃዎችም ወጥተው ነበር። የእግዱ ውሳኔ ተገቢ አይደለም በማለት ለሰፖርት ግልግል ፍርድቤት (ካስ) አቤቱታቸውን ያቀረቡት ፕሬዝደንት አህመድ ጉዳያቸው ተቀባይነት አግኝቶ በፊፋ የተወሰነባቸው ውሳኔ ባለፈው ሳምንት ታግዷል። ይህን ተከትሎም ትናንት በያውንዴ ስብሰባ ያደረገው የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በካስ ውሳኔ መሰረት የፕሬዝዳንትነት ቦታቸውን የመለሰላቸው ሲሆን ማርች ወር ላይ በሚካሄደው ቀጣዩ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ለመወዳደር እጩ ከሆኑት አራት ተወዳዳሪዎች ጋር ለመፎካከርም አረንጓዴ መብራት ስለማግኘታቸው ተሰምቷል።

በዚህ ሳምንት ከትውልድ ሀገራቸው ማዳጋስካር ወደ ካሜሩን ለማቅናት በአዲስ አበባ ለሰዓታት ለትራንዚት በቆዩበት አጋጣሚ ከወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀኃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

በተያያዘ ዜና በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ካሜሩን የሚገኙት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራም በካፍ የሥራ አስፈፃሚ አባል ሆኖ ለመመረጥ እንደሚወዳደሩ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው ዕለት ፍፃሜውን በሚያገኘው ውድድር ላይ ማሊ ከ ሞሮኮ የሚያደርጉትን የፍፃሜ ጨዋታ በኮሚሽነርነት እንደሚመሩ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ