የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀቁ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የመጀመርያ ዙር የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

ረፋድ ላይ የተካሄደው የገላን ከተማ እና የሰ/ሸ/ደ/ብርሃን ጨዋታ አጀማመሩ ሞቅ ብሎ እና በጎል ታጅቦ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርከት ያሉ ጎሎች ይስተናገድበታል ቢባልም መጨረሻው ሳይምር በአንድ አቻ መጠናቀቁ አስገራሚ ሆኗል። ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ሰሜን ሸዋዎች ናቸው። በመልሶ ማጥቃት ከሜዳቸው አጋማሽ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ አፍትልኮ የገባው ካሳሁን ሰቦቃ በጥሩ አጨራረስ በ3ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል መምራት ጀምረው ነበር። ጎል ይቆጠርባቸው እንጂ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የነበራቸው ገላኖች የተሳካም ባይሆን በተደጋጋሚ ወደ ጎል መድረሳቸው ኃላ ላይ ተሳክቶላቸው በ12ኛው ደቂቃ የሰሜን ሸዋው ግብጠባቂ ሙሴ ገብረኪዳን የሰራውን ስህተት ተከትሎ የተሰጠውን ሁለተኛ ቅጣት ምት ወጣቱ ተስፈኛ አጥቂ ከማል አቶም በግሩም ሁኔታ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። 

በመጀመርያው አስራ አምስት ደቂቃ በተቆጠሩ ጎሎች ጨዋታው የተጋጋለ ቢመስልም አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ብዙም የጎል ሙከራ አልታየበትም ነበር። የገላኖቹ አጥቂ አብዱልለጢፍ ሙራድ እና ከማል አቶም ከፈጠሩት የጎል አጋጣሚ ውጭ ሌላ ሙከራዎች ባናይም የሁለቱም ቡድኖች እንቅስቃሴ ሳቢ ነበር።

ከዕረፍት መልስ በመጨረሻው ደቂቃ በገላን በኩል የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተስፈኛ አጥቂ እና በዘንድሮ ከፍተኛ ሊግ ክስተት የሆነው ኪቲካ ጀማ ከርቀት ሞክሮት ሙሴ ገብረኪዳን በጥሩ ሁኔታ ካዳነበት ሙከራ ውጭ ፍትጊያ የበዛበት የሀይል አጨዋወት እና የሚቆራረጡ ኳሶች በሁለቱም በኩል አስመልክቶን ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጄኔራል መሐመድ የመከላከያ ስፖርት ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ እና አቶ ባህሩ ጥላሁን የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ የምድብ ሀ የመጀመርያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታን በክብር እንግድነት በመታደም ዘጠኝ ሰዓት የጀመረው ተጠባቂው የመከላከያ እና የለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ ያለጎል ተጠናቋል።

ብዙ የኳስ ንክኪዎች የበዙበት እና እንደ ቡድን ጎል ለማስቆጠር ጥረት የተደረገበት ጥሩ ጨዋታ መመልከት ብንችልም አልፎ አልፎ የሚታዩ አላስፈላጊ አንባጓሮዎች የጨዋታውን መንፈስ ቀይረውታል። መከላከያ የጎል ዕድል ለመፍጠር በሳሙኤል ሳሊሶ እና በመሐመድ አበራ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል። በአንፃሩ ጣፎዎች አስጨናቂ የሆኑ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ መከላከያ ላይ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም የተለየ ነገር ሳያስመለክቱን ጨዋታው ያለጎል ተጠናቋል። 

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ የመጀመርያ ዙር በኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነት ሲጠናቀቅ ከቀናት በኃላ ሁለተኛው ዙር ጨዋታ በተመረጠ አንድ የክልል ሜዳ የሚካሄድ ይሆናል።

በመጨረሻም በርከት ያሉ ውድድሮችን እያስተናገደ ያለው የሼር ሜዳ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ዘመናዊ ሆኖ ከመጫወቻ ሜዳ ስር ባለው ውሀ በማጠጣት የሚከባከቡበት መንገድ ለሁሉም ሜዳዎች አስተማሪ እንደሚሆን መታዘብ ችለናል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ