ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

የአስራ አንደኛው ሳምንት ትኩረት ሳቢ የሰልጣኞች ነክ ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶችን እንደሚከተለው ቃኝተናል።

👉የአሰልጣኝ ሹም ሽር ለቅዱስ ጊዮርጊስ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣልን ?

የቅዱስ ጊዮርጊስ ቦርድ አሰልጣኝ ማሒር ዳቪድስን አሰናብቶ በምትካቸው ሌላ አሰልጣኝ ለመቅጥር እያጤነ እንደሚገኝ መዘገባችን ይታወሳልነገርግን ‘የቅዱስ ጊዮርጊስ ችግር በአሰልጣኝ ሹም ሽር ይፈታል ? ‘ስንል እንጠይቃለን።

በሀገሪቱ የሚገኙ አሉ የሚባሉ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው ቡድን ወደ ቀደመ ክብሩ የሚመራው አሰልጣኝ አጥቶ በአሰልጣኝ መቅጠር እና የማባረር አዙሪት ውስጥ ይገኛል።

ከፕሪምየር ሊጉ ክብር ከተራራቁ ሦስተኛ የውድድር ዘመናቸው ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በእነዚህ ወቅቶች ቡድኑን የመሩት አሰልጣኞች ክለቡን የሊጉ ባለክብር ለማድረግ የሚያንስ አቅም አላቸው ብሎ ለመውሰድ ቢያስቸግርም በክለቡ የቦርድ አመራሮች ዘንድ ክለቡ ወደ ቀደመ የበላይነቱ በአፋጣኝ እንዲመለስ ከመጓጓት በመነጨ የሚወስዷቸው ጊዜያቸውን ያልተጠበቁ የአሰልጣኝ ስንብት እና ሹመት ውሳኔዎች ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።

በቅድመ ዝግጅት ወቅት የተጫዋቾች ዝውውር ከተጠናቀቀ በኋላ ለሀገሪቱ እግርኳስ ባዳ የሆነን አሰልጣኝ የሚቀጥረው ቡድኑ አሰልጣኞች ነገሮችን በራሳቸው እሳቤ ለመገንባት የሚያስችል በቂ ጊዜም ከመስጠት አንፃር ክፍተቶች አሉበት። በዚህም ሂደት ቡድኑ በአንድ አሰልጣኝ ቀጣይነት ያለው የሚያድግ እንቅስቃሴ ከማሳየት ይልቅ በተደጋጋሚ የሽግግር ጊዜያት ውስጥ እየተገኘ ከውጤት እንደተራራቀ ቀጥሏል።

አሁንም አሰልጣኙን ለማሰናበት እንደወሰነ እየተነገረ የሚገኘው ቡድኑ እንደቀደመው ጊዜያት ወደ ሽግግር ውስጥ ከመክተት በዘለለ የሚሰጠው ጥቅም አጠያያቂ ነው።

👉 በህመም ውስጥ ሆነው ቡድናቸውን የመሩት አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቡድናቸው ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከነማን ሲገጥም አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን የወትሮው አዝናኝ አስተያየታቸው አብሯቸው አልነበረም። ከጨዋታ በፊት አሰልጣኙ በሰጡት አስተያየት ላይም ፊታቸው ላይ ጥሩ ስሜት አይነበብም ነበር። የዚህ ምክንያት ግን ከቡድኑ ውጤት ማጣት እየበረታ ያመጣው ጫና አልነበረም። ይልቁኑም አሰልጣኙ የጤና ዕክል ገጥሟቸው የነበረ በመሆኑ ነው።

ከሽንፈት መልስ ድሬዳዋ ከተማ ከሊጉ መሪ ጋር የነበረውን ከባድ ጨዋታ ማስታገሻ መርፌ ተወግተው ለመምራት የተገደዱት አሰልጣኙ ከሌላው ጊዜ በተለየ በተቀዛቀዘ ስሜት ጨዋታውን ጨርሰዋል። በጨዋታ መሀል ይታይ የነበረው የተጠባባቂ ተጫዋቾች አካላዊ እንቅስቃሴም ከሜዳ ላይ ውጤቱ ባሻገር ከአሰልጣኝ ፍሰሀ ጥሩ ስሜት ላይ ካለመሆን ጋር የተገናኘ ይመስል ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ ለማጣራት እንደሞከረችው አሰልጣኝ ፍሰሀ ዛሬ ህክምናቸውን ሲከታተሉ የዋሉ ሲሆን ውጤቱ ነገ የሚታወቅ ቢሆንም በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መገንዘብ ችላለች።

👉ተጫዋቾቻቸውን ተጠያቂ የሚያደርጉት ዘርዓይ ሙሉ፤ ኃላፊነትን የሚጋሩት ፋሲል ተካልኝ እና ካሣዬ አራጌ

የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው በኢትዮጵያ ቡና አሰቃቂ ሽንፈትን ማስተናገዱን ተከትሎ የገዛ ቡድናቸውን የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎችን ሲወቅሱ ተደምጠዋል።

አሰልጣኙ ከጨዋታ በኋላ ሲናገሩ “ዛሬ ቡድናችን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ጥሩ አልነበረም። በተለይ ተከላካዮቻችን በጣም ይሸሹ ነበር። እኔ ካልኩት ውጪ ነው ሲጫወቱ የነበሩት። ያንን ለማስተካከል ሞክረናል። ግን ያው በተፈጥሮ ፍጥነት ስለሌላቸው የግድ ይሸሻሉ። የቡናን ተጫዋቾች እየጋበዙ ነበር። በዚህ የተነሳ አሸፋፈንም ችግር ስለነበር በተደጋጋሚ በእነሱ ግራ በእኛ በቀኝ በኩል በሚመጡ ኳሶች ነው የተጠቀሙት። በዛ በኩል የሚጫወተው አማኑኤል ዛሬ የአቋቋም ችግር ነበረበት። ታይሚንጉን የጠበቀ አካሄድ አይደለም የሄደው። የእኛ አጨዋወት ያመጣው ነገር ነው። ተነሳሽነትም ይጎድል ነበር። በተለይ ጎሎች ሲገቡ እየወረዱ ነው የሄዱት። ያው ኳስ ላይ ያጋጥማል ግን የምንፈልገውን ጨዋታ ለመጫወት አልቻልንም። እነሱ ግን ተሳክቶላቸዋል።ጥሩ ነበሩ ውጤቱም ይገባቸዋል።” የሚል ሀሳብን ሰጥተዋል።

እርግጥ እግርኳስ በአንድ ግለሰብ ብቻ የሚንጠለጠል ባይሆንም ተጫዋቾቻቸው ደካማ እንቅስቃሴ ቢያሳዩ እንኳ አሰልጣኞቻቸው ጉዳዩን በጓዳቸው አድርገው ከመገናኛ ብዙሀን ፊት ግን ተጫዋቾቻቸውን በግልፅ ከመተቸት ቢቆጠቡ የቡድን ስሜትን ከመጠበቅ አንፃር የሚመከር አካሄድ እንደሆነ ይጠበቃል። በተጨማሪም ተጫዋቾች በጨዋታ ላይ ለሚያሳዩት ደካማ አቋም የራሳቸው ድክመት እንዳለ ሆኖ ኃላፊነት ወስዶ የሚያሰልፋቸው አሰልጣኝ የሚሰጣቸው ሚና እና ይዞት የሚቀርበው አጨዋወት አስተዋፅኦ ያለው እንደመሆኑ ሙገሳውንም ወቀሳውንም መጋራት ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደምም ቀይረው ያስገቡት እሱባለው ሙሉጌታን በተመሳሳይ መንገድ የወቀሱት አሰልጣኝ ዘርዓይ አስተያየቶች የተጫዋቾቻቸው ስነ-ልቡና ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ቀላል የሚባል አይደለም።

በተቃራኒው የባህር ዳር ከተማው ፋሲል ተካልኝ እና የኢትዮጵያ ቡናው ካሣዬ አራጌ ከጨዋታ በኋላ በሚሰጡት አስተያየት ስህተት የሚሰሩ ተጫዋቾቻቸውን የሚከላከሉበት መንገድ የሚጠቀስ ነው። አሰልጣኝ ፋሲል በዚህ ሳምንት ባህር ዳሮች ነጥብ በጣሉበት የጅማው ጨዋታ ብዙ ጎል ስለሚያስተናግደው የኋላ ክፍል ሲጠየቁ ስህተቱን ግለሰባዊ ከማድረግ ይልቅ ችግሩን የጋራ ያደረጉበት አስተያየትም እዚህ ጋር የሚጠቀስ ነው።

“ችግሩን እንደቡድን ብመለከተው ይሻላል። ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ዋጋ የሚያስከፍሉ ብዙ ስህተቶች ሜዳ ላይ እየታዩ ነው። እነዛን ማሻሻል ይጠበቅብናል። ተጫዋቾቹ የሚችሉትን እያደረጉ ነው። ቡድኑ ስህተቶች እየደጋገመ ከሆነ የእኔ ኃላፊነት ነው ያንን ማሻሻል። ተጨዋቾቼ ግን የሚችሉትን እያደረጉ እንደሆነ ይሰማኛል።”

ዓበይት አስተያየቶች

👉አሸናፊ በቀለ ስለውጤቱ ተገቢነት

“ማግኘት የነበረብን ውጤት ነበር ፤ በራሳችን ጥፋት ነው ጎል የገባብን በተከላካይ እና በግብ ጠባቂ አለመናበብ ችግር ነው። ከዛ ውጪ ለእኛ ይሄ ትልቅ ውጤት ነው። ምክንያቱም ከአራት ቀን በላይ ቡድኑ አልተዘጋጀም። ሥራው የነበረው ሙሉ ለሙሉ የታክቲክ ስራ ነው። በቀላሉ ጎሎች እንዳይቆጠሩብን የምንሰራቸው ሥራዎች ነበሩ። ካሳለፍነው ውጣ ውረድ አንፃር ትልቅ ድል ነው ለእኛ ለሀዲያ ሆሳዕናዎች።”

👉ማሂር ዴቪድስ ስለማጥቃት ዕቅዳቸው

“በተወሰኑ ቅፅበቶች ወደ ፊት ስበናቸው ከጀርባ መግባት ችለን ነበር። ጥሩ ቅብብሎችን አድርገን ለመግባት እንሞክር ነበር ፤ ግን ክፍተት አልነበረም። ግዙፍ ተከላካዮቻቸው እና የተከላካይ አማካዩ ክፍተቶችን ይዘጉ ነበር። በተወሰኑ ደቂቃዎችም መስመሮች በኩል የመግባት ዕቅድም ነበረን ግን በፈለግነው ጊዜ ላይ ክፍተት ማግኘት አልቻልንም። በመጨረሻም 1-1 ተጠናቋል።”

👉አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስለአቡበከር እና ስለሜዳው ጥራት ተፅዕኖ

“ሜዳው ምንም ጥያቄ የለውም። ለሁሉም ቡድን ተፅዕኖ ያደርጋል። ጥሩ ሜዳ ከሆነ በሜዳ ምክንያት የምታጣውን ነገር በጥሩ ሜዳ ልታገኘው ትችላለህ። ይህ ከተመቻቸ አጥቂዎች ብዙ ጎል ማስቆጠር ይችላሉ። ለአቡበከርም እንደቡድን ያን የተመቻቸ ነገር ለመፍጠር ነው እና ከተመቻቸለት በግሉ ደግሞ በደንብ ጨዋታውን አይቶ ድርጊቱን መጨረስ የሚያስችል አቅም ያለው ተጫዋች ነው።”

👉የሱፍ ዓሊ ስለቡድኑ መነሳሳት

“ዛሬ ሁለቱም ከንቲባዎች መጥተው ብዙ ነገር ነው ቃል ሲገቡላቸው የነበረው ፤ በጎደለው ነገር እንዲሟላ እስከመልበሻ ቤት ድረስ መጥተው። ትልቅ ተነሳሽነት ነበራቸው። ውጤት ይዘን እንደምንወጣ ነበር ስንነጋገር የነበረውም። ያው አቻውን ይዘን ወጥተናል።”

👉 አስቻለው ኃይለሚካኤል ስለአዳማ የኋላ ክፍሉ መሻሻል

“ከዚህ በፊት እንዳያችሁት በራሳችን ጥቃቅን ስህተት ነበር ጎሎች የሚቆጠሩት። ያን ከደካማ ጎናችም ተነስተን እየሰራን ነው። ያን እያሻሻልን መጥተናል ያው ለውጦች አሉ ቡድናችን ላይ። የኋላ መስመሩም ቅርፅ እየያዘ ነው።”

👉አብርሀም መብራቱ አዳማ ከተማ ላይ ስላስመዘገቡት ድል ትርጉም

“በተደጋጋሚ ከነበሩ አቻ እና ሽንፈቶች በኃላ ሦስት ነጥብ አግኝቶ ወደ ማሸነፍ መመለስ በተጫዋቾቻችን እና በአጠቃላይ በቡድኑ አባላት ሥነ-ልቦና ላይ የሚፈጥረው እገዛ ቀላል እይደለም። እና ወደ አሸናፊነት መመለሳችን ትልቅ ትርጉም አለው ለቡድናችን።”

👉ሙሉጌታ ምህረት ስለመስመር ተጫዋቾቹ የዕለቱ ብቃት

“በእርግጥ እኛ ሁሌም መስመሩን ለመጠቀም እንጥራለን። ክለቦች ግን ትኩረት አድርገው የሚመጡት እነዛ ልጆች ላይ ነው። ጨዋታው እንደውም ብዙ ፋዎሎች አሉት። ዳኞች እንደውም የሚያልፏቸው ነገሮች አሉ ፤ ጥሩ ነው። ያ ይመስለኛል እኔ። ያው አንድ ቡድን የአንድን ቡድን ደካማ ጎን አይቶ ነው የራሱን የሚሰራው። ዛሬ ደስታ ቢኖር ጥሩ ነበር ፤ ዘነበ ግን ሸፍኖታል። እንደበፊቱ እንደደስታ ኳሶች ወደ ፊት ባይወርዱም ጥንቃቄ የመረጥነው አሸንፈን ለመሄድ ነበር።”

👉ሥዩም ከበደ ስለቡድኑ የአደራደር ምርጫ

“4-1-4-1 ሲሆን ሙጂብ ጀርባ ላይ የሚያግዘው መበራከት አለበት ፤ እሱን ነው ያረግነው። በኋላ ግን ወደ 4-2-3-1 ብዙ ጊዜ የለመድነው ጋር መሄድ ችለናል። በሁለቱም ቢሆን በቦታው ላይ ያሉ ተጫዋቾች ምን ያህል ስኬታማ ሆነዋል የሚለውን ነው እያረምን መሄድ ያለብን። በአጠቃላይ ግን ውጤቱን ስለምንፈልገው ለማጥቃት ብዙ ጥረት አድርገናል። ደህና ነው ብዬ ነው የማስበው። 


© ሶከር ኢትዮጵያ