በአስራ አንደኛው ሳምንት በተከናከኑ ጨዋታዎች የተመለከትናቸውን ትኩረት ሳቢ ተጫዋች ነክ ጉዳዮች እንደሚከተለው አሰናድተናል።
👉 የባለ ሐት-ትሪኩ አቡበከር ናስር አስደናቂ መሻሻል
ስለዚህ ወጣት ያልተባለ ነገር ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። ከዕድሜው ቀድሞ ለኃላፊነት የተዘጋጀው ተጫዋቹ በአስደማሚ ዕድገቱ ቀጥሏል።
በዚህ ሳምንት ቡድኑ ሲዳማ ቡና ላይ የዓመቱን ከፍተኛ ጎል በማስቆጠር 5-0 ሲረመርም በድጋሚ ሦስት ጎሎች ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ቡናው ኮከብ በአንድ የውድድር ዓመት ሁለተኛ ሐት ትሪክ መሥራት ችሏል። በ2010 የውድድር ዘመን የጅማ አባ ጅፋሩ ኦኪኪ አፎላቢ በአንድ ዓመት ሁለት ሐት-ትሪኮች ከሠራ ወዲህ ይህን ያደረገ የመጀመርያው ተጫዋች መሆን የቻለው አቡበከር በትልቅ ደረጃ መጫወት ከጀመረ ብዙ ጊዜ ባያስቆጥርም ከወዲሁ በሊጉ ታሪክ ከታዩ ታላላቅ አጥቂዎች ጎራ የሚያሰልፈው አስደናቂ አቋም ላይ ይገኛል።
በለጋ ዕድሜው የኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ አምበል ለመሆን የበቃው አቡበከር ዘጠኝ ጨዋታዎች አድርጎ 14 ጎሎችን በማስቆጠር የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክርን እየመራ ይገኛል። ዐምና ውድድሩ እስኪቋረጥ ድረስ ስምንት ጎሎች አስቆጥሮ የነበረው አቡበከር ዘንድሮ ገና ውድድሩ ሳይጋመስ ይህን ያህል ጎል ማስቆጠሩን ስንመለከት ምን ያህል ከፍተኛ መሻሻል እንዳሳየ መረዳት ይቻላል።
👉የነገው ጥሩ አሰልጣኝ – መስዑድ መሐመድ
ሰበታ ከተማ አዳማ ከተማን በዳዊት እስጢፋኖስ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በረታበት ጨዋታ ከጨዋታ ዕለት ስብስብ ውጪ የነበረው መስዑድ መሀመድ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቅን ተከትሎ አንዳች የተለየ ድርጊትን ሲያደርግ ተመልክተናል።
ከተመልካች ጋር ሆኖ ጨዋታውን ሲከታተል የነበረው የሰበታ ከተማው ተቀዳሚ አምበል መስዑድ በዕረፍት ሰዓት ከነበረበት የመቀመጫ ስፍራ ወርዶ ለቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ይታገሱ ጨዋታውን የተመለከተ የሚመስሉ ሀሳቦችን ሲያካፍል ተመልክተናል። በዚህም ወቅት ሀሳቡን ይገልፅበት የነበረው መንገድ እና አካላዊ እንቅስቃሴው በመስዑድ ውስጥ የነገውን ጥሩ የእግርኳስ አሰልጣኝ ያስመለከተን ክስተት ነበር።
👉”የማይታየው” አሥራት ቱንጆ
በእግርኳስ ሜዳ ላይ ያላቸውን የሚሰጡ እንዲሁም ለቡድኑ ውጤት ማማር ከፍተኛ አስተዋጽኦን እየተወጡ በሚገባቸው ደረጃ አድናቆት የማይቸራቸው ዕድለ ቢስ ተጫዋቾች አሉ። ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር ተከላካይ አሥራት ቱንጆ ይገኝበታል።
ሜዳ ላይ ያለውን ለመስጠት ወደ ኋላ የማይለው አሥራት ለኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር ማጥቃት ተጨማሪ ጉልበትን የሰጠ ተጫዋቾች ነው። ታታሪነት መገለጫው የሆነው ተጫዋቹ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ያለው ተሳትፎ ይበልጥ እየጎላ መጥቷል። ተፈጥሮአዊ የቀኝ አግር ተጫዋች ሆኖ በግራ የመስመር ተከላካይነት መጫወቱ የሚሰጠውን ወደ ውስጥ ሰብሮ እያጠበበ የመግባት ዕድልን ተጠቅሞ በተደጋጋሚ ወደ ውስጥ እያጠበበ በመግባት አደጋ ሲፈጥር እያስተዋልነው እንገኛለን።
ቡድኑ ሲዳማ ቡናን ሲረታም አንድ ግብ ከማስቆጠር አልፎ አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ሲያቀብል ሀብታሙ ታደሰ ላስቆጠረው ግብ መነሻ ሆኗል። ታድያ ይህን ሁሉ በአንድ ጨዋታ ማድረግ የቻለው አስራት እንደወትሮው ሁሉ ስለጥረቱ እና አበርክቶው በቂ ዕውቅና ሲቸረው አይስተዋልም።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሐት-ትሪክ የሰራው አቡበከር ናስር ግን ከሱፐር ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ ከቡድን አጋሮቹ ለይቶ ለአሥራት ቱንጆ አድናቆቱን ችሮታል።
👉ታታሪው ሄኖክ አዱኛ
ተገማች እየሆነ በመጣው የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ በቀኝ መስመር ተመላላሽነትም ሆነ በግራ ተከላካይነት የሚጫወተው ሄኖክ አዱኛ በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ያለው ሚና እጅግ ወሳኝ እንደሆነ ቀጥሏል።
ፊት ላይ የሚገኙትን አጥቂዎች በቀጥተኛ አጨዋወት ቶሎ ቶሎ ለማግኘት ከሚሞክረው የቡድኑ ተቀዳሚ የማጥቂያ ስልት በተጓዳኝ ከሄኖክ የሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች የቡድኑ ዓይነተኛ የማጥቂያ መንገድ ሲሆኑ ይስዋላል። ለዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥሙ ቡድኖች የሄኖክን እንቅስቃሴ መገደብ ተቀዳሚ ዕቅዳቸው ሲያደርጉ ይታይ ጀምሯል።
ተጫዋቹ በተጋጣሚ ቡድኖች ክትትል ስር ቢወድቅም ከዚህ ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት፤ ብሎም በግራ መስመር ተከላካይነት ሆነ በሚና መሸጋሸግ በቀኝ መስመር ተመላላሽነት የሚሰጠውን ሚና የሚወጣበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው።
በሆሳዕናው ጨዋታ በመስመር ተከላካይነት የጀመረው ተጫዋቹ በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች ባደረጉት የአደራደር ለውጥ በቀኝ መስመር ተመላላሽነት ለቡድኑ ጥሩ ግልጋሎት ለመስጠት ጥረት አድርጓል። በዚህም ቡድኑ አቻ የሆነበትን ግብ በግል ጥረቱ ማስቆጠር ችሏል።
👉በቡድኑ ሽንፈት ክፉኛ የተበሳጨው ይገዙ ቦጋለ
በ11ኛ ሳምንት የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን ፍፁም በሆነ የጨዋታ የበላይነት 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
ከጉዳት መልስ የቡድኑን ጨዋታ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ የተከታተለው ወጣቱ አጥቂ ይገዙ ቦጋለ በአጠቃላይ የቡድኑ እንቅስቃሴ እና ግቦችን ያስተናግዱ በነበረበት መንገድ እጅጉን በመበሳጨቱ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ሲያለቅስ የታየ ሲሆን በብስጭት ተቀምጦ የነበረበትን ወንበር አሽቀንጥሮ የወረወረበት መንገድም ተጫዋቾቹ በወቅቱ የተሰማውን ብስጭት ያሳየ ነበር።
ይገዙ ከዚህ ቀደም ቡድኑ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ሲወጣ በተመሳሳይ ፊቱ በእንባ ሲታጠብ የተመለከትን መሆኑን ስናስብ የተጫዋቹ ስሜት ስስ ስለመሆኑ መረዳት እንችላለን።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ድሬዳዋ በዚህ ሳምንት በፋሲል ከነማ በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጡ የቡድኑ አባላት ሲያሳዩት የነበረው የሀዘን ሁኔታ ትኩረት ሳቢ ነበር።
👉የፋሲል ከነማ ወጣቶች ዕድል ማግኘት
ሊጉን በ25 ነጥቦች እየመራ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ ለወጣት ተጫዋቾች የመሰለፍ ዕድል እየሰጠ ይገኛል።
በፕሪምየር ሊጉ ከሚገኙ የተረጋጉ ቡድኖች አንዱ የሆነው ፋሲል ከነማ በመጀመሪያ ተመራጭነት የሚጀምሩት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከጨዋታ ጨዋታ የሚታወቁ ቢመስልም ቡድኑ በስብስቡ የያዛቸውን ተስፈኛ ተጫዋቾችን ግን ተቀይረው በመግባትም ቢሆን ዕድሎችን እየሰጠ ይገኛል።
በተለይ እነዚሁ ወጣት ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የሚገቡት ቡድኑ አዎንታዊ ውጤትን በያዘበት ወቅት መሆኑ ተጫዋቾቹ ከጫና ነፃ ሆነው ይበልጥ ራሳቸው የሚገልፁበት ዕድል እየፈጠረላቸው የራስ መተማመናቸውን ከጨዋታ ጨዋታ እያሳደጉ እንዲመጡ እያስቻላቸው ይገኛል።
ድሬዳዋ ከተማን 2-0 በረቱበት ጨዋታ ያደረጓቸው ቅያሬዎችም ይህንን ያሳይቶናል። በጨዋታው ገና ከ56ኛው ደቂቃ አንስቶ 2-0 እየመሩ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ ሜዳ የተመለሰው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ምሩቁ እና የቀድሞ የደደቢት አማካይ ኪሩቤል ኃይሉን ጉዳት በገጠመው ሀብታሙ ተከስተ ቀይረው ሲያስገቡ ዘንድሮ ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ተፅእኖ እየፈጠረ የሚገኘው ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና ሌላው ወጣት ዓለምብርሃን ይግዛውን ቀይረው ማስገባታቸው ከላይ የጠቀስነውን ሀሳብ ያጠናክራል።
👉የተመስገን ደረሰ ልዩ ሆኖ መታየት
በእግርኳስ ብዙ ሚና መወጣት የሚችሉ ተጫዋቾች በአሰልጣኞች ዘንድ ተፈላጊ ቢሆኑም የተጫዋቾቹ የእግርኳስ ሕይወት ላይ ግን ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው። በተለያየ የመጫወቻ ሚና መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾች በተለያየ ስፍራ መጫወት በመቻላቸው ብቻ የዚህ የሚና መለዋወጥ ሰለባ ሲሆኑ መመልከት የተለመደ ነው። የዚህ አንዱ ማሳያ የጅማ አባ ጅፋሩ ተመስገን ደረሰ ነው።
በአጥቂ እና በግራ የመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው የቀድሞው የጅማ አባ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ተጫዋች በሁለቱም ሚናዎች ቡድኑን እያገለገለገ ይገኛል። ከባህር ዳር ከተማ ጋር ሁለት ለሁለት በተለያዩበት ጨዋታም የዘንድሮው የክለቡ የዓመቱ የመጀመሪያ ጎል አስቆጣሪ ቡድኑን በሁለቱም ሚናዎች ላይ አገልግሏል።
በአጥቂነት ጨዋታውን የጀመረው ተመስገን ሁለት የግል ጥረት የታከለባቸውን አስደናቂ ግቦች ለቡድኑ ቢያስቆጥርም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ዳግም ወደ በመስመር ተከላካይነት ተመልሶ ታይቷል። እንደ ቡድን እጅግ አንገብጋቢ የሆነው የግብ አስቆጣሪ ተጫዋች እጥረት ያለበት ቡድኑ በመስመር ተከላካይ ሌሎች ተጫዋችን እየተጠቀመ ተመስገንን በአጥቂ ስፍራ መጠቀም የሚችልበትን ዕድል ቢያመቻች ተጫዋቹ ያለውን አቅም ይበልጥ መጠቀም በቻለ ነበር።
👉የዳዊት እስጢፋኖስ በጎ ተፅዕኖ
የሰበታ ከተማው አማካይ ዳዊት እስጢፋኖስ በተለያዩ ምክንያቶች ከመጀመሪያ ተመራጭነት ርቆ ቢቆይም ወደ መጀመሪያ አሰላፍ በተመለሰበት የአዳማ ከተማው ጨዋታ ግን ለቡድኑ የነበረው አበርክቶ እጅግ ከፍ ያለ ነበር።
ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገር ለነበረው የሰበታ ከተማ ቡድን የዳዊት እስጢፋኖስ መመለስ የተለየ አቅም የፈጠረ ይመስላል። በጨዋታው ሰበታ ከተማዎች ካደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በስተጀርባ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የነበረው ሚና የላቀ ነበር።
በተጨማሪም ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይ ሳይጠቀም ወደ ሜዳ የገባውን ቡድን አጠቃላይ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከኃላ ሆኖ ይመራበት የነበረበት መንገድም እጅግ ልዩ ነበር።
👉የሁለቱ ግብጠባቂዎች ብሽሽቅ
ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በቅጣት ሳቢያ መሰለፍ ያልቻለው የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ እንዲሁም በጉዳት ከሲዳማ ቡና ስብስብ ውጪ የነበረው ሌላኛው ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በስታድየም ተገኝተው በጋራ ሲመለከቱ አስተውለናል።
በኢትዮጵያ ቡና 5-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ተክለማርያም ከግቦች መቆጠር በኃላ መሳይ አያኖ ላይ ሲቀልድ የተስዋለ ሲሆን በተቃራኒው መሳይ ደግሞ አዝኖ በተደጋጋሚ ሲያቀረቅር በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ዕይታ ውስጥ ገብቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ