ሽመልስ በቀለ መድመቁን ቀጥሏል

ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ በተከታታይ ጎል ማስቆጠሩን ቀጥሏል።

በ11ኛ ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ዋዲ ዴግላን የገጠመው ምስር ለል ማቃሳ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል። ካይሮ ላይ አመሻሹን በተደረገው በዚህ ጨዋታ ሽመልስ በቀለ በ23ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ቡድኑን ቀዳሚ ሲያርግ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ፓውሊን ቮአቪ እና ባሰም ሞርሲ ላስቆጠሯቸው ጎሎችም አመቻችቶ በማቀበል ድንቅ ዕለት አሳልፏል።

ድሉን ተከትሎ አስራ አራት ጨዋታዎች ያደረገው ምስር ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ ነጥቡን 23 በማድረስ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ጎል ያስቆጠረው ሽመልስ በቀለም ከዛማሌኩ የሱፍ ኦባማ በመቀጠል በስድስት ጎሎች በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ሰንጠረዥ ሁለተኛ ላይ ተቀምጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ