ዘወትር እንደምናደርገው በመጨረሻው የትኩረት ፅሁፋችን ከሦስቱ ርዕሶቻችን ውጪ ያሉ ሀሳቦችን እንዲህ አንስተናል።
👉 የሊጉ የጅማ ቆይታ መጠናቀቅ
እንደሚታወቀው የዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዚህ ቀደም ይደርግ ከነበረበት መንገድ በተለየ ሁኔታ እየተከናወነ ነው። በዚህም ቡድኖች በአንድ ከተማ ላይ ተቀምጠው የተወሰኑ ሳምንታት ጨዋታዎቻቸውን አከናውነው ለቀጣይ ጨዋታዎች ወደ ሌላ ከተማ የሚዘዋወሩበትን ሂደት እየተከተለ ነው። የምዕራብ ኢትዮጵያዋ ጅማ ከተማም በአዲስ አበባ የጀመረውን ውድድር ስታስተናግድ ከርማ ዕንግዶቿን ሸኝታለች።
ከተማዋ መሰል ውድድሮችን በማስተናገድ ያላትን ልምድ ጥያቄ ውስጥ ያስገቡ የስፖርት ቤተሰቦች ስለውድድሩ ስኬት ጥርጣሬ ገብቷቸው የነበረ ቢሆንም ጅማ ኃላፊነቷን በአግባቡ መወጣት ችላለች። የጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታድየምን እና የህክምና ድጋፍን የመሰሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ባሟላበት ሁኔታ የተደረገው ውድድር በአመዛኙ ስኬታማ ነበር። ይህን ለማለትም በተለያዩ አጋጣሚዎች አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ማየት ይቻላል። ሁሉም የከተማዋን እንግዳ ተቀባይነት እና በነበራቸው ጊዜ ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁበት መንገድ ለዚህ ምስክር መሆን ይችላል።
ሊጉ ከሁለት ሳምንት በኋላ በባህር ዳር እንደሚቀጥል ይጠበቃል። የቀጣይዋ ባለተራ ባህር ዳር ኃላፊዎችም ከወዲሁ በጅማ በነበረው ውድድር ላይ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ለመውሰድ ከድክመቶቹም ለመማር ከጅማ አቻዎቻቸው ጋር የሥራ ግንኙነት ፈጥረው ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ቢወስዱ መልካም ነው እንላለን።
👉ጨዋታ ያስጀመረው ታዳጊ
አዳማ ከተማን ከሰበታ ከተማ ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ አንድ ያልተለመደ ክስተት ተመልክተናል።
እንደተለመደው ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሜዳ ከገቡ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አምበሎች ከዕለቱ አርቢትሮች ጋር በጋራ በመሆን በሚያደርጉት የቅድመ ጨዋታ ሁነት ላይ በመሀል ዳኛው የሚመሩ ሲሆን በአዳማ እና ሰበታ ጨዋታ ላይ ግን ጨዋታውን በአራተኛ ዳኝነት የመሩት የአልቢትር ሄኖክ አክሊሉ ልጅ ወደ ሜዳ በመግባት ለቡድኖቹ ዕጣ በመጣል ጨዋታውን እንዲያስጀምር ዕድል የሰጡበት መንገድ አስገራሚ ክስተት ነበር።
👉አክስሲዮን ማኅበሩን ወክለው የተገኙት ግለሰብ
የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርን በመወከል በየጨዋታ ሳምንቱ የተለያዩ ሰዎች ውድድሩ በሚካሄድበት ስታድየም ተገኝተው ሲከታተሉ መመልከት የተለመደ ነገር ነው።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት እንኳ የአክስዮን ማህበሩ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፈቀደ ማሞ ወደ ጅማ አቅንተው የተመለሱ ሲሆን የዚህኛው ሳምንት ባለተራ የነበሩት ደግሞ የቀድሞው የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት በአክሲዮን ማኅበሩ የስራ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የሚገኙት አቶ አሰፋ ሀሲሶ ነበሩ።
እኚህ ግለሰብ በሀገራችን የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች ባልተለመደ መልኩ በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታድየም ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ጨዋታዎችን መታደማቸው ትኩረትን የሚስብ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል።
👉ለትጋታቸው የማይመጥን ክፍያ የሚከፈላቸው ኳስ አቀባዮች
በጅማ ዮኒቨርስቲ ስታድየም ላለፉት ሳምንታት ሲካሄድ በቆየው የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመልካም ተሞክሮነት ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ በተጋጣሚ ቡድኖች ፍላጎት የማይዘወሩት ፣ በተሻለ የአለባበስ ንፅህና ከፍ ባለ ትጋት ይሰሩ የነበሩት ታዳጊዎች ጉዳይ ነበር።
ታድያ በጅማ ዩኒቨርስቲ ስታድየም በተደረጉት ሠላሳ ጨዋታዎች በከፍተኛ ትጋት ያገለገሉት እነዚሁ ታዳጊዎች ሊጉ የጅማውን ቆይታ ማጠናቁቁን ተከትሎ ለሰላሳ ጨዋታዎች ግልጋሎታቸው በነፍስ ወከፍ የሁለት ሺህ ብር ክፍያ እንደተፈፀመላቸው ለማረጋገጥ ችለናል።
እነዚሁ ታዳጊዎች ሙሉ ቀናቸውን መስዕዋት አድርገው ላለፉት አስራ አምስት የጨዋታ ቀናት ለውድድሩ ማማር ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንፃር እና ከወቅታዊ የኑሮ ሁኔታ አንፃር በቀጣይ ውድድሮቹ በሚደረጉባቸው ከተማዎች ለሚገኙ ሌሎች ታዳጊዎች የክፍያ ማሻሻያ ማድረግ ተገቢ ይመስላል።
👉 የጅማ ከንቲባ የመልበሻ ክፍል ቆይታ
ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች የተወጠረው ጅማ አባ ጅፋር ሜዳ ላይም መጠነኛ መሻሻሎችን ቢያሳይም ወደ ድል መምጣት አልቻለም። ሆኖም ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የቡድን መንፈሱ ከፍ ብሎ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ከጨዋታው አንዳች ውጤት ለማግኘት ሲታትሩ ታይተዋል። በዚህም ጅማ በጨዋታው መጀመሪያ ጎል ማስቆጠር ሲችል በሁለተኛውም አጋማሽም በትጋት ተከላክሎ ነጥብ መጋራት ችሏል።
ይህ ሁነት ሜዳ ውስጥ ሲታይ ከሜዳ ውጪ ደግሞ የከተማው ከንቲባ አቶ ቲጃኒ ናስር በተመልካቾች መቀመጫ ላይ ሆነው እንቅስቃሴውን በስሜት ሲከታተሉ ይታይ ነበር። ከንቲባው ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ በመልበሻ ክፍል ተገኝተው ከቡድኑ አባላት ጋር መነጋገራቸውም ተሰምቷል። በቆይታቸውም ለተጨዋቾች የማበረታቻ ድጎማ ለማድረግ እና ትልቅ ችግር የነበረውን የደመወዝ ጉዳይ ለማስተካከል ቃል መግባታቸው ታውቋል። ይህን ጉዳይ ሜዳ ላይ ከነበረው የቡድኑ እንቅስቃሴ አንፃር ስናገናዝበው ቡድኑ የሜዳ ውጪ ችግሮቹ ከተቀረፉለት ለውጥ የማምጣት አቅም እንዳለው ያሳየናል።
👉ከዲ.ኤስ.ቲ.ቪ ባለሙያዎች ምን እንማራለን ?
የዘንድሮውን የቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የተለየ ገፅታ ካላበሱት ነገሮች መካከል የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭቱ መሆኑ አያጠያይቅም።
ታድያ በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን ከሚደርሰው የላቀ የፕሮዳክሽን ውጤት በስተጀርባ ውድድሩ በሚካሄድባቸው ሜዳዎች ከተመልካች እይታ የተሰወሩ በሚያስገርም ትጋት የሚሰሩ በርካታ ባለሙያዎች መኖራቸው እርግጥ ነው።
ታድያ ከዚህ ውስጥ ለዛሬው ለማንሳት የወደድነው ጉዳይ የስራ ትጋት ጉዳይን ነው። እንደሚታወቀው በአዲሱ መርሐግብር መሰረት ጨዋታዎች ከረፋዱ አራት ሰአት እንዲሁም ቀትር ዘጠኝ ሰዓት የሚደረጉ ሲሆን የዲ.ኤስ.ቲ.ቪ ባለሙያዎች ግን ከጠዋቱ ጨዋታ መጀመር ሦስት ሰዓት አስቀደመው አንድ ሰዓት ላይ በስታድየሙ ይሰባሰባሉ።
ታድያ ወደ ሥራ ከመግባታቸው አስቀድሞ በዳይሬክተራቸው መሪነት የቀደሙ ጨዋታ ስርጭቶችን በመገምገም ሊታረሙ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉ በማረም ብሎም በጨዋታ ዕለት ሥራቸው ላይ ማካተት የሚገባቸው እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ወደ ሥራቸው ይሰማራሉ። ከተቋሙ ልምድ አኳያ ይህ ላያስገርም ቢችልም በተመሳሳይ የሚዲያ ዓይነት ላይ ለሚገኙ የሀገራችን ተቋማት ግን ብዙ ትምህርት እንደሚሰጥ ዕሙን ነው።
👉አሁንም ቢሆን ችላ የተባለው የኮቪድ ፕሮቶኮል
ዓለም ዳግም ባገረሸው ሁለተኛው የኮሮና ቫይረስ ማዕበል ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ እየገባበት በሚገኝበት በዚህ ወቅት በሀገራችን የሚታየው ቸልተኝነት እጅግ አስደንጋጭ ነው። እንደማኅበረሰብ የተጠናወተን ግዴለሽነት በስታድየሞቻችን መንፀባረቁንም ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 5-0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በቁጥር ከአስር የሚበልጡ ተቀማጭነታቸውን በጅማ ያደረጉ እና ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩ ታዳጊ ሴቶች እና ጥቂት ወንዶች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የመጫወቻ ሜዳውን ከተመልካቾች መቀመጫ የሚለየውን አጥር አልፈው በመግባት በጨዋታው ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስርን ለማቀፍ እና ፎቶ ለመነሳት ሲረባረቡ አስተውለናል።
ይህም ውድድሩን ለማካሄድ በጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተቀመጠው ምክረ ሀሳብን ፍፁም የጣሰ ድርጊት ነበር። ከጨዋታዎች 72 ሰዓታት በፊት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው ተነጥለው በአንድ ስፍራ እንዲቆዩ የሚደረጉ ተጫዋቾች በዚህ መልኩ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ካላደረጉ ግለሰቦች ጋር በሚኖር ንክኪ በቫይረሱ የሚጠቁበት ዕድል ቢፈጥር ሌሎች የቡድን አባላትን የማዛመት ዕድላቸው ሰፊ ከመሆኑ አንፃር አሁንም ትኩረት ሊደረግበት ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪም በየጊዜው ምርመራ የሚደረግላቸውን ተጫዋቾች ከወረርሺኙ ለመጠበቅ ሲባል የተቀያሪ ተሰላፊዎች መቀመጫ ላይ የመድኃኒት ርጭት ሲከናወን ቢታይም ሌሎች የውድድሩ አካል የሆኑ ግለሰቦች ከጨዋታዎች መጀማር በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ወንበሮቹ ላይ የሚቀመጡ የሚነሱበት ሁኔታ የርጭቱን ዓላማ ዋጋ ሲያሳጣውም አስተውለናል። ይህ እና ሌሎች መዘናጋት የታየባቸው ጉዳዮች በባህር ዳሩ ውድድር ላይ ታርመው እንደሚቀርቡም ተስፋ እናደርጋለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ