የ2013 የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ዛሬ በሁለት ከተሞች ተጀመረ

በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአስራ አራት ቡድኖች መካከል በሁለት ከተሞች የሚካሄደው የ2013 የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ዛሬ ተጀምሯል።

በአዳማ እና በአሰላ ከተሞች የሚካሄደው የዘንድሮው ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከባለፈው ዓመታት የተሳታፊዎች ቁጥር በአምስት ክለቦች ቀንሶ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በአስራ አራት ክለቦች መካከል መካሄዱን ዛሬ ጀምሯል። ሶከር ኢትዮጵያ በተገኘችበት የምድብ ለ አዳማ ከተማ የተካሄዱትን የሦስቱን ጨዋታ ውሎ እንደሚከተለው ቃኝታዋለች።

በማለዳ የተካሄደውን የሀላባ ከተማ እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የወጣቶች እና የታዳጊዎች ልማት ኮሚቴ የሆኑት አቶ ያሬድ በክብር እንግድነት ተገኝተው ውድድሩን አስጀምረዋል። በጨዋታውም በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳታፊ የሆነው ሀድያ ሆሳዕና ከጨዋታ ብልጫ ጋር ከመመራት ተነስቶ 3-1 ማሸነፍ ችሏል።

ጥሩ እግርኳስ ባስመለከተን የመክፈቻ ጨዋታ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጎል የሀላባው አጥቂ ጀሚል ታምሬ በጥሩ አጨራረስ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተው ነበር። በውድድሩ የመጀመርያ ተሳታፊ የማይመስሉት ሀድያዎች በመጀመርያው አጋማሽ የነበራቸውን የአጨራረስ ክፍተት በሚገባ አርመው በመምጣት በአጥቂዎቻቸው ቃለአብ ውብሸት፣ ናትናኤል አረጉ እና ደስታ ዋሚሾ አማካኝነት አከታትለው ባስቆጠሩት ጎሎች ውጤቱን ቀልብሰው አሸንፈው በመውጣት በታሪክ የመጀመርያውን ከ20 ዓመት በታችውድድር ሦስት ነጥባቸውን አግኝተዋል። በሆሳዕና በኩል የመጀመርያውን ጎል ያስቆጠረው ቃልአብ ውብሸት ቀይ ካርድ የተመለከተ ቀዳሚ ተጫዋች ሆኗል።

በሁሉም ቦታ የሚገርም አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ያሳየን ሀድያ ምን አልባትም ለእነዚህ ታዳጊዎች በቂ ድጋፍ እና ክትትል ከተደረገ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በዋናው ቡድን የምንመለከታቸው ተጫዋቾች እንደሚኖሩ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

ረፋድ አራት ሰዓት በሊጉ ልምድ ያላቸው እና ጠንካራ ቡድኖች በመገንባት የሚታወቁት አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ያገናኘው ጨዋታ በመድኖች 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጥሩ የኳስ ፍሰት ያስመለከተን ይህ ጨዋታ መድኖች በዕለቱ በጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው በአሸናፊ ተስፋዬ ጎል መሪ ችለዋል። 

ከዕረፍት በፊት መድኖች ተጨማሪ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበት ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም አሸብር ደረጄ የመታውን የአዲስ አበባው ግብጠባቂ ብሩክ ወንድሙ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል። በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የመድኑ ተጫዋች መስፍን ዋሼ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር የአዲስ አበባዎችን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት አቀዝቅዞት ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር በኢትዮጵያ መድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አስር ሰዓት የተካሄደው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የአዳማ ከተማ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ እንደተጠበቀው በስታድየሙ የነበሩትን በርከት ያለ ተመልካች አዝናንቶ ተጠናቋል። ምንም እንኳ በርከት ያሉ ሙከራዎችን ባናይም የመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ የመጫወት ፍላጎት የተመለከትንበት ነበር። ከዕረፍት መልስ ከአስራ ስድስት ከሃምሳ ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት የቡድኑ አንበል እና ወሳኝ ተጫዋች ሄኖክ ማህቶት ግብጠባቂውን አቁሞ ድንቅ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ብዙም ሳይቆይ ተቀይሮ የገባው ፍሬው መሐመድ ከመስመር የተሻገረለትን ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የኢትዮ ኤሌክትሪክን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል። ጎል ይቆጠርባቸው እንጂ እንቅስቃሴያቸው መልካም የነበረው አዳማዎች በበረከት አበበ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታው በኢትዮ ኤሌትሪክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የምድብ ሀ በአሰላ ከተማ ጠዋት በተካሄዱ ጨዋታዎች መከላከያ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 ሲረታ ለመከላከያ ናትናኤል ሰለሞን እና ተሾመ ባልቻ ጎሎቹን ሰልመታ ኢብራሂም ለድሬ አስቆጥሯል። በማስከተል የተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ አንድ አቻ ሲጠናቀቅ የፈረሰኞቹን ዐወት ኪዳኔ፤ የድቻን ዘላለም አባተ አስቆጥሯል። የከሰዓቱ የወንድማማቾች ደርቢ የሀዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ቡና ተጠባቂ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በቀጣዮቹ ቀናት በውድድሩ ዙርያ የታዘብናቸውን ዐበይት ጉዳዮች ይዘን የምንመለስ መሆናችንን ከወዲሁ እንጠቁማለን።





© ሶከር ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *