ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ11ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ11ኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንዲህ መርጠናል።

አሰላለፍ : 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ታሪክ ጌትነት – አዳማ ከተማ

በተለዋዋጩ የአዳማ የግብ ጠባቂዎች አጠቃቀም ውስጥ ሁለተኛ ተከታታይ ዕድል ያገኘው ታሪክ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ቢገባበትም ቡድኑ በሰበታ በሰፊ ልዩነት እንዳይሸነፍ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። በጨዋታው ታሪክ ኢላማቸውን የጠበቁ አራት ከባባድ ሙከራዎችን ማዳን ችሏል።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

እስካሁን ሁሉንም የቡድኑን ጨዋታዎች ሙሉ ደቂቃ ተሰልፎ የተጫወተው ሄኖክ ጊዮርጊስ ሆሳዕናን በገጠመበት ጨዋታ በግራ መስመር ተከላካይነት ጀምሮ ወደ ቀኝ መስመር ተመላላሽነት ሚና ተዘዋውሮ እንደሁል ጊዜው የቡድኑን ማጥቃት ሲያግዝ ውሏል። የማጥቃት ደመ ነፍስ ያለው ተጫዋቹ በሳጥን ውስጥ ተገኝቶ በግል ጥረቱ ባስቆጠረው ጎሉ ቡድኑን ከሽንፈት ታድጓል።

ላውረንስ ላርቴ – ሀዋሳ ከተማ

ለሁለተኛ ጊዜ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት የቻለው ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ሀዋሳ ከተማ ከወልቂጤ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ባልተዛነፈ ትኩረት ተጫውቷል። የወልቂጤን የአየር ላይ እና የቅብብል ጥቃቶች ደጋግሞ በማቋረጥ አስፈላጊ ሰዓት ላይም ኃይልን በመጠቀም ቡድኑን ወደ ሽንፈት ሊወስዱ የሚችሉ ቅፅበቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓል።

ከድር ኩሊባሊ – ፋሲል ከነማ

ኩሊባሊ ከያሬድ ባየህ ጋር በፈጠረው ጥምረት ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ የፋሲል መረብ እንዳይደፈር በማድረጉ ቀጥሎበታል። የድሬዳዋ መልሶ ማጥቃት ስጋት በፈጠሩባቸው የጨዋታው ጊዜያት አይቮሪኮስታዊው የመሀል ተከላካይ እርጋታ በተሞላበት መከላከል ጥቃቶችን በቀላሉ በመቆጣጠር እና አደገኛ ኳሶችን በማራቅ የበኩሉን ተወጥቷል።

አሥራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና

የማይታየው ኮከብ ለሦስተኛ ጊዜ በስብስባችን ውስጥ ያካተተውን አስደናቂ ብቃቱን በሲዳማው ጨዋታ አስመልክቶናል። አንድ ግብ አስቆጥሮ አንድ በአቡበከር ወደ ግብነት የተቀየረ ኳስ ሲያመቻች የሀብታሙ ጎል እንዲቆጠርም መነሻ የሆነው ጥቃት ከአስራት የሁል ጊዜ የማጥቃት ድፍረት የተሞላ እንቅስቃሴ ነበር መነሻውን ያደረገው።



አማካዮች

ዳዊት እስጢፋኖስ – ሰበታ ከተማ

6ኛው ሳምንት ላይ ቡድኑ ጅማን ሲገጥም ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ያልተመለከትነው ዳዊት በተመለሰበት የጅማው ጨዋታ ድንቅ ቀን አሳልፏል። የቡድኑን ብቸኛ ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ከማስቆጠሩም በላይ ከኋላ ሆኖ የአማካይ ክፍሉ ላይ እርጋታን ሲጨምር ወደ ፊት በተጠጋባቸው ወቅቶች ደግሞ ሦስት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ፈጥሮ ነበር።

ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ

በምርጥ 11 ቢያንስ ተጠባባቂ ላይ የማይጠፋው ፍፁም ለአራተኛ ጊዜ በምርጥ ቡድናችን ውስጥ ተካቷል። በጅማው ጨዋታ የሁል ጊዜው ታታሪነቱ አብሮት የነበረው ፍፁም ቡድኑ ባልጠበቀው መንገድ በጊዜ በተመራበት ቅፅበት ክፍተት የማነፍነፍ ብቃቱን ተጠቅሞ አስደናቂ የመልሶ ማጥቃት ግብ በማስቆጠር ባህር ዳርን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።

በዛብህ መለዮ – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ በተሰጠው ግምት እና ግብ ለማስቆጠር ከነበረው ከፍ ያለ ጉጉት መነሻነት የማጥቃት ሂደቱ ተበታትኖ ሳለ የተቆጠረችው የበዛብህ መለዮ ጎል የጨዋታውን መልክ የቀየረች ቡድኑንም ወደ መረጋጋት ያመጣች ነበረች። ተጫዋቹ ከወልቂጤው አብዱልከሪም ወርቁ ልቆ ምርጫው ውስጥ እንዲገባም ጎሏ በጨዋታው ላይ የነበራት ዋጋ ከፍተኝነት ምክንያት ሆኗል።

አጥቂዎች

ተመስገን ደረሰ – ጅማ አባ ጅፋር

ሳምንቱ ልዩ ሆኖ ካለፈላቸው ተጫዋቾች መካከል ተመስገን ግንባር ቀደሙ ነው። ወደ ፊት አጥቂ ስፍራ በተመለሰበት ጨዋታ ሁለት የግል ብቃቱን አጉልተው ያሳዩ ግቦችን አስቆጥሮ ጅማ ከሦስት ጨዋታ በኃላ አንድ ነጥብ እንዲያሳካ አስችሏል። ተጨዋቹ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በድጋሚ የመስመር ተከላካይነት ሚናም ተወጥቷል።

ሀብታሙ ታደሰ – ኢትዮጵያ ቡና

በኢትዮጵያ ቡና የቡድን እንቅስቃሴ ውስጥ በታታሪነት የግራው የቡድኑ የማጥቃት እና የመከላከል ሂደት ላይ ሲሳተፍ የሚታየው ሀብታሙ በሲዳማው ጨዋታ ጥሩ አቋም ማሳየቱ እና እጅግ የተረጋጋ ጨራሽ እንደሆነ ባሳየበት አኳኋን ግብ ማስቆጠሩ እንዳለ ሆኖ በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች በቦታው የተሻለ ብቃት ያሳየ ተፎካካሪ ባለመኖሩ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ስብስባችን መጥቷል።

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

ወጣቱ አጥቂ ቡና ሲዳማን 5-0 በረታበት ጨዋታ ላይ ባሳየው ብቃት ለአራተኛ ጊዜ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ መካተት ችሏል። ሁለት ግብ የሆነን ኳስ አቀብሎ ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው አቡበከር በአንድ የውድድር ዘመን ሁለተኛ ሐት-ትሪክ በመስራት በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ውስጥ ከተካተቱ ቀደምት ከዋክብት መካከል ስሙን አስፈር ችሏል።

አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቡድኑ የዓመቱን ከፍተኛ ጎል አስቆጥሮ እንዲያሸንፍ ማድረግ ሲችሉ ከጨዋታ በፊት እንደተናገሩትም በተከላካይ መስመር ላይ ይሰሩ የነበሩ ስህተቶችን በመቀነስ ኢትዮጵያ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ አስችለውታል፡፡

ተጠባባቂዎች

ፅዮን መርዕድ – ባህር ዳር ከተማ
ተስፋዬ ነጋሽ – ወልቂጤ ከተማ
ቶማስ ስምረቱ – ወልቂጤ ከተማ
አብዱልከሪም ወርቁ – ወልቂጤ ከተማ
ሬድዋን ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ
ምንይሉ ወንድሙ – ባህር ዳር ከነማ


© ሶከር ኢትዮጵያ