የፋሲል ተጫዋቾች እና የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ?

ለብሔራዊ ቡድን አገልግሎት ጥሪ የተደረገላቸው አምስቱ የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቀጣይ ለሚኖርባቸው ወሳኝ ጨዋታ ለሁለተኛ ምዕራፍ ዝግጅታቸው 28 ተጫዋቾችን ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል። በዛሬው ዕለት ከ10:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ የቡድኑ አባላት ዝግጅታቸውን እያደረጉ መሆናቸውን በስፍራው በተገኘንበት ወቅት መመልከት ችለናል። ሆኖም ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል የፋሲል ከነማዎቹ ያሬድ ባዬ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ሽመክት ጉግሳ እና ሙጂብ ቃሲም በቦታው በመገኘት ልምምድ እየሰሩ አለመሆናቸውን አረጋግጠናል።

ምክንያቱ ምን ይሆን ብለን በፌዴሬሽኑ በኩል ስንጠይቅ በጉዳዩ ላይ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ፤ ካለም አጣርተው እንደሚነግሩን ገልፀውልናል። ያም ቢሆን ሙጂብ ቃሲም ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ተነጋግሮ ፍቃድ መጠየቁን የሰማን ሲሆን የቀሩት ተጫዋቾች ምክንያት ምን እንደሆነ ግን ከሁለቱም ወገን መረጃ አላገኘንም። ምን አልባት ክለቡ ተጫዋቾቹ ከነበረባቸው ተደራራቢ ጨዋታ አንፃር ዕረፍት እንዲያደርጉ ታስቦ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ መሆናችንን ከወዲሁ እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ