የሲዳማ ቡና ቦርድ የተለያዩ ለውጦች ለማድረግ ከውሳኔ ደርሷል

ሲዳማ ቡና ካጋጠመው የውጤት ቀውስ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የክለቡ ቦርድ የተለያዩ ለውጦችን ለማድረግ ስብሰባ አከናውኗል፡፡ በስብሰባውም አዳዲስ ውሳኔዎች ተወስነዋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከ2002 አንስቶ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው እና በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የሚታወቀው ሲዳማ ቡና ዘንድሮ በሊጉ ባለፉት ዓመታት ሲያስመዘግብ የነበረውን ውጤት የማስቀጠል ችግር በመታየቱ ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች አፋጣኝ ለውጥን ለማድረግ በማሰብ አዳዲስ ውሳኔዎችን ማስተላለፉ ታውቋል፡፡ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ ካደረጋቸው አስር የሊጉ ጨዋታዎች በአምስቱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ወጥቶ በቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ድል አስመዝግቦ በደረጃ ሰንጠረዡ በያዘው አስራ አንድ ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የአዲስ አበባ እና የጅማን ቆይታ አጠናቆ ወደ ባህር ዳር በዚህ ሳምንት ያመራል፡፡

ቡድኑ ወደ ባህር ዳር ከሚያደርገው ጉዞ በፊት የክለቡ ቦርድ በዛሬው ዕለት ስብሰባን አድርጓል፡፡ በስብሰባውም ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ክለቡን ከ1998 ጀምሮ በሥራ አስኪያጅነት እና በቡድን መሪነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ መንግሥቱ ሳሳሞን ከሀላፊነት ስለማንሳት መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ አቶ መንግሥቱ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳሉት ከሆነ ደግሞ ከቀናት በፊት የመልቀቂያ ደብዳቤን ያስገቡ ሲሆን ምናልባትም በነገው ዕለት በይፋዊ ደብዳቤ ከክለቡ ጋር እንደሚለያዩ ለማወቅ ችለናል፡፡

በተመሳሳይ ክለቡን በተጫዋችነት እና በአምበልነት ከ2009 ጀምሮ ደግሞ ከረዳት አሰልጣኝነት እስከ ዋና አሰልጣኝነት በመምራት ክለቡን ጠንካራ ተፎካካሪ ሲያደርግ የነበረው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እና ረዳት አሰልጣኙ ያሬድ ገመቹን ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ለማሰናበት ከውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ምንም እንኳን ክለቡ እንደወሰነ ይሰማ እንጂ በደብዳቤ አለማሳወቁን እና በነገው ዕለት ግን ይህን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ባደረግነው ማጣራት አረጋግጠናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ