የሊግ ካምፓኒው ውድድሮች የሚካሄድባቸውን ከተሞች አስቀድሞ የመገምገም ተግባሩን ቀጥሎ የድሬዳዋን ቅድመ ዝግጅት እየተመለከተ ይገኛል።
የቤትኪንግ በፕሪምየር ሊግ በአምስት በተመረጡ ከተሞች እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። አስራ አንደኛ ሳምንት በደረሰው የዘንድሮ ውድድር አዲስ አበባ እና ጅማ ከተማ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ሌላኛዋ ከተማ ባህር ዳር ማስረከባቸው ይታወቃል። አወዳዳሪው አካል ከተለያዩ መመዘኛዎች አንፃር የስከመጣቸውን መስፈርቶች የተመረጡት ከተሞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ምን እየሰሩ ነው በማለት በቅርቡ በባህር ዳር ያደረገውን ምልዕከታ አጠናቆ መመለሱን መዘገባችን ይታወቃል።
ከሰኞ ጀምሮ ደግሞ የሊግ ካምፓኒው የቦርድ አባል አቶ አሰፋ ሀሲሶ፣ የውድድር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ተገኔ ዋልተ ንጉስ እና ኮሚሽነር ሚካኤል አርዓያ የተመራ የልዑክ ቡድን ከመጋቢት 24 እስከ ሚያዝያ 15 ቀን የሚካሄደውን ከ17ኛ እስከ 21ኛ ሳምንት ድረስ የምታዘጋጀው ምስራቃዊቷ ከተማ ድሬደዋን ለውድድሩ እያደረገች ያለውን ዝግጅት እየገመገሙ ይገኛል።
ለውድድሩ የሚያስፈልጉ የልምምድ ሜዳዎች የኮቪድ ምርመራ የፀጥታ ሁኔታ የህክምና ማዕከል እና የመጫወቻ ሜዳውን ተዟዙረው የተመለከቱ መሆኑን ሰምተናል። በተለይ የመጫወቻ ሜዳው በቀሩት ጊዚያት በቂ ክትትል እንዲደረግበት እና ሌሎች መስተካከል የሚገባቸው እንዲስተካከሉ መንገራቸው ተገልጿል።
የልዑክ ቡድኑን በቢሯቸው ያናገሩት የአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮምሽን ኮምሽነር ሻኪር አህመድ እና ድሬዳዋ አስተዳደር ከተማ ሥራ አስኪያጅ ኃላፊና የክለቡ ቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ የተሰጠውን አስተያየት እንደ ግብዓት በመጠቀም ውድድሩን ከሚጠበቀው በላይ ለማዘጋጀት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የሊግ ካምፓኒው ውድድሩ ከሚጀመርበት ቀናት በፊት አዘጋጅ ከተሞች ያሉበትን ሁኔታ ተዟዙሮ መገምገሙ ችግሮችን ለመቀነስ የሚረዳ በመሆኑ መለመድ ያለበት በጎ ተግባር መሆኑን እንገልፃለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ