የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የአንደኛው ዙር ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2013 የአንደኛ ዲቪዚዮን የአንደኛ ዙር ጨዋታዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ በውድድሩ ላይ ጥሩ አቋም ያሳዩ ምርጥ ተጫዋቾችን በማካተት የዙሩን ምርጥ ቡድን ሰርተናል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የ2013 የውድድር ዓመት የመጀመሪያው ዙር መርሐ ግብር ከታህሳስ 10 እስከ ጥር 21 ድረስ በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት ሲደረግ ቆይቶ ከሰሞኑ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በውድድሩ ላይ በርካታ ተስፋ ሰጪ እና ሊበረታቱ የሚገባቸውን ተጫዋቾችን መመልከትም ተችሏል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም እስከ አሁን በተደረጉ የዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ ሽፋን ስትሰጥ መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ በወጥነት ክለባቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ ተጫዋቾችን በማካተት የዙሩን ምርጥ ቡድን ይፋ ታደርጋለች፡፡ ምርጫው ሊጉን ሲከታተሉ የነበሩ የእግር ኳስ ባለሙያዎች ፣ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ፣ በቦታው የነበሩ ጋዜጠኞችን ጭምር በማስተባበር የተደረገ ነው፡፡

አሰላለፍ ፡ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ታሪኳ በርገና – መከላከያ

በውድድሩ ላይ በርከት ያሉ አስደናቂ ግብ ጠባቂዎችን መመልከት ብንችልም በሜዳ ላይ ሙሉ የተጫዋችነት ክህሎቷን በወጥነት በማሳየት የታሪኳ በርገናን ያህል የሆነች ግብ ጠባቂ አለች ለማለት አያስችልም፡፡ ተጨዋቿ በስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፋ የተጫወተች ሲሆን በየጨዋታው ታሳይ ከነበረው አስደናቂ ብቃቷ በተጨማሪ በሦስት ጨዋታዎች ላይ ግብ አላስተናገደችም፡፡

ተከላካዮች

ብዙዓየሁ ታደሰ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የቀድሞዋ የቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ መስመር ተጫዋች በመጀመሪያ አሰላለፍም ሆነ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስታ ስትጫወት ኳስን መሠረት ባደረገው አጨዋወቷ ለንግድ ባንክ የማጥቃት አማራጭ ስትሆን ተመልክተናታል፡፡ በተለይ ከመከላከሉ ወደ ማጥቃቱ በሚደረግ ሽግግር ውስጥ ለአጥቂዎች ኳስን በማሻገሩ ረገድ ንግድ ባንኮች ሲተገብሩ ለነበረው የአጨዋወት መንገድ የብዙአየው ሚና ከፍ ያለውን ቦታ ይወስዳል፡፡

ፅዮን እስጢፋኖስ – መከላከያ

በሥነ ምግባራቸው ከሚመሰገኑ ሴት ተጫዋቾች መሐል የሆነችው አንበሏ ቡድኗን ከመምራት ባለፈ በመሀል የተከላካይ ስፍራ ላይ ተሰልፋ በምታሳየው ቀልጣፋ እንቅስቃሴ አጥቂዎችን መፈተን ችላለች፡፡ በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ከተጫዋች ኳስን ስትነጥቅ እና የቡድኗን ማጥቃት ስታስጀምር የነበረበት መንገድ የቅርብ ጊዜ የማስተርስ ተመራቂዋን ተመራጭ አድርጓታል፡፡

ትዝታ ኃይለሚካኤል – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ በሊጉ ወጥነት ቢጎለውም ይህቺ ተከላካይ በግሏ የነበራት ወጥነት ብዙሀኑን ያስገረመ ሆኗል፡፡ ኳስን በማስጣሉም ሆነ በተደጋጋሚ ያለቀላቸው ዕድሎች ወደ ጎልነት እንዳይለወጡ ተንሸራታ በማውጣት ቡድኗን ስትታደግ የነበረበት መንገድ ላቅ ያለ ሲሆን ረጅም ልምዷን በመጠቀም ሀዋሳ ባደረጋቸው የዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ በሙሉ ተሰልፋ መጫወት ችላለች፡፡

ነፃነት ፀጋዬ – መከላከያ

ክለቡን በአዲስ መልኩ ብትቀላቀልም በቡድኑ ውስጥ ረጅም ጊዜ የቆየች የምትመስለው ነፃነት ለመከላከያ የማጥቃትም ሆነ የመከላከል ሂደት ያደረገቻቸው አስተዋፅኦዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ በተለይ ከግራ አቅጣጫ ለቡድን አጋሮቿ ሴናፍ ዋቁማ እና መዲና ዐወል በረጅሙ ስትጥልላቸው ከነበሩ ኳሶች ለቡድኑ ውጤት ማማር ጉልህ ድርሻ ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡



አማካዮች

ማዕድን ሣህሉ – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከመጥፎ አጀማመሩ እያገገመ ወደ ውጤት ጎዳና ሲሸጋገር ወጥነት ይንፀባረቅባት የነበረችው ተጫዋቿ ኳስን ለቡድን ጓደኞቿ እያደራጀች ስታቀብል አጥቂዎች በተደጋጋሚ ላስቆጠሯቸው ጎሎች የሷ ሚና ትልቁን ቦታ ሲይዝ ታይቷል፡፡ የድሬዳዋ የውጤታማነት አንዱ ሚስጥርም እሷ የመሀል ሜዳውን በታታሪነት በተሰጣት ኃላፊነት ልክ መጥቀም መቻሏ ነበር፡፡

ኤደን ሺፈራው – መከላከያ

የቡድኗን ሚዛን በመጠበቅ እና ኳስን ከቡድን ጓደኞቿ ጋር በጣምራ በቅብብል ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሶ ጎል እንዲቆጠር ያደረግ በነበረው ሂደት ውስጥ ተደጋጋሚ አስተዋጽኦዋ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከማጥቃቱ ባሻገር በመከላከሉ ረገድ ለተከላካዮች ሽፋን በመስጠት እና በተቃራኒ ቡድን የመሀል ሜዳ ብልጫ እንደዳይወሰድ በየጨዋታው የምታደርገው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በምርጥነት እንድትካተት አድርጓታል፡፡

ሰናይት ቦጋለ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የቀድሞዋ የደደቢት እና አዳማ ከተማ አማካይ ወደ ንግድ ባንክ ካመራች በኋላ ለክለቡ ውጤታማ የአንደኛ ዙር ጉዞ የነበራት ድርሻ ቀላል የሚባል አደለም፡፡ አስፈሪነታቸው በተደጋጋሚ ለተስተዋለው የንግድ ባንክ አጥቂዎች የተደራጀ ኳስ ማግኘት እንዲችሉ በማቀበሉም ሆነ የመሀል ሜዳውን በሚገባ በመቆጣጠር በዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ ቡድኗ ውጤታማ እንዲሆን የበኩሏን አድርጋለች፡፡

አጥቂዎች

ረሂማ ዘርጋው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከሎዛ አበራ በመቀጠል አስር ጎሎችን አስቆጥራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘዋ ታታሪዋ አጥቂ ለንግድ ባንክ የተዋጣለት የስኬት ጉዞ ግንባሩን ቦታ ትይዛለች፡፡ ቡድኗ ኳስ ሲያገኝ ከፊት ትገኝ የነበረችው አጥቂዋ በአንፃሩ ሲጠቃ ወደ ኋላ በመሳብ የምትሰጠው ግልጋሎት አስደናቂ ነበር፡፡ ቡድኑ የተቀዛቀዘ ስሜት ሲታይበት በማነቃቃቱም የአምበልነቷን ሚና በመወጣቱ ሲሳካላት ታይታለች፡፡

ሎዛ አበራ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከቢርኪርካራ መልስ በሊጉ የመጀመሪያው ዙር ደካማ አጀማመር ብታደርግም በሂደት ግን ወደለመደችሁ ጎል አስቆጣሪነት በመመለስ ለቡድኗ የስኬት ጉዞ ቁልፍ መሆን ችላለች፡፡ ኳስ ስታገኝ የመጨረሻው የውሳኔ አሰጣጧ አስደናቂ የነበረ ሲሆን ወደ መሀል ክፍሉ ተስባ በመጫወትም ጭምር ለቡድኗ ስኬት አስፈላጊ የነበሩ አስራ አንድ ጎሎችን አስቆጥራ በኮከብ ግብ አስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚ መሆን እላለች፡፡

አረጋሽ ካልሳ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከተፈጥሯዊ የመሀል ሜዳ ተጫዋችነቷ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው አማካኝነት ወደ ግራ መስመር አጥቂነት ከተሸጋገረች በኃላ የተሰጣትን ሚና በአግባቡ ስትጠቀምበት ተመልክተናል፡፡ ስድስት ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈች ሲሆን ወደ ጎልነት የተለወጡ ኳሶችን ስታቀብል ተስተውሏል፡፡ ንግድ ባንክ ተጫዋቿን በአንድ አጋጣሚ በጉዳት ሲያጣት በእንቅስቃሴ ተዳክሞ የታየ ሲሆን ወደ ሜዳ ከተመለሰች በኃላ ግን በርካታ ግቦችን ወደማቆጠሩ ተመለሷል፡፡

አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አሰልጣኙ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጉን በመሪነት እንዲያጠናቅቅ ከማስቻላቸውም በላይ የ100% የማሸነፍ ውጤትን ይዞ እንዲዘልቅ በማድረጋቸው የዚህ ዙር ምርጥ አሰልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ተጠባባቂዎች

ንግስቲ መዐዛ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ጥሩአንቺ መንገሻ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ፀሐይነሽ በቀለ – ድሬዳዋ ከተማ
ሕይወት ረጉ – መከላከያ
እፀገነት ግርማ – ጌዲዮ ዲላ
መሳይ ተመስገን – ሀዋሳ ከተማ
ሴናፍ ዋቁማ – መከላከያ


© ሶከር ኢትዮጵያ