የሀዋሳ ዝግጅት በሊግ ካምፓኒው ተገመገመ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የውድድር ዘመኑ የመጨረሻ አምስት ሳምንታት ጨዋታዎች እንድታስተናግድ ወደተመረጠችው ሀዋሳ በማቅናት የከተማዋን ዝግጅትገምግሟል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቤትኪንግ ስፖንሰር አድራጊነት ጅማሮን ካደረገ እነሆ ሦስተኛ ወሩ ላይ ይገኛል፡፡ በሱፐር ስፖርት ለብዙሃኑ ተመልካቶች እየደረሰ የሚገኘው ሊጉ ያለፉትን አስራ አንድ የሊግ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ላይ አከናውኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ቀጣይ አምስት ሳምታትን በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋል፡፡ ከባህር ዳር በመቀጠል የድሬዳዋ ስታዲየም የሁለተኛውን ዙር የሚያስተናግድ ሲሆን የመጨረሻ ሳምንታት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በሀዋሳ ይደረጋል፡፡በዛሬው ዕለትም የሊግ ካምፓኒው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና የካምፓኒው የፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በሀዋሳ በመገኘት ለውድድሩ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ገምግመዋል፡፡

የሊግ ካምፓኒው ቀደም ብሎ የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ለውድድሩ መርጦ የነበረ ቢሆንም የመጫወቻ ሳሩ ያልተተከለ በመሆኑ ሜዳውን ለመሰረዝ የተገደደ ሲሆን እንደ አማራጭ የቀረበውንም የአርቴፊሻል ሜዳን ቢመለከትም ለውድድሩ የቀረፃ ሁነት ምቹ ባለመሆኑ ለመሰረዝ ተገዷል፡፡ እንደ አማራጭ በሦስተኝነት ተይዞ የነበረው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ግን በሊግ ካምፓኒው ተወካዮች ከታየ በኃላ የመጫወቻ ሳሩ ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተቀየረ ውድድሩን እንዲያስተናግድ መመረጡን የሊግ ካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከዋናው የመጫወቻ ሜዳው ባሻገር በመቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የተመራው ልዑክ አምስት በከተማዋ የሚገኙ የመለማመጃ ሜዳዎች፣ የኮቪድ መመርመሪያ ማዕከላት እና ሆቴሎችን ተዟዙሮ ተመልክቷል፡፡

አቶ ክፍሌ የመለማመጃ ቦታዎች እና ሆቴሎች በበቂ ሁኔታ መኖራቸውን እንደተመለከቱ የተናገሩ ሲሆን አስተናጋጁ ከተማም የመጫወቻ ሜዳውን በአጭር ጊዜ እንዲያስተካክል ትዕዛዝ መሰጠቱን አክለዋል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከሀያ አምስት ቀናት በኃላ በድጋሚ የሚመለከት አካል ተልኮ የሚታይ ሲሆን የመጫወቻ ሜዳው ለውጥ ከሌለው ግን ወደ ሌላ አማራጭ የሀገሪቱ ስታዲየም ፊቱን እንደሚያዞር ገልፀውልናል፡፡ የሲዳማ ክልል የእግር ኳስ ፌድሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ በበኩላቸው ከነገ ጀምሮ የመጫወቻ ሳሩን በፍጥነት ለማደስ እንደተዘጋጁ ለሊግ ካምፓኒው ቃል ገብተዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ