የከፍተኛ ሊጉ አወዳዳሪ አካል ለቀረበበት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።
ምክትል ኃላፊው ሻምበል ሀለፎም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ በተነሱባቸው ቅሬታዎች ዙሪያ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በከፍተኛ ሊጉ የምድብ ሀ ጨዋታዎች መከናወኛ ቦታ ሀዋሳ ሆኖ የወስነበትን ምክንያት እንደሚከተለው አብራርተዋል።
“ውድድሩን ለማካሄድ ኮሚቴው ብዙ ቦታዎችን በአካል ሄዶ ለመመልከት ሞክሯል። ከታዩት ቦታዎችም ውስጥ ወልዲያ ፣ ነቀምቴ ፣ ድሬዳዋ እና አዳማ ሌሎችም ቦታዎች ይገኙበታል። ክለቦች በቅሬታቸው ያነሷቸው ቦታዎችም እንዲሁ ታይታዋል። ለምሳሌ አዳማ የ20 ዓመት በታች እና የሴቶች ውድድሮችን የሚያስተናግድ በመሆኑ ለመምረጥ ከባድ ነው። ድሬዳዋም እንዲሁ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ወልዲያም ራሱ ተጋጣሚ ክለብ በመሆኑ በነቀምቴም የተያዘ ፕሮግራም በመኖሩ ወዳዛ መውሰድ አልተቻለም። ሆኖም ነፃ የሆነው እና ለውድድሩ የመጀመሪያ አማራጫችን የነበረው ሀዋሳ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ባቱ ላይ ይወዳደሩ የነበሩ የምድብ ሀ ክለቦች የኮቪድ 19 ምርመራ ለማድረግ ሲቸገሩ እና ከፍተኛ ወጪ ሲያወጡ ነበር። የምርመራው ውጤት ለማዋቅ ከባቱ ከተማ ውጭ ደርሶ መምጣቱ ወጪውን ስላናረው ይህንን ችግር ለመፍታትም ሀዋሳ የተሻለ አማራጭ ሆኗል። የአየር ንብረቱም ተመሳሳይ ስለሆነ የምድብ ሀ ጨዋታዎች ሀዋሳ ላይ እንዲካሄድ ወስነናል።
“ውሳኔው በአንድ እና በሁለት ሰው የተወሰነ ነው መባሉም የተሳሳተ ነው። ይህ ውሳኔ ሲወሰን አዲስ አበባ ያሉት አራት የኮሚቴ አባላት ፣ ዋና ሰብሳቢው አቶ ዓሊሚራህ እና እኔ ተሳትፈንበታል። አወዳዳሪው አካል የውድድር ቦታ እና ሳዓት መምረጥ እንደሚቻል በደንባችን እንዳለ ይታወቃል ክለቡች ማወቅ ያለባቸው ይህን ቦታ ለመወሰን የመወዳደሪያ ቦታዎችንም ስንመርጥ ተሳታፊዎች እንዳይቸገሩ እንደነሱ ሆነን ነው ስንመርጥ የነበረው። አንዱን ክለብ ከሌላው ለይተን ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራነው ምንም ዓይነት ስራ የለም። ክለቦች ይህንን ሊያያውቁ እና ሊገነዘቡ ይገባል።
“ከዚህ በተጨማሪ የሃያ ቀናት ዕረፍቱን እና የዝውውሩን ሁኔታ እየመከርንበት እንገኛለን። አወዳዳሪው አካል የውድድሩ የሚጀምርበትን ቀን ዕኩል ለማድረግ ሀሳብ አለው። ሀሳቡን በተመለከተ ውሳኔ ላይ ስንደርስ ለክለቦች የምናሳውቅ ይሆናል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ