በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አዲስ ሀሳብ መነሻነት እየተካሄደ የሚገኘው የብሔራዉ ቡድኑ ዝግጅት ሁለተኛ ምዕራፍ ከስድስት ቀናት ልምምድ በኋላ ዛሬ ተጠናቋል።
ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ወሳኝ ጨዋታዎች በቀጣይ ወር ከማዳጋስካር እና አይቮሪኮስት ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ 28 ተጫዋች በመጥራት የካፍ ልህቀት ማዕከል ማረፍያውን አድርጎ የሁለተኛ ምዕራፍ ዝግጅትን ባሳለፍነው ሰኞ መጀመሩ ይታወቃል።
ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል የፋሲል ከነማዎቹ ያሬድ ባዬ አምሳሉ ጥላሁን ሀብታሙ ተከስተ እና ሽመክት ጉግሳ እስካሁን ቡድኑን ሳይቀላቀሉ የቀሩ ሲሆን ሙጂብ ቃሲም ከሦስት ቀን በፊት ብሔራዊ ቡድኑን በመቀላል ልምምድ ሲሰራ ተመልክተነዋል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በስድስት ቀን የልምምድ ቆይታው በጨዋታ ወቅት ሊተገብሩ ያሰቡትን ኳስን ተቆጣጥሮ ማጥቃት እና መከላከልን መሠረት ያደረገ አጨዋወትን በተደጋጋሚ ሲሰሩ ተመልክተናል።
በዛሬው የመጨረሻ ቀን ልምምዳቸው አቤል ያለው ያደረገው ጫማ እግሩን በመላጡ ባጋጠመው መጠነኛ ህመም ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሳይሰራ ሲቀር አቡበከር ናስር ኢትዮጵያ ቡና በጅማ ከተማ በነበረው ቆይታ የግራ እጁ ጀርባ ላይ ያጋጠመው ህመም ስሜቱ እየተነሳበት የተወሰኑ ልምምዶችን ሰርቶ እረፍት እንዲያደርግበት ወጥቷል። በተመሳሳይ ሀይደር ሸረፋም ቀለል ያለ ልምምድ ሠርቶ እረፍት እንዲያደርግ መውጣቱን ተመልክተናል።
የሁለተኛ ምዕራፍ ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ብሔራዊ ቡድኑ መጋቢት ወር ላይ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚያደርጉት የመጨረሻ የተጫዋቾች ጥሪ አማካኝነት ጨዋታውን በሚያከናውኑበት ባህር ዳር ከተማ የሚዘጋጁ ይሆናል።
በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት ዙርያ ለሚዲያ አካላት በሚጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ