የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ እና ሐ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ የተጠናቀቁ ሲሆን በምድብ ለ ሻሸመኔ ከተማ በጎል ተንበሽብሾ ኢኮሥኮን ሲረታ ጅማ አባ ቡና እና ቡታጅራም ድል አስመዝግበዋል።
ምድብ ለ
የረፋዱ የኢኮሥኮ እና ሻሸመኔ ጨዋታ ሰባት ጎሎችን አስመልክቶን በሻሸመኔ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የኢኮሥኮዎች የጨዋታ የበላይነት በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ ኳስን በማንሸራሸር ወደ ሻሸመኔ የግብ ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችልም ጎል ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ግን ደካማ ነበር፡፡ ለዚህም ማሳያ በ8ኛው ደቂቃ ቤዛ መድህን ሁለት የሻሸመኔ ተጫዋቾችን አልፎ ነፃ አቋቋም ለነበረው ቃለፍቅር መስፍን ሰጥቶት ተጫዋቹ አስቆጠረው ሲባል የሻሸመኔ ከተማውን ግብ ጠባቂ ግዛቸው ሀብቴን ያሳቀፈበት አጋጣሚ ይጠቀሳል፡፡ ሻሸመኔ ከተማዎች በዚህኛው አጋማሽ መረጋጋት ቢሳናቸውም በረጃጅሙ ከሚሻገሩ አልያም ከርቀት በሚመቱ አደገኛ ኳሶች ሙከራ ለማድረግ ቃጥተዋል፡፡ 24ኛው ደቂቃ ላይ ለኢኮሥኮ በተደጋጋሚ ጎሎችን ሲያስቆጥር የሚታየው ወጣቱ አማካይ ቤዛ መድህን ቡድኑን መሪ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ በኳስ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ የእንቅስቃሴ ይዘትን የተገበሩ ቢሆንም የአማካይ ተጫዋቾችን በመቀየር ረጃጅም ኳሶችን ወደ አጥቂዎች ሲልኩ በተደጋጋሚ የተስተዋሉት ሻሸመኔ ከተማዎች የኢኮሥኮ ተከላካዮች ስህተትን በመጠቀም ወደ ጨዋታ መመለስ ችለዋል፡፡ ፀጋ ጎሳዬ ከርቀት በሞከራት አደገኛ አጋጣሚ ወደ ጎል መጠጋት የቻሉት ሻሸመኔዎች ጥረታቸው ሰሞሮ 52ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል፡፡ ተቀይሮ የገባው የኢኮሥኮው ተከላካይ አቡበከር ጀማል ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ማናዬ ፋንቱ ወደ ጎልነት ለውጧት ሻሸመኔን አቻ አድርጓል፡፡
ከእንቅስቃሴ ውጪ በስህተት የተሞላው የኢኮስኮ የተከላካይ ክፍል መረጋጋት እየተሳነው መሞጣቱ ይበልጥ ለሻሸመኔ አጥቂዎች እንደፈለጉ እንዲቦርቁ ዳርጓቸዋል፡፡ 58ኛው ደቂቃ የቀድሞው የኤሌክትሪክ የግራ ተከላካይ ዳንኤል ራህመቶ ያሻማውን ማናዬ ፋንቱ በድጋሚ በሚስቆጠር ሻሸመኔን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሻግሯል። ተጋላጭነታቸው ቢስተዋልም ኳስን ሲይዙ ወደ ፊት ለመሄድ የማይቸገሩት ኢኮሥኮዎች ከመሀል ሜዳ በተገኘች ኳስ 65ኛው ደቂቃ ላይ በበየነ ባንጃው አማካኝነት ጎል አስቆጥረው 2 ለ 1 ሆነዋል፡፡
የቀድሞው የኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ አጥቂ ማናዬ ፋንቱ ለሻሸመኔ አከታትሎ በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሰርቷል፡፡ 76ኛው ደቂቃ ላይ እሸቱ መና ከመሐል ሜዳ በረጅሙ ያሻገረለትን በኃይሉ ወገኔ አማካኝነት አራተኛ ጎላቸው ከመረብ አዋህደው የግብ መጠናቸውን ማስፋት ችለዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወገኔ ሌላ ግብ አክሎ ሻሸመኔ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን 5-2 በሆነ ውጤት አሳክቷል።
8፡00 ላይ ሀላባ ከተማን ከ ቤንች ማጂ ቡና ሁለት አቻ ተለያይተዋል፡፡ ብርቱ ፉክክር በታየበት እና ለዕይታ ማራኪ በነበረው ጨዋታ የአሰልጣኝ ወንዳየው ኪዳኔው ቤንች ማጂ በረጃጅም ኳሶች ወደ አጥቂዎች በሚላኩ የተሳኩ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን ሀላባ ከተማዎች ከወትሮው የመሀል ሜዳ ክፍል እንቅስቃሴ ይልቅ ወደ መስመር ባደላ እና ወደ አጥቂው እዩኤል ሳሙኤል በሚጣሉ ክኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ታትረዋል፡፡
በጎል ቀዳሚ የነበሩት ቤንችማጂ ቡናዎች ነበሩ፡፡15ኛው ደቂቃ ላይ ለቤንች ማጂዎች ጥሩ የሜዳ ላይ አቅሙን ሲያሳይ የነበረው ኦኒ ኡጁሉ ያሻገረለትን ኳስ ወልዲያን ከለቀቀ በኃላ በክለቡ አራተኛ ዓመቱን እያሳለፈ የሚገኘው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኤሪክ ኮልማን በመጀመሪያ ጨዋታው ያገኛትን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ማጥቃት ወረዳው በይበልጥ ተጠግተው ለመጫወት የጣሩት ሀላባ ከተማዎች በውብሸት ስዩም አስደንጋጭ ሙከራን ከርቀት አድርገው በሌሊሳ ታዬ ከተመለሰባቸው በኋላ 24ኛው ደቂቃ ላይ አቡሽ ደርቤ የሰጠውን ኳስ የቀድሞው የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋች እዩኤል ሳሙኤል በቀላሉ አስቆጥሮ ሀላባ ከተማን 1-1 አድርጓል፡፡ ጨዋታው በዚሁ ቀጥሎ 28ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከመስመር የተጣለለትን ኳስ ኤሪክ ኮልማን በድጋሚ ለክለቡ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ቤንች ማጂ ቡናን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል ቡድኖቹ አምርተዋል፡፡
ከዕረፍት በኋላ 57ኛው ደቂቃ ላይም ሀላባዎች ጎል አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ የተባለባቸው ሲሆን የሀላባ የቡድን አባላትም አግባብ ያልሆነ ውሳኔ ነው በሚል ረዳት ዳኛው ላይ የቴክኒክ ክስ አስመዝበው ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ አቻ ለመሆን ሲጥሩ የነበሩት ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ካሜሩናዊው ሮጀር ኡኩሜ ሀላባ ከተማን አቻ በማድረግ ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል፡፡
የቀኑ ሦስተኛ እንዲሁም የዘጠነኛ ሳምንት መርሀ ግብር ማሳረጊያ በጅማ አባቡና እና ካፋ መካከል ተደርጎ በሂደት እየተሻሻሉ በመጡት አባ ቡናዎች 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው በፍላጎትም ሆነ በሜዳ ላይ ሚዛኑን የጠበቀ አጨዋወትን በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያስመለክቱን የነበሩት ጅማ አባ ቡናዎች ከቀኝ በኩል ታከለ ታንቱ የሰጠውን ኳስ ሱራፌል ፍቃዱ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ጅማን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም ሙከራዎችን መመልከት ያልቻልን ቢሆንም ካፋ ቡናዎች በይበልጣል አዳሙ እና አረጋኸኝ ማሩ አማካኝነት ከርቀት የሞከሩ ሲሆን እምብዛም ሊጠቀስ የሚችል የጠራ አጋጣሚን ሳንመለከት ጨዋታው በጅማ አባ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል፡፡ ጅማ አባቡናም ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን ካለ ደመወዝ በሚጓዙት ተጫዋቾቹ ታግዞ አሳክቷል፡፡
በዚህ የጅማ አባ ቡና እና ካፋ ቡና ጨዋታ ላይ በኮቪድ 19 ተይዘዋል የተባሉ የካፋ ቡና ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የተገኙ ሲሆን አወዳዳሪው አካልም ተጫዋቾቹ መኖራቸውን ተመልክቶ ከሜዳ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ በተደጋጋሚ በክለቦች ግድ የለሽነት ቫይረሱ የተገኘባቸው ተጫዋቾች በማገገሚያ መቀመጥ ሲገባቸው በሜዳ ላይ ከተመልካች ጋር መታየታቸው በአፋጣኝ ሀይ ሊባል የሚገባ ድርጊት መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ምድብ ሐ
2:00 ላይ የድሬዳዋ ስታድየም የአርሲ ነገሌን እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ጨዋታ በዘጠነኛ ሳምንት የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ አስተናግዶ ያለ ጎል 0-0 ተደምድሟል፡፡
በመቀጠል 4፡00 ሲል ባቱ ከተማን ከ ጌዲኦ ዲላ ያገናኘ ሲሆን የአሰልጣኝ ኤፍሬም ባቱ በ27ኛው ደቂቃ ሄኖክ ታደሰ ከመረብ ባሳረፋት ብቸኛ ጎል ሙሉ ሦስት ነጥብን ሊጨብጥ ችሏል፡፡
ከሰአት 9፡00 የምድቡ ሦስተኛ መርሐ ግብር በቡታጅራ ከተማ እና ሺንሺቾ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ውጤት እየራቀው የመጣው ሺንሺቾ ገና በ3ኛው ደቂቃ በአምበሉ ሚሊዮን ካሳ አማካኝነት በፍፁም ቅጣት ምት ቀዳሚ የነበሩ ቢሆንም አቤል ሽጉጤ እና ሙሴ ክንዴ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ጎሎች ቡታጅራ ከተማ 2-1 አሸናፊ አድርገዋል፡፡
ከጨዋታዎች መጀመር በፊት ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ሳህለማርያም ክፍሌ የህሊና ፀሎት ተደርጎላቸዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ