ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ በአሸናፊነቱ ሲቀጥል አአ ከተማ እና ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አስረኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ንግድ ባንክ ሲያሸንፍ አዲስ አበባ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ረፋድ አራት ሰዓት የተካሄደው የአርባምንጭ ከተማ እና የንግድ ባንክ ጨዋታ በንግድ ባንክ 5–0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሊጉ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው መጫወታቸው እንጂ በእንቅስቃሴ ደረጃ የመጀመርያውን ጎል እስካስቆጠሩበት ጊዜ ድረስ ንግድ ባንኮች ተቸግረው የነበረ ሲሆን በ20ኛ ደቂቃ ሰናይት ቦጋለ አመቻችታ ያቀበላችን ኳስ በግራ እግሯ ገፍታ አረጋሽ ካልሳ በማስቆጠር መሪ ሆነዋል። ወደ ፊት በጥሩ እንቅስቃሴ ኳሱን ይዘው ይሂዱ እንጂ የጎል ዕድል መፍጠር አለመቻላቸው አርባምንጮችን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተፅዕኖ ሲያደርግባቸው ተስተውሏል። በዚህ ሂደት ውስጥ ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ ረሂማ ዘርጋው በጥሩ ቅብብል ወደፊት ይዛ የገባችው እና የአርባምንጭ ግብጠባቂዋ ድንቡሽ አባ ያዳነችው ኳስ በጨዋታው ሁለተኛ ግልፅ የጎል አጋጣሚ ነበር።

አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የቡድኑ እንቅስቃሴ ምቾት ያልተሰማቸው እንደሆነ እና መሻሻል አለበት ብለው ባሰቡት ቦታ በሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ የታክቲክ ለውጥ በማድረግ ሎዛ አበራ፣ እመቤት አዲሱ እና ብዙነሽ ሲሳይን ቀይረው ማስገባታቸው ተሳክቶላቸው ሎዛ አበራ ከአንድ አንድ ያገኘችውን ዕድል በ50ኛው ደቂቃ ወደ ጎል በመቀየር የንግድ ባንክን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋዋለች። ከዚህ በኃላ ቀሪ ባንክ የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የቻሉ ሲሆን ረሂማ ዘርጋው ከቀኝ የማዕዘን ምት መምቻው ያሻገረችውን ኳስ አረጋሽ ወደ ጎል አጥብቃ ስትመታው ሎዛ አበራ ደገፍ አድርጋ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች።

በጨዋታው ከዚህ በላይ ጎል እንደሚቆጠር ቢጠበቅም ብዙም የረባ ነገር ሳንመለከት በጨዋታው መጠናቀቂያ ሰባት ደቂቃዎች ሲቀሩት ረሂማ ዘርጋው በ83 እና 90ኛው ደቂቃ የግል ጥረቷ የታከለበት ሁለት ጎሎችን አከታትላ በማስቆጠር ጨዋታው በንግድ ባንክ 5–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

10:00 በቀጠለው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የአዲስ አበባ ከተማ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ጥቂት የማግባት ዕድሎች ተፈጥረውበት በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። የመጀመርያው አርባምስት በሁለቱም በኩል ያልተደራጀ መሐል ሜዳ ላይ ብቻ የተገደበ እንቅስቃሴ እያስመለከተን ቆይው በተመሳሳይ ከዕረፍት መልስ በዚሁ መልኩ ጨዋታው ቀጥሎ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል በመጨረሻው አስር ደቂቃ ድራማዊ ትዕይንት አስመልክቶናል።

በአዲስ አበባ በኩል ተቀይራ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ ጥሩ ትንቀሳቀስ የነበረችው ድንቅነሽ በቀለ በ79ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ጠርዝ ከርቀት ግሩም ጎል አስቆጥራ አዲስ አበባዎችን መሪ አድርጋቸው ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ በሚገርም ሁኔታ ከአንድ ደቂቃ በኃላ በረጅም የተላከን ኳስ በተከላካዮች ተደራርቦ የተመለሰውን ሳራ ነፍሶ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የአቻነት ጎል አስቆጥራ ቀሪውን የጨዋታ ደቂቃ መንፈስ ወደ ውጥረት ብትቀይረውም ተጨማሪ ሌሎች የጎል አጋጣሚዎችን ሳንመለከት ጨዋታው አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ